“የምናመልከው አምላክ ከሚነደው እሳት ሊያድነን ይችላል!! ”

                                                           በመምህር ሣህሉ አድማሱ

1

ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት ከ605-562 በከለዳውያን ላይ ነግሦ የነበረውና ናቡከደነፆር በመባል የሚጠራው የባቢሎን ንጉሥ ከፍታው 60 ክንድ ወርዱ 6 ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል (ጣኦት) በማሠራት በባቢሎን አውራጃ በዱራ ሜዳ ላይ አቁሞ የሀገሩን መኳንንት፣ ሹማምንት፣ አገረ ገዢዎች ሁሉ ለወርቁ ምስል (ጣኦት) እንዲሰግዱና ለምስሉ (ለጣኦቱ) በዓል አከባበር እንዲሰበሰቡ አዘዘ፡፡ (ዳን. 3÷1-4) ናቡከደነፆር ያቆመው የወርቅ ምስል (ጣኦት) ከእንጨትና ከቀለጡ መአድናት የተሠራ የማምለኪያ ምስል ነው፡፡
ይህ ጣኦት በአሕዛብ አምላክ ተብሎ ይጠራ እንጂ ጣኦቱ ራሱ ሕወት የለውም፣ ኃይልም የለውም፣ (መዝ. 114÷12) (1ቆሮ. 8÷4) የናቡከደነጾር ጣኦት በቆመበት በዱር ሜዳ ላይ አዋጅ ታወጀ፡፡
አዋጁም “ሕዝቦች ሆይ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ሰዎች ሁሉ እንድታደርጉ የታዘዛችሁት ይህ ነው የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት እንዲሁም የዘፈን ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ መስገድ አለባችሁ፤ ተደፍቶ የማይሰግድ ማንም ሰው ቢኖር ወዲያውኑ በሚነደው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል፡፡”
በአዋጁ መሠረት ከላይ የተጠቀሱት የአዋጅ መሣሪያዎች ሲሰሙ ሕዝቡ ሁሉ፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል (ጣኦት) ተደፍተው ሰገዱ፡፡
በዚህ ጊዜ ሲድራቅ ሚሳቅ፣ አብደናጐ የተባሉ ሦስት አይሁዳውያን ወጣቶች ለወርቁ ምስል አንሰግድም ብለው እምቢ አሉ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን በከበበበት ወቅት በምርኮ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸው ሲሆን ወጣቶቹ የተማረኩበት ዋና ዓላማ ማንኛውንም ትምህርት ተምረውና ዕውቀት ሞልቶባቸው በቋንቋ አስተርጓሚነትና በሥነ ጽሑፍ ዝግጅት ሥራ ተመድበው እንዲሠሩ ነው፡፡ ወጣቶቹን ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብደናጐ ተብለው የተጠሩት ከምርኮ በኋላ ሲሆን፣ ስያሜውም የባርነት ስያሜና የናቡከደነፆር አማልክት (ጣኦታት) መጠሪያ ስም እንደነበረ ይታወቃል፡፡ የወጣቶቹ አይሁዳዊ ስማቸው ግን አናንያ፣ አዛርያ፣ ሚሳኤል ይባላል፡፡
በዲራ ሜዳ ላይ ለቆመው ምስል (ጣኦት) አላሰግድም ያሉት ሰዎች እነዚሁ ሦስት አይሁዳውያን ወጣቶች ናቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሥ ናቡከደነፆር በታላቅ ቁጣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅን፣ አብደናጐን አስጠራቸውና ላቆምኩት ምስል (ጣኦት) ለምን አትሰግዱም? ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም ላንተ ምስል (ጣኦት) አንሰግድም ብለው መልስ ሰጡት፡፡ ንጉሡም ወደሚነደው የእቶን እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄ ሊአድናችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው? አላቸው፡፡ ሲድረቅ፣ ሚሳቅ፣ አብደናጐ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱለት ንጉሥ ሆይ በሚነደው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል የምናመልከው አምላክ ሊአድነን ይችላል፡፡ ባያድነንም እንኳ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል (ጣኦት) እንደማንሰግድ እወቅ አሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ እጅግ በመቆጣት ከሠራዊቱ ብርቱ የሆኑትን ወታደሮች ሦስቱን አይሁዳውያን ወጣቶች ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ እንዲጥሉአቸው አዘዘ፡፡ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብደናጐ የተባሉት ወጣቶች መጐናጸፊያቸውን፣ ሱሪአቸውን፣ የራስ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደለበሱ ታስረው በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ፡፡ የእቶኑ እሳት ወላፈን ወታደሮቹን ገደላቸው፡፡ ሦስቱ ወጣቶች ግን አራት ሆነው በእሳቱ ውስጥ ሲመላለሱ ታዩ፤ አራተኛውም የልዑል አምላክ አገልጋዮች ኑ ውጡ አላቸው፤ የንጉሡ ተከታዮች እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጐዳው፣ ከራሳቸውም ጠጉር አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች አዩ፡፡ ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፣
መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ የሲድራቅ፣ የሚሳቅ፣ የአብደናጐ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ስለዚህ እንደዚህ የሚአድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅ፣ በሚሳቅ፣ በአብደናጐ አምላክ ላይ ማናቸውንም ቃል የሚናገሩ ሕዝቦችም ሆኑ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ይቆረጣሉ፣ ቤቶቻቸውም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ ብዬ አዝዣአለሁ በማለት አዋጅ አውጆ ሲድራቅን፣ ሚሳቅን፣ አብደናጐን በባቢሎን አውራጃ ላይ ሾማቸው፡፡
ንጉሥ ናቡከደነፆር “መንግሥቱ ዘለዓለም ወምኩናኑኒ ለትውልደ ትውልድ” (ዳን. 4÷3) በማለት የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊነት መሠከረ፡፡ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብደናጐ በሚንበለበለው የእቶን እሳት በተጣሉ ጊዜ የሚያመልኩት እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እንዳዳናቸው በትንቢተ ዳንኤል (3÷28) ላይ በግልፅ ተጽፏል፡፡ ወጣቶቹን ከሚነደው የእቶን እሳት ያወጣቸው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል እንደሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፣ ታስተምራለችም፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተብሎ ሰሙ ባይጠቀስም፡፡ ከሦስቱ ወጣቶች ጋር በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ አራተኛ ሆኖ ሲመላለስ የታየው የአማልክት ልጅ ይመሰላል ተብሎ ተገልጿል (ዳን. 3÷25) ገብርኤል ብሂል ብእሲ ወአምላክ በመባል የሚታወቀው መልአክ ደግሞ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ የተባለውን የምስጢረ ሥጋዊንና የምሥጢረ መለኮትን ነገር ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም አብሥሯልና፡፡ ገብርኤል ማለት የእግዚአብሔር ሰው ማለት ነው፡፡ በሰው ምሳሌ ለሰዎች የተገለጠ የእግዚአብሔር መልአክ ነው፡፡ ለዳንኤል የእግዚአብሔርን ቃል ለመተርጐምና የሚመጣውን (መጻእያቱን) ለመግለጥ ተላከ (ዳን. 8÷15) ለዘካርያስ ስለዮሐንስ፣ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ስለ ክርስቶስ ልደት የምሥራችን ቃል አቀረበ (ሉቃ. 1÷11-38) ከዚህ ጥልቅ ከሆነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ የምንማረው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚመጣ ፈተና ሁሉ ከባድ መስሎ ቢታይም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እግዚአብሔር ሊያስወግደው ይችላል፡፡
በተለይ የእግዚአብሔርን አምላክነት የሚፈታተን የጣኦት አምልኮ ፈተናን መቋቋም ይኖርብናል፡፡ እስራኤላውያን ጣኦትን ሠርተው አመለኩ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ተቆጣቸው፡፡ (ዘፀ. 32÷1) ጣኦት ማምለክ አእምሮን ያሳውራል (ኢሳ. 44÷18) ከአጋንንት ጋር አንድ ያደርጋል፡፡ (1ቆሮ. 10÷20) ስለዚህ እስራኤል ጣኦትን እንዲአቃጥሉ ታዘዙ (ዘዳ. 7÷25) ምእመናንም ከጣኦት እንዲርቁ ታዘዋል፡፡ (1ቆሮ. 10÷14)

{flike}{plusone}