የሰሜን አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ መልዕክት አስተላለፉ

ቃለ እግዚአብሔር ተንሥአ ወሥጋሁኒ ኢማሰነ

የእግዚአብሔር ቃል ተነሣ ሥጋውም ጥፋት አላገኘውም፤ መበስበስም አልገጠመውም ሥ.ቅዳሴ 256

4
መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ መልዕክት

ከዘመናት ቁጥር ልኬት በአፍአ የሚኖር ዘመን እና ዘመናት የማይወስኑት መጀመሪያ በሌለው ቅድምና የነበረ ቃል፣ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረ፤ እርሱ እግዚአብሔር፤ አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም ሥጋን ተዋሃደ፤ ከኃጢአት በቀር በሁሉ እኛን መሰለ፤ እኛንም ስለማዳን ለመሰቀል ሞት እንኳን ታዘዘ፤ ድካማችንን ተቀበለ፣ ሕማማችንን ታመመ፤ ስለ እኛ ቆሰለ፣ ስለበደላችንም ደቀቀ፤ ከመነገር በላይ የሆነውን ፍቅሩን አሳየን፡፡

እርሱ አምላካችን መስማት ላልቻሉት የመስሚያ ጆሮ፣ የረሃብተኞች መጋቢ፣ ለተጠሉት እና ለተረሱት የቅርብ ወዳጅ፤ የዕውራን ብርሃን፤ የአንካሶች መጽናኛ የሆነ አዳኛችን በእኛ ስለእኛ ተናቀ፣ ተጠላ፣ እንደተቸገረ ቆጠርነው እንኳን ሊጨክኑበት አትኩረው ሊያዩት የሚያሳሳውን በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ አሳራፊውን አንገላቱት፤ አሳላፊውን አሳልፈው ሰጡት፤ የዘመናት የአዳም ዘር ጥያቄ የ5500 ዘመን አደናጋሪ እንቆቅልሽ ይፈታ ዘንድ፤ ከሞት ቀንበር ከኃጢአት ማዕሰር ከሲኦል ሀገር፤ ከመጨካኙ መንደር፤ ነፃ ያወጣን ዘንድ ኤፍታህ ብሎ የፈታ ስለ እኛ ታሰረ በቁጣ ሲጎትቱት በፍቅር ተከተለ፤ ቀንበርን ሊሰብር አመፃን ጥሎ ጽድቅን ሊጨምር ከወንበዴዎች ጋር ተደመረ፡፡

ክብር ይግባውና የኃጢአታችን ዋጋ የሆነውን ዕዳ ከፈለልን እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ ቀድሞ በነቢያት እንዳናገረው ከመቃብራችን ሊያወጣን በመቃብር አደረ የሞትን ኃይል ይሰብር ዘንድ የኃያላን ኃያል በስጋ ሞተ፡፡ አስጨናቂያችን የሆነውን ሞትን ይገድል ዘንድ ሞተ፤ መቃብርን ባዶውን አስቀርቶ ሞትን ያሳፍረው ዘንድ እኛም አፋችንን ሞልተን እንዝትበት ደግሞም እንሳለቅበት ዘንድ ሞትን ቅስሙን ሰብሮ፤ ቈዬውን መዝብሮ፤ ነፍሳትን ማርኮ፤ በታላቅ ኃይልና ስልጣን በቃሉ እንደተናገረ በሥራውም ብርቱ የሆነ አዳኝና ነፃ አውጪ ስለ መንጋዎች ነፍሱን እንዳኖረ ሁሉ ነፍሱን ያነሣ ዘንድ ሰዓቱ ሆነና በእግዚአብሔርነት ኃይሉ በኀቱም ድንግልና የተወለደ ከኀቱም መቃብር በክብር ተነሳ፡፡ ዮሐ. 10፣17-18 ወተንሣእኩ በሥልጣነ ባኀትትየ ስለዚህ የተከበራችሁ ሕዝበ ክርስቲያን የዘመናት ዋይታችን ጥያቄ ተመልሷል፡፡

እንደወጣን አልቀረን፤ እንደናፈቀን አልተተውንም፤ እንደራበንና እንደጠማን አልቀረንም፤ ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን ሰጠን ሞት ድል በመነሳት ተዋጠ የተባለው ቃል ተፈፀመ፡፡ ኢሳ 25፣8 የድል ነሺው ልጆች ነንና እንደ ቅዱስ ዳዊት በአምላካችን ኃይል በጠላታችን በአጋንንት ላይ ተራመድን እንግዲህ ሁሉ ይስማ ለቀረቡት ብቻ አይደለም ለራቁትም ሰላም ሆኗል፡፡ ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ተነስቷል፤ የሲዖል ደጆች ተከፍተዋል፤ ነፍሳት አርነት ወተዋል፤ ንጉሳችን በክብር ከፍ ከፍ ብሏል፤ በጨለማ ለሚኖር ህዝብ ታላቅ ብርሃን ሆኗል፤ ብርሃንን የሚጎናፀፈው ተነስቷልና፡፡ አሁንስ ይሁን ይደረግልንና በትንሣኤው ኃይል እንድንነሳ ክብሩን እንድናገኝ እንትጋ፡፡ ፊል. 3

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችሁ ጋር ይሁን፡፡

መልካም የትንሣኤ በዓል

መ/ሰላም ቀሲስ ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ