የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ መልዕክት
በስመአብ ወወልድ ወመነፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ
የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ መልዕክት
ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዋለበት እየዋሉ ከአደረበት እያደሩ ረቂቅ የሆነውን ሰማያዊ ምሥጢር ተአምራትንና መንክራትን እያዩ ቃሉን ኢየሰሙ ዓለምን ሁሉ አስተማሩ፤ ዓለምን በደሙ አድኖ ተነሥቶ ካረገ በኋላ መንፈስ ቅዱስን ገንዘብ አድርገው በእኔ ያመነ እኔ የምሠራውን ይሠራል ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት እሱ ይሠራው የነበረውን እየሠሩ ኑረዋል፡፡ ለቀጣዩ ትውልድም አስተላልፈዋል፡፡ ቀጥለው የነበሩና ያሉ ሊቃውንትም ተመርምሮ በማያልቅ መንፈሳዊ ጥበብ ሲራቀቁ ቆይቷል፡፡ እየተመራመሩም ይገኛሉ፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው ነፍስ ያለሥጋ ሥጋም ያለነፍስ መቆም አትችልም እንዳለው መንፈሳዊን በመንፈሳዊ ጥበብ ሥጋዊውን ለሥጋ በሚያመቸው መሠረት በምድራዊ ጥበብ ማለትም በግዙፉ እግዚአብሄር ከፈጠረው ከመሬት በተገኘው ቁሳቁስ ሲመራመሩ ቆይቷል፡፡ አሁንም የዘመኑ ትውልድ ጥበብን የሚገልጽ መንፈስ ቅዱስ ገልጾላቸው አባቶቻችን በረቂቅ መንፈስ ሲጓዙት የነበረውን ሕዋ በረቂቅ አየር ሲጓዙት ይገኛሉ፡፡ በዚሁ መነሻነት ቤ/ክርስቲያናችንም የመሪዋ የኢየሱስ ክርስቶስንና የሐዋርያትን ረቂቅ መንፈሳዊ ጥበብን ሳትለቅ ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ እየተጠቀመች ትገኛለች፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሀገሪቱ የታሪክ የኢኮኖሚያዊ፤የማህበራዊ፤ሥልጣኔና ዕድገት በረዥም ዘመን ጉዞዋ ያበረከተችው እሴት ለአፍሪካዊያን መኩሪያና ለመላው ዓለም በታሪክ መዝገብ ከፍተኛሥፍራየሚሰጣት ቤተክርስቲያን መሆንኗ ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡
ለሀገራችን የታሪክና የመልካም ገፅታ መንፀባረቂያ የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ለሀገራችን ዕድገትና ህዳሴ ትልቅ ድርሻ አበርክታለች አቅም በፈቀደ ሁሉ አሁንም ድርሻዋን በማበርከት ላይ ትገኛለች፡፡ በሀገሪቱ ዋና መዲናችን በአዲስ አበባ ከተማና በኢትዮጵያ የሚገኙት ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት ከመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ባሻገር ለሀገሪቱ ማንነት የስኬት ውጤት ዋና መሠረቶች ናቸው፡፡በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ጥንታውያን አድባራትና ገዳማት /ካቴድራሎች/ ለምዕመናን በየቀኑ ከሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኝዎች በቱሪስት መስህብነት የሚሰጡት አገልግሎት በእጅጉ የላቀ ነው ፡፡ይህም የሀገሪቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ ከመግለፅ ባሻገር በቱሪዝሙ ረገድ ለሀገሪቱ እድገትና ምጣኔ ሀብት እንዲሁም ለጥናትና ምርምር የሚሰጡት አገልግሎት/አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
በመሆኑም በአዲስ አበባ የሚገኙ ታሪካዊያንና ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናትን የበለጠ ለማወቅ የተዘጋጀው ይህ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ድረ ገጽ ለአብያተ ክርስቲያናት ጠቃሚ መረጃን ከመስጠት በተጨማሪ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ሀገር ጎብኚዎች የማንነት መገለጫ የሆኑትን ታሪካዊ መረጃዎችን በመስጠት የሚሰጡት አገልግሎት ጠቀሜታው እጅግ በጣም የላቀነው ብዩ አምናለሁ፡፡
በመሆኑም ቤተክርስቲያችን ብዙ ዘመናትን ተሻግራ አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ የደረሰች ሲሆን ከአባቶቻችን የተረከብነውን ሃይማኖት ለትውልዱ ዘመኑ በሚፈቅደው መሳሪያ በመገልገል ሐዋሪያዊ መልዕክት ማስተላለፍ አስፈላጊነው ፡፡ ወጣቱ ትውልዱ ቴክኖሎጂውን ሲጠቀም መንፈሳዊ ትምህርትም በያሉበት እንዲያገኙና በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲጠነክሩ/እንዲበረቱ ማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ከመሆኑም በተጨማሪ አጠቃላይ የአህጉረ ስብከቶችም ይሁን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ መልዕክት ለማስታላለፍ ጥሩ አማራጭ መንገድ ነው።በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያናችን በተለይም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከቶች በቴክኖሎጂው መስክ እየተሠራ ያለው ሥራ ጅምሩ የሚበረታታ ቢሆንም ከሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ አኳያ ሲታይ ግን ገና ብዙ የሚጠበቅብን በመሆኑ የተጀመሩትን መልካም የሥራ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪዩን አቀርባለሁ ፡፡
መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ መልዕክት