የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን ደቀ መዛሙርት አስመረቀ
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ኮልፌ ክፍለ ከተማ የሚገኘውና ከሦስቱ መንፈሳዊ ኮሌጆች መካከል አንዱ የሆነው እንዲሁም በርካታ የቤተ-ክርስቲያንን ምሁራንን ያፈራውና በማፍራት ላይ የሚገኘው ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ላይ ለሦስትና ለአምስት ዓመታት አስተምሮና አሰልጥኖ ያበቃቸውን ማለትም በሐዲሳት ትርጓሜ መጻሕፍት ትምህርት 12 ደቀመዛሙርት፤በመደበኛው ሴሚናሪ ትምህርት 31 ደቀ መዛሙርትና በማታው መርሐ ግብር ሴሚናሪ ደግሞ 213 ደቀመዛሙርትን በድምሩ 256 ደቀ መዛሙርትን በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በዛሬው ዕለት በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ፡፡
የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይም ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያሪክ፤ የመ/ፓ/ጠ /ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁእ አቡነ ያሬድ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ብፁእ አቡነ ዮሴፍ፤ የስዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስመንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ብፁእ አቡነ ሕዝቅኤልና ሌሎችም በርካታ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያውና የድርጅት ኃላፊዎች፤ የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን መጋቤ ብርሃናት ተስፋዬ ሀደራ፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኃላፊዎችና ሠራተኞች በርካታ የአስመራቂ ቤተሰቦችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።
የመንፈሳዊ ኮሌጁ ዋና ዲን መ/ር ልሳነ ወርቅ ደስታ የምርቃት ሥነ ሥርዓቱን አስመለክተው ባቀረቡት ሪፖርት በብዙ ውጣውረድ አልፋችሁ ለዛሬው የምርቃት ቀን ለደረሳችሁ ተመራቂ ደቀ መዛሙርት እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ መንፈሳዊ ኮሌጃችን በአካዳሚክ ዘርፍ ከሚሠራቸው ጠንካራ ሥራዎች በተጨማሪ በአስተዳደርና በልማት ዘርፍ ላይ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፤ በመሥራትም ላይ ይገኛል።
ነገር ግን በተፈለገው ፍጥነትና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሥራዎችን ለመከወን ያስቸገሩ ሁኔታዎች እንዳጋጠሟቸው ተናግረው ችግሮቹንም ሲያስቀምጡ በካሪክለም ችግር የተነሣ ደቀ መዛሙርቱ የሚማሩበት ጊዜ ረጅም ሆኖ ሳለ የሚመረቁበት ማዕረግ ግን ከሴሚናሪና ዲፕሎማ ያልዘለለ መሆኑ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጥናት ቢቀርብም ጥናቱ ተግባራዊ አለመሆኑ፤ የኮሌጁ መምህራን ሙያቸውን ለማሻሻል የሚችሉበት የአቅም ግንባታ ሥልጠና አለመሰጠቱ፤ በጀት የተፈቅደለት የጥናትና ምርምር ማእከል አለመኖሩ፤ ኮሌጁ ከልማዳዊ አሠራር ወጥቶ በተቀናጀና በተደራጀ ዘመናዊ አሠራር አለመደራጀቱና ሌሎችም መሆናቸውን ገልጸው ወደፊትም ቢሆን ትኩረት ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
እነዚህም የትኩረት አቅጣጫ የሚያስፈልጋቸው ነጥቦች ኮሌጁ ከሁለቱ አቻ ኮሌጆች ጋር ተመሣሣይ በጀት እንዲመደብለት፤ የኮሌጁ መምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠና ቢመቻችላቸው፤ በበጀት የተደገፈ የጥናትና ምርምር ማእከል ቢቋቋምና በየዓመቱ ከሚመረቁ ደቀ መዛሙርት መካከል ብልጫ ያስመዘገቡትን ኮሌጁ በተተኪ መምህርነት ቢያስቀር የሚሉ ናቸው፡፡
ቅዱስ ፓትርያሪኩም ለሁሉም ደቀ መዛሙርት ቡራኬና ሰርተፈኬት ከሰጡ በኋላ ባደረጉት አጭር ንግግር ለተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ጀምረው የሚጠበቃቸው ሐላፊነት ከባድ ከመሆኑም ባሻገር የነፍስ አድን ተግባር መሆኑን ተገንዝበው ራሳቸውን በሚገባ እንዲያዘጋጁ አሳስበው መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል፡፡
በምርቃት ሥነ ሥርአቱ ላይ ተገኝተው የነበሩ አንዳንድ ግለ ሰዎች እና የዕለቱ ተመራቂ ደቀ መዛሙርት እንደተናገሩት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከፊደል ማስቆጠር ጀምሮ በትምህርት ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ በማስተማር ረገድ ተወዳዳሪ የማይገኝላት ትልቅ ተቋም ስትሆን በሚልዮን ለሚቆጠሩት ተከታዮቿና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አገልጋዮች ሦስት የሥነ መለኮት ኮሌጆች መክፈት ፈጽሞ በቂ አለመሆኑን ተናግረው፣ ከእነዚሁም ሦስት መንፈሳዊ ኮሌጆች ተመርቀው ለሚወጡት ምሩቃን የሚመደበው በጀት የወቅቱን የኑሮ ሁኔታ ያላገናዘበ፤ የትምህርት ዝግጅታቸውንና ድካማቸውን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ከመሆኑም ባሻገር የአገልጋዮችን ሥነ ልቦና የሚሰብርና ወደፊት ቤተ ክርስቲያንን ተረክቦ ሊመራ ለሚችለው የተማረ የሰው ኃይል ትኩረት መነፈጉን የሚያሳይ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገበል ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚድያ ክፍልም ከላይ በአስተያየት ሰጪዎች የተሰነዘሩ ሐሳቦችን በእጅጉ እየተጋራ ለተመራቂ ደቀ መዛሙርትና ቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ አላችሁ እያለ መልካም የአገልግሎት ዘመን ይሆንላችሁ ዘንድ ጽኑ ምኞቱን ይገልጻል።
በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሚድያ ክፍል