የቀበና ምዕራፈ ጻድቃን አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ቅ/ገብርኤል አዲሱ መቃኞ ቤተ ክርስቲያን ተመረቀ
ታኅሣሥ 18/2013 ዓ/ም በካሳንችስ ዓድዋ ድልድይ የሚገኘው አዲሱ የተሠራ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና ቅ/ገብርኤል መቃኞ ቤተ ክርስቲያን ተመርቆ ተባርኳል።
በመርሃ ግብሩ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ብ ሳሙኤል ደምሴ፥ የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ እሰኪያጅ መጋቤ ትፍስሕት ግርማ አሰፋ፥ የየካ ክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ሠራተኞች፥ የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ መ/ሰላም አበበ አሸናፊን ጨምሮ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርከት ያሉ ምእመና የተገኙ ሲሆን፣ መ/አሚን ቆሞስ አባ ላ/ማርያም የአራዳ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በቦታው ተገኝተው አዲሱ የተሠራ ቤተክርስቲያን ባርከውታል።
በዕለቱ በመ/ብ ሳሙኤል ደምሴ የቤተ ክረስቲያን መሠረት በተመለከተ አጭር ትምህረት ተሰጥተዋል።
መምህሩ ክርስቶስ “እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” ብሎ ለሓዋርያት የጠየቀው ጥያቄና “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በሚለውን የስምዖን ጴጥሮስ መልስ መነሻነት ክርስቶስ ስለ ቤተ ክርስቲያን የተናገረውን ጥልቅ ምሥጢር በአጭር ጊዜ አመስጥረው አብራርተዋል።
ክርስቶስ “አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል” ብሎ በተናገረው መሠረት የመንግሥተ ሰማያት ቁልፋ ለካህናት ተሰጥተዋል፤ ይህ ደግሞ በቤተክርስቲያን በኩል በካህናት ይፈጸማል ብለዋል።
የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ልክ እንደ ምድራዊ በማመሳሰል የማይቀረጽ፥ ተመሳሳይ ሆነ አቻ የሌለው እውነተኛና ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያሰጥ ቁልፍ ነው ካሉ በኋላ ሁላችን ወደዚህ ሕይወት የሚወስደን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በካህናት የሚሰጠን ትምህርት ሰምተን በአንድነት ልንኖር ያስፈልጋል፤ ፍቅርና ሰላምም ሊኖረን ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም የደብሩ ዋና ጸሓፊ መ/ኃይል በላይ የአከባቢው ወጣቶች ሰ/ት/ቤት እና ካህናት የንስሓ ልጆቻቸውን በማስተባበር ላደረጉት ትብብር በቤተ ክርስቲያኑ ስም ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ