የረቢ መካነ ጎልጎታ መድኃኔዓለም ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ መዘክርና ሁለገብ አዳራሽ ተመረቀ

d00200

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የረቢ መካነ ጎልጎታ መድኃኔዓለምና ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ከአስር አመታት በላይ የግንባታ ሥራው የቆየውን ሁለገብ አዳራሽና ቤተ መዘክር ብፁዕ አቡነ ሰላማ የምሥራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጰጳስ፣ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን፣የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እና በርካታ ምእመናን በተገኙበት እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም ተመርቋል፡፡
የግንባታ ሥራው ተጠናቅቆ ለምረቃ የበቃው ሕንጻ ባለ አንድ ፎቅ ሁለገብ አዳራሽና ቤተ መዘክር የሕንጻ ሥራው በሚከናወንበት ወቅት የነበረው ፈተና ከፍ ያለ እንደነበር የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ ሪፖርት አመልክቶአል፡፡
ይህ ሁለገብ ሕንጻ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ካሉ ሕንጻዎች በስፋትና በግንባታ ጥራት ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚመደብ በመሆኑ  ለደብሩ ተጨማሪ ሀብት ከመሆኑም በተጨማሪ የደብሩን ታሪክና ታላቅነት በማስጠበቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ይገመታል፡፡
ለሕንጻው ግንባታ 3450689.27 እንደፈጀ የተነገረለት ዘመናዊ ሁለገብ አዳራሽና ቤተ መዘክር በተለያዩ በጎ አድራጊዎች የገንዘብ ድጋፍ ለፍጻሜ መድረሱን ከደብሩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በተጨማሪም በዚሁ ዕለት አዲስ ለሚገነባው ካቴድራል ብፁዕ አቡነ ሰላማ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ለምረቃ የበቃውን ሁለገብ ዘመናዊ አዳራሽና ቤተ መዘክር አስመልክተው በአስተላለፉት መልእክት ይህ የዛሬው የምረቃ በዓል ሁላችንንም እጅግ አድርጎ አስደስቶናል፡፡የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በሀለተኛው ሀገረ ስብከታቸው በከንባታ ሀድያና ጉራጌ ቅዳሴ ቤት የሚከበርለት በዓል ስላለባቸው ብፁዕ አቡነ ሰላማን የምሥራቅ ሀረርጌ ሊቀ ጳጳስ ወክለውልን ሄደዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በመንፈስ ከመካከላችን አሉ በማለት ሰፋ ያለ ማብራርያ ከሰጡ በኋላ ብፁዕ አቡነ ሰላማ የምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጰጳስ በበኩላቸው ይህ በዓል ታላቅ በዓል ነው የተሠሩት ሥራዎች በእግዚአብሔር እርዳታ ነው ምክንያቱም እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ቤተ ሠሪ በከንቱ ይደክማል ተብሎ በመጽሐፍ እንደተነገረው እግዚአብሔር በሥራው ባያግዘን ኑሮ ሥራው ለዚህ ደረጃ ባልበቃም ነበር፡፡ ቦታውም ቢሆን አስቀድሞ ለእግዚአብሔር ቤት የተመረጠ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በአባታችን በቅዱስ ያዕቆብ ታሪክ ላይ እንደምንገነዘበው ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ደንጊያ ተንተርሶ በተኛበት ወቅት ሌሊት በህልሙ የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ ባየበት ጊዜ ጧት ሲነሳ በቦታው ላይ ዘይት አፍስሶ ሀውልት አቁሞ እንደሄደ እንረዳለን፡፡
ይህንም ሥራ ቢሆን ከዚህ ለይተን ልናየው አንችልም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ከዚህ የበለጠ ሥራ ለመሥራት ይፍቀድልን በማለት ብፁዕነታቸው መርሐ ግብሩን በጸሎት አጠናቅቀዋል፡፡

በሌላ ዜና ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት፣የጉራጌ ሐድያና ከንባታ አህጉረ ስብከት፣የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስና እና ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም በቡታጅራ ደብረ ምሕረት ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የህንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ቅዳሴ ቤት ያከበሩ መሆኑን በቦታው የተገኙት ሊቀ ትጉኃን ታጋይ ታደለ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአዲስ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሰው ኃይል ኃላፊ አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ የቅዳሴ ቤቱ በአል በበርካታ ምዕመናን በከፍተኛ ድምቀት የተከበረው የቡታጅራ ደብረ ምሕረት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል የግንባታ ሥራው በኩረ ምዕመናን ከበደ ተካልኝ በተባሉ የእምነቱ ተቆርቋሪና በጎ አድራጊ ምዕመን ሙሉ በሙሉ በግል የገንዘብ ወጪ የተገነባ ሲሆን የዚሁ ታሪካ ባለቤት የሆኑት ክቡር በኩረ ምዕመናን ከበደ ከቅርብ ዓመት ወዲህ በተከሠተባቸው የጤና መታወክ አቅማቸው የደከመ ቢሆንም ካላቸው የቤተክርስቲያን ፍቅር የተነሳ  የቅዳሴ ቤቱን በዓል ማክበራቸውንና ለተገነባው ካቴድራልም አጠቃላይ ከብር ሃያ ስምንት ሚሊየን ያላነሰ የገንዘብ ወጪ ማድረጋቸውን ገልፀውልናል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ቀሌምንጦስ ሰፋ ያለ ትምህርትና ቃለ ቡራኬ በመስጠት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖአል፡፡

 

{flike}{plusone}