የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ያስተማራቸውን ደቀመዛሙርት በዲፕሎማ አስመረቀ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰዋስወ በርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማታውና በቀን መርሐ ግብር ያስተማራቸውን ደቀመዛሙርት ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት በዲፕሎማ አስመረቋል፡፡ በምረቃው መርሐ ግብር ላይ በተመረቂ ደቀመዛርት ያሬዳዊ ለብ ቀርቧል፤ በተለያዩ የቅኔ ባለሙያዎች ቅኔያት ቀርበዋል፤ ኮሌጁ ካስመረቃቸው ደቀመዛሙርት መካከል አንድ የብሉይ ኪዳን ትርጓሜ ደቀመዝሙር በመምህርነት፣ አንድ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ደቀመዝሙር በመምህርነት የተመረቁ ሲሆን በተጨማሪም በማታው የትምህርት መርሐ ግብር ሁለት መቶ ደቀመዛሙርት እና በቀኑ መርሐ ግብር አሥራ አንድ በድምሩ ሁለት መቶ አሥራ ሶስት ደቀመዛሙርትን ኮሌጁ በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡
ደቀመዛሙርቱ በተመረቁበት ወቅት የኮሌጁ ዲን መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወ/ሐና ባቀረቡት ሪፖርት በመማር መስተማሩ ሂደት ከባድ ፈተና ያጋጠማቸው መሆኑን ሲገልጹ የፈረሰውን ስንገነባ ለምን ሆነ? የወደቀውን ስናነሳ ለምን ሆነ? የተጣመመውን ስናቃና ለምን ሆነ? የጎደለውን ስንሞላ ለምን ሆነ? የተበተነውን ስንሰበስብ ለምን ሆነ? መምህራን እንዲተኩልን በጽሑፍ ስንጠይቅ መልስ ያለመስጠት፤ በጣም አስቸኳይ ለሆኑ ነገሮች ደብዳቤ ስንጽፍ የደብዳቤዎች ደብዛ መጥፋት እና በዕለት ተዕለት ሥራዎቻችን ላይ ጣልቃ መግባት የሚል ይገኝበታል፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት ችግሮቹ በጥናት ተደግፈውና በመረጃ ተጠናክረው ከመጡ አስፈላጊውን መፍትሔ ማግኘት እንደሚችሉ በመግለጽ እና ለመንፈሳዊ ኮሌጆች እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው፤ ይልቁንም በኮሌጆቹ እየተመረቁ የሚወጡ ተመራቂ ደቀመዛሙርት ቤተክርስቲያንን ጠንክረው እንዲያገለግሉ በማለት አባታዊ መመሪያ ሰጥተው የምረቃው መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡
{flike}{plusone}