የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር ፲፪ ቀን በ UNESCO እንዲመዘገብና በኢትዮጵያም ብሔራዊ በዓል እንዲሆን በድጋሜ ተጠየቀ

የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር ፲፪ ቀን በዩኔስኮ እንዲመዘገብና በኢትዮጵያም ብሔራዊ በዓል እንዲሆን በድጋሜ ተጠየቀ።
በየዓመቱ ከጥምቀት በዓል ቀጥሎ የሚከበረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው በዓደባባይ ካሳያቸው ተአምራት መካከል የመጀመሪያ የሆነው በቃና ዘገሊላ ሠርግ ላይ ውኃውን ወደ ወይን የለወጠበት የተአምር በዓል ቃና ዘገሊላ በሚል ይከበራል።
በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ባለችበት ሁሉ በዐቢይ ክብር የሚከበረው ሲሆን ከበዓሉ ታላቅነት፣ሁሉን አሳታፊነትና መንፈሳዊነት አኳያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (UNESCO) ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል የቃና ዘገሊላ በዓል ዛሬ ጥር ፲፪/፳፻፲፯ ዓ/ም ላይ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የኦቶዶክሳውያኑን ጥያቄ በድጋሚ አቅርበዋል።
በዓሉ እንዲመዘገብ የዛሬ ዓመት በዚሁ ቅዱስ ቦታ መጠየቁ የሚታወስ ሲሆን አስፈላጊ ቀጣይ ሥራዎች እንደሚሠሩም ተገልጿል።
ዋና ሥራ አክኪያጁ አክለውም በዓሉ በሀገራችን ኢትዮጵያም ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲመዘገብና እንዲከበር ጠይቀዋል።
ቀጥለውም የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያናችን የምታከብራቸው በዓላት እግዚአብሔርን በጉልበታችን፣ በአንደበታችን፣ በምናውቀውና ባለን ጸጋና ሥጦታ የምናመሰግንበት በዓል እንጂ ሌሎች እንደሚሉት ሥጋዊ ሐሳብ ማንገሻ አለመሆኑን ልንረዳውና በቃልና በተግባር ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል።
በዓሉ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት መከበሩን ቀጥሏል።

©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ