የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ተካሄደ
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤው በዛሬው እለት ህዳር 27 ቀን 2013ዓ.ም ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የጉራጌና የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ የኬንያ፣ የታንዛኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት፣መ/ር ዕንቆባህሪ ተከስተ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ በተገኙበት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብሰባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
የጉባኤው ዋና ዓላማ በአንድነት በመሆን ቤተክርስቲያንን ለማገልግል፣ከብፁዓን አባቶች መመሪያ ለመቀበል፣አዳዲስ የተሾሙ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አመራሮችን ለማስተዋወቅና ከብፁዓን አባቶች ቡራኬ እንዲቀበሉ ለማድረግ፣እርስ በእርስ በመመካከርና በመወያየት ሥራ ለመሥራት፣ለሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉልህ ሚና ለፈጸሙ የሽልማትና የምሥክር ሰርተፊኬት ለማበርከት እነደሆነ ከመድረኩ ተደምጧል፡፡
በጉባኤው ላይ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤ/ን የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ዝማሬ አቅርበዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞ ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት የሐዋርያውን የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕ 11 ቁጥር 16 ላይ የሚኘውን “ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው” የሚለውን ሕያው የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል መነሻ በማድረግ ትምህርተ-ወንጌልና አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕነታቸው አያይዘውም “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ” (ዮሐ 15፡5) የሚለውን የክርስቶስን ትምህርት አንስተው በክርስቶስና በአማኞች መካከል ያለውን መንፈሳዊ ትስስር አብራርተውና አመሳጥረው አስተምረዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የጉራጌና የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት “የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በማስተላለፍ” የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በሀገረ ሰብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ቀጣይነት ባለው መልኩ በመሰብሰብ መንፈሳዊ ምክክሮችን እንዲያደርጉ ፈቅደዋል፡፡በጋራ በመሆን ሁላችንም የተሰጠንን መንፈሳዊ ሐላፊነት በበቂ ሁኔታ እንወጣ በማለት አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ከተመሠረተ ጀምሮ ትልቅ አሰትዋጽኦ ላደረጉና ጉልህ ሚና ለፈጸሙ አባቶችና ወጣቶች በሦስት ደረጃ በመክፈል የሽልማትና የምሥክር ሰርተፊኬት በብፁዓን አባቶች ተበርክቶላቸዋል፡፡
መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ የሀገረ ስበከቱ ዘጋቢ