የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በአሸባሪው ህውሓት የደረሰበትን ሁለንተናዊ ጉዳት የሚያጠና ቡድን አቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ገለጸ !!!
በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በተለያዩ ወረዳዎች በአሸባሪው የህውሓት ቡድን በካህናት እና በምእመናን ሕይወት የደረሰውን ጭፍጨፋ፣ እንዲሁም በገዳማትና አድባራቱ የደረሰውን ቁሳዊ ጉዳትና ውድመት የሚያጠና የልኡካን ቡድን አቋቁሞ የጥናት ሥራ መጀመሩን ከጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በተሰጠው የሥራ መመሪያ መሠረት የልኡካን ቡድኑ በጦርነቱ የደረሰውን የጉዳት መጠንና ውድመት ለይቶ ከማጥናት ባሻገር የችግሩ ሰለባ የሆኑ ወገኖችን ማጽናናትና ማስተማርንም እንደሚጨምር አቅጣጫ መስጠታቸው ተገልጿል።
በየቦታው የደረሰውን የጉዳት መጠን በትክክል ለይቶ ለማስቀመጥ የወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎችን የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችንና ልዩ ልዩ አገልጋዮችን፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትን እንዲሁም የአካባባውን ምእመናንና የሰ/ት/ቤት ወጣቶችን በግብዓትነት እንደሚያሳትፍም የጥናት ቡድኑ አስረድቷል።
በተጨማሪም ከሚመለከታቸው የመንግሥት አመራሮች እና የጸጥታ አካላት፣ ከታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች እና የዕድር አመራሮች ጋር በቃለ ጉባኤ የተደገፈ ተገቢ ውይይት እንደሚደረግ ተመልክቷል።
በችግሩ ሰለባ የሆኑ አገልጋይ ካህናትን እና ምእመናንን: ውድመት የደረሰባቸውን የአብያተ ክርስቲያናት ቅርሶች እና አብነት ትምህርት ቤቶችን በፍቶግራፍ፣ በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ በማሰባሰብ ውጤቱን በአጭር ጊዜ ይፋ ይደረጋል ሲልም ሀገረ ስብከቱ ገልጿል።
በመ/ር ሽፈራው እንደሻው