የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የታኅሣሥ ቅዱስ ገብርኤልን በዓል አስመልክቶ በተለያዩ አህጉረ ስብከቱ ለሚላኩ መምህራን መመሪያና የተልእኮ አቅጣጫ በመስጠት ማሠማራቱን ገለጸ

የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የታኅሣሥ ቅዱስ ገብርኤልን በዓል አስመልክቶ በተመረጡ አህጉረ ስብከቱ ለሚላኩ መምህራን መመሪያና የተልእኮ አቅጣጫ በመስጠት ማሠማራቱን ገለጸ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐትና ትውፊት መሠረት በየዓመቱ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በዓል በዐቢይ ክብር ይከበራል።
በዓሉ ቅዱስ ገብርኤል በእምነታቸው የኖሩ ለታመኑለት አምላክ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ፣ ናቡከደነጾር በዱራ ሜዳ ላቆመው ምስል ያልሰገዱ ብቻቸውን እውነት ጋር የቆሙ ሦስቱ ወጣቶችን (ሠለስቱ ደቂቅ) ከሚነድ እሳት ያደነበት በዓል መሆኑን ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ መጽሐፍን ዋቢ አድርጋ ታስተምራለች።
በመሆኑም በዓላት መምህራን ወደ ሁሉም ቦታ ማሠማራት ልምድ ያለው የመንበረ ፓትርያርክ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በዚህ ዓመትንም የተለያዩ መምህራን የቅዱስ ገብርኤል በዓልን ወደ ሚከበርባቸው አብያተ ክርስቲያናችን በመለየት ወደ ተለያዩ አህጉረ ስብከት እንደሠማሩ ተልእኮ ሰጥቷል።
ይህንን አስመልክቶም ለበዓሉ የሚሰማሩ መምህራንን በመሰብሰብ በዛሬው ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አጽርሐ ተዋሕዶ አደራሽ መምሪያና የተልእኮ አቅጣጫ ለመስጠት የሥምሪት መርሐ ግብር አአከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሊቀ ጳጳስ፣ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የመምሪያ ዋና ሐላፊ ፣ መጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚእ አሰፋ የትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ሐላፊ ፣ መምህር ዘማርያም ጌጡ የየስብከተ ውንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ምክትል መምሪያ ሐላፊ፣ የመምሪያው ዋና ጸሐፊ መጋቤ ሐዲስ ሽፈራው እንደሻው ፣ የመምሪያ የሥራ ሐላፊዎች ፣ መደበኛ የዕለተ ረቡዕ ጉባኤ መምህር መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር እንዲሁም የስምሪቱ አካል የሆኑ በርካታ መምህራንና የጉባኤ ታዳሚዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ወጥነት ያለው ትምህርትና መልእክት መምህራን ያስተላልፉ ዘንድ በመጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር የታኅሣሥ ቅዱስ ገብርኤል በዓል ታሪካዊ ዳራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት በተለይም የሠለስቱ ደቂቅ የእምነት ተጋድሎ በተረዳና በጎላ መልኩ አሳይተዋል።
አክለውም በዓሉ የሚሰጠው ትምህርተ ወንጌል በልጅነት እግዚአብሔርን ከማወቅ ጀምሮ በፊቱ እስከ መክበር ድረስ ያለው የክርስትና ጉዞን ከሠለስቱ ደቂቅን አርአያነት ያለውን ሕይወት ዋቢ በማድረግ ማስተማር እንደሚገባው ተቁመዋል።
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሊቀ ጳጳስ በኩላቸው መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር ለሰጡት ጥልቅና ግልጽ ማብራሪያ አመስግነው ትምህርቶቻችን መሠረት ያላቸውና ሕይወትን የሚያሻግሩ መሆን ይባቸዋል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም ወንጌል በቃልና በሕይወት በማስተማር ወጥነት ባለው መልኩ የበዓሉን መልእክት እንዲያስተላልፉ መምሪያ ሰጥተዋል።
መልአከ ሰላም ዳዊ ያሬድ የመምሪያ ሐላፊ በበኩላቸው የተላኩ ልዑካን በተላኩበት አህጉረ ስብከት በመገኘት የቅድስት ቤተክርስቲያንን ተልእኮ መምሪያውንና ቅድስት ቤተክርስቲያንን በሚመጥን መልኩ በተሰጠው የስምሪት አቅጣጫ( ኦሬንቴሽን) መሠረት እንዲያገለግሉና በሄዱበት ወይም በተሰማሩበት አህጉረ ስብከት ያለውን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በሪፖርት መልኩ ግብረ መልስ ይዘው እንዲመጡ መምሪያ አስተላልፈዋል።