የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት!!

0896

ቀድሞ በነቢያት፣ ኋላም በሐዋርያት የተሰበከውና የተገለጠው የቤተ ክርስቲያን የጀርባ አጥንት በመሆን የእግዚአብሔርን ሕገ መንግሥት ሲያስፋፋ የቆየው ስብከተ ወንጌል ሲወርድና ሲዋረድ በመምጣት እኛ ባለንበት ዘመን መድረሱ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት ከደጋ እስከ ቆላ ስታዳርስ ቆይታለች፡፡
አሁንም ይህንኑ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ተግባርን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ በሆነው በርዕሰ መዲናችን በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡
የምንመገበው ምግብ፣ የምንለብሰው ልብስ፣ የምንጠለልበት መጠለያ የስብከተ ወንጌል ምርት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይህ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ በሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከመቼውም በተሻለ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ኅዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም ሊቀማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከአዲስ አበባ ከተማ አድባራትና ገዳማት ለተገኙ በርካታ የስብከተ ወንጌል ሠራተኞች የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ በሰጡት ማብራሪያ የሚከተሉት ቀጣይ የዕቅድ ተግባራት እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡
መደበኛ ሰባክያነ ወንጌልን በሀገረ ስብከቱ አይቲ እና ዶክመንቴሽን ክፍል በኩል ከነፕሮፋይላቸው መዝግቦ መያዝ፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ በስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ለይቶ ማወቅና ለችግሮቹ መፍትሔ መስጠት፣ ስለ ዘወትር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እና ዓበይት በዓላት እንዲሁም ልዩ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮች በተመለከተ ወጥ መመሪያ ማዘጋጀት፣ በነጻ አገልግሎት እንሰጣለን ስለሚሉ ሰባክያንና ዘማርያን በተመለከተ በማዕከል ፈቃድ ተሰጥቷቸው በሀገረ ስብከቱ በኩል ተረጋግጦ ካልሆነ በስተቀር ከመደበኛ አገልጋዮች ውጭ እንዳያገለግሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶችን በማካሄድ ጥብቅ መመሪያ ማስተላለፍ፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙትን ሰባክያን ስፖንሰር በማፈላለግ ወይም ከሀገረ ስብከቱ በጀት በማስፈቀድ ወቅታዊና አስፈላጊ በሆኑ ነጥቦች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የእውቀት ማበልጸጊያ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ ያሉትን ሰባክያን የአገልግሎት ዘመናቸውን እና ያሳዩትን የሥራ ፍሬ በመገምገምና በመለካት ወደተሻለ የሥራ ኃላፊነት ቦታ ላይ እድገት ተሰጥቷቸው እንዲሠሩ ማድረግ፣ ቋሚ የሆነ በ3 ወር አንድ ጊዜ የሰባክያነ ወንጌል አጠቃላይ ስብሰባ እንዲኖር ማድረግ፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከሥራ ኃላፊዎች ጋር ስለ ስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ በሰፊው በመወያየት ለችግሮቹ መፍትሔ እንዲሰጡ ማድረግ፣ በየጊዜው በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ስለሚካሄዱ ጉባዔዎች ከክፍለ ከተማ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ጋር በመሆን በየአብያተ ክርስቲያናቱ በመገኘት ቁጥጥር ማድረግ፣ በዓመቱ ውስጥ በአጠቃላይ በሁሉም ክ/ከተሞች የስብከተ ወንጌል ቀን እንዲኖር ማድረግ፣ የልምድ ልውውጦችን ማካሔድ፣ ስለአንድነት ጉባዔው ጠቃሚነት ስለአጋጠሙ

ችግሮች ተወያይቶ መፍትሔ መስጠት፣ ስለ ጣልቃ ገብ አካሎች በመወያየት መፍትሔ መስጠት እና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የስብከተ ወንጌል ሥራ ማስኬጃ በወጥነት እንደየአብያተ ክርስቲያናቱ የገቢ መጠን ከሀገረ ስብከቱ የፋይናንስና በጀት ዋና ክፍል እና ከሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር በተመሳሳይ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ለስብከተ ወንጌል የሥራ ማስኬጃ በጀት እንዲኖራቸው ማድረግ ሲሆን ዝርዝር እቅዶቹ በቀጣይ በስፋት የሚዘጋጁ ይሆናል፡፡
ከአድባራትና ገዳማት የመጡት የስብከተ ወንጌል ሠራተኞችም በቀረቡት ዝርዝር የሥራ ተግባራት ነጥቦች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡ በተሰብሳቢዎቹ የቀረቡት ሐሳቦች የተሃድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያናችን ህልውና ላይ እያደረሰ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ፣ በአድባራትና ገዳማት በኩል ለስብከተ ወንጌል የሚመደበው በጀት አናሳ መሆኑ፣ የስብከተ ወንጌል ፈቃድ ሳይሰጣቸው እንሰብካለን የሚሉ ሕገ ወጥ ሰባክያን በምዕመናን ዘንድ የሚፈጥሩት የመለያየት ችግር፣ የአንዳንድ ሰባክያን የብቃት ማነስ ችግር፣ ለምእመናን በቂ ትምህርት አለመስጠት፣ ሰባክያኑ የማኅበራት የጥገኝነት ሰለባ መሆን፣ አንድ አንድ የአድባራት አለቆች ለስብከተ ወንጌል ትኩረት አለመስጠት፣ ቀደም ሲል በሀገረ ስብከቱ የነበረው የሥራ አመራር ለስብከተ ወንጌል ትኩረት አለመስጠት፣ በንጹሐን አገልጋዮች ላይ የሚሰነዘረው መልካም ስምን የማጉደፍ ተግባር፣ ማኅበራት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚፈጥሩት አሉታዊ ተፅዕኖ፣ ለአድባራትና ገዳማት የስብከተ ወንጌል ሠራተኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና አለመስጠት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመተባበር ችግሮቹን በዘለቄታ የሚፈታ ኮሚቴ ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ቁጥራቸው ከዘጠኝ ያላነሱ ኮሚቴዎች ተመርጠዋል፡፡ በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀገረ ስብከቱን የሥራ አፈጻጸም፣ የስብሰባውን ሒደትና ዝርዝር የሥራ መመሪያን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት፡፡ በተግባር የሚገለጽ ሥራ ያስፈልጋል፤ ለስብከተ ወንጌል ወጥ መመሪያ ይወጣል፤ በዐበይት በዓላት ጊዜ ትልቅነት የሚሰማቸው ሰባክያን በነፃ አገልግሎት እንሰጣለን በሚል ግሩፕ እየመሠረቱ ናቸው፤ እነዚህ ወገኖች እገሌ መናፍቅ ነው እያሉ ስም የሚሰጡ ናቸው፡፡ እገለ መናፍቅ ነው ብለን መፈረጅ የእኛ ሥልጣንና አቅም አይደለም፡፡ ይህ ሥራ የሚመለከተው አካል አለ፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ማለት አይቻልም፤ በሃይማኖት ህፀዕ የተጠረጠረ ሰው በመጀመሪያ ይጠየቃል፤ አቋሙ የተለየ ሆኖ ከተገኘ ነው የሚወገዘው፡፡ ስለጣልቃ ገቦች ተወያይቶ መፍትሔ መስጠት ይገባል፤ የቤተ ክርስቲያን ፈተና የሆኑት ማኅበራት በየጊዜው እየተፈለፈሉ ናቸው፡፡ ከሰባክያነ ወንጌል ጋር መወያየት ደስ ያሰኛል፤ ከሰባከያን ጋር መነጋገር ከትልቅ ሰው ጋር እና ንግግር ከለመዱ ሰዎች ጋር መነጋገር ማለት ነው፤ ሰባኪ በሃይማኖት ህፀዕ መጠርጠር የለበትም፤ ለምንስ ይጠረጠራል?
ጠርጣሪውስ ማን ነው? አጣሪውስ ማንነው? ብዙ ሰዎች ከመስመር ወጥተው እየተደናበሩ ናቸው፤ ጫካ ውስጥ ገብተን በዘንዶ ወይም በነብር መካከል ልንወድቅ እንችላለን “ቶማስ ቶምስ የተባለ ምሁር ስለመንግሥታት አመጣጥና ስለሀገራት አመሠራረት ሲናገር በተፈጥሮ ሁሉም ሰው እኩል ነው፡፡ ብዙ መሮጥ የማይችሉ ሰዎች አሉ ሁሉም ፀረ ሁሉም ነበር፡፡ ሁሉም ሰው ማንን ይጠረጥራል ሳያጠፋኝ ላጥፋው ይላል፤ የማይተዋወቅ ሰው የጋራ ዓላማ ሊኖረው አይችልም፤ ለአንድ ዓላማ የቆሙ ሰዎች መተዋወቅ አለባቸው፤ ለስብከተ ወንጌል መዳከም ተጠያቂው ሰባኪው ነው፡፡ አስተዳዳሪው ሳያውቅ ሰባኪው የሚሠራ ከሆነ ሕገወጥ ነው፤ አረም ማለት ሕገ ወጥ ተክል ሳይሆን ባልተፈለገበት አካባቢ የሚበቅል ነው፤ ማፈንገጥ ሕገ ወጥነት ነው አለቃና ሰባኪ ሳይፈቅዱለት የሚሰብክ ሕገወጥ ነው፤ ራሳችንን ማሻሻል አለብን፤ ወደ ውስጥ ማየት አለብን፤ እራሳችንን ካሻሻልን ሁሉም ቃላችንን ይሰማል፤ ራሳችንን ካላሻሻልን ደጀጠኚዎች ነን፤ ወገቡን ጠበቅ አድርጐ የታጠቀ ሰው ነው መሪ መሆን የሚችለው ስብከተ ወንጌል ብዙ ሥራ ያለበት ቦተ እንጂ የሥራ ፈት ሥራ አይደለም ሕገ ወጦች በዕውቀት ያነሱ ናቸው፤ የተማረ ሰው ገንዘብ አያከማችም ህልም የሚያየው ሁሉ ሰባኪ እየሆነ ነው፤ ሞንታርቦ ሊሰብክ አይችልም፤ ቤተ ክርስቲያንን እያዋረድን እኛ ትልቅ መሆን አንችልም፤ ሁልጊዜ የችግር ባለቤት የምናደርገው ሌላውን ነው፤ በማማተብ የሚሄድ ሰይጣንን እንዴት ማባረር አቃተን? አድር ባይ ሰባኪ እንዴት ሰባኪ ሊሆን ይችላል? የሚሰርቅ ሰው ሰባኪ ሊሆን አይችልም፤ ከአስተሳሰብ የበታችነት ነፃ መውጣት አለበን፤ ነፃ የወጣ ጭንቅላት ሊኖረን ይገባል፤ ሥራውን ወዶ የሚሠራ ሰው ሀብታም ይሆናል በማለት ዋና ሥራ አስኪያጁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም የዝግጅት ክፍላችን በሀገረ ስብከቱና በሰባክያን ተወካይ ኮሚቴዎች የጋራ ጥረት የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ለውጥ ዙሪያ የሚከናወኑትን ተግባራት እየተከታተለ መረጃውን ለአንባብያን ለማድረስ የሚሠራ መሆኑን እየገለጽን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍልም የተጣለበትን ታላቅ ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባል እንላለን፡፡

{flike}{plusone}