የሚድያ አገልግሎትን እናጠናክር!!

በዘመኑ የአነጋገር ዘይቤ ሚድያ እየተባለ የሚጠራው የመረጃ ልውውጥ አገልግሎት በዓለማችን ዙሪያ የንግዱም፣ የማኅበራዊውም፣   የፖለቲካውም፣ የመንፈሳዊ ዓለሙም የሚጠቀምበትና የሚገለገልበት ቢሆንም እንኳን የዚህ ቴክኖሎጂ የመጀመሪያዋ መሥራች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች የታሪክ መዛግብት ይስማማሉ፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ ሚድያ በሁለት ዐበይት ነጥቦች ሊመደብ ይችላል፡፡ አንደኛው በሥነ ጽሑፍ የሚገለጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በስዕልና በድምፅ የሚገለጥ ነው፡፡

ሥነ ጽሑፍ

ሥነ ጽሑፍ በተለያዩ ምሁራን የሚቀነባበር ታላቅ የአእምሮ ሥራ ሲሆን በዘመነ ነገሥት በቤተ መንግሥቱ አካባቢ የሥነ ጽሑፍ ጦማርያን እና አማካሪዎች ይኖሩ ነበር (1ዜና 27፥32) እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የሥነ ጽሑፍ ጦማርያን ጥሩ ልብስ ለብሰው የቀለም ቀንድ በወጋባቸው ይይዙ ነበር (ሕዝ.9፥2) ከምርኮ በኋላም እንደ ዕዝራ ያሉት የሕግም ምሁራን እና ፈጣን ጦማርያን ሆኑ፡፡ (ዕዝ.7፥6) በዘመኑ አንድ ጸሐፊ (ጦማሪ) ሦስት አይነት ሥራ እንዲሠራ ይደረጋል፡፡

1) የሙሴን ሕግ በትክክል መተርጎም

2) ለሰዎች ሕግን ማስተማር

3) የዳኝነት ሥራውንም ማከናወን ነው፡፡

በሐዲስ ኪዳን መግቢያ የነበሩት ጸሐፍት ሕጉ እንዳይጣስ በማሰብ የሽማግሌ ወግ የተባለውን ልምድ በሕዝቡ ጫንቃ ላይ ጫኑት (ማቴ.15፥2) ይሁን እንጂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለግብዝነታቸው ብዙ ጊዜ ወቀሳቸው (ማቴ.23) ምክንያቱም ለመልካም እና ሰውን ለማነፅ የሚረዳውን የሥነ ጽሑፍ ሙያ ለግል ጥቅማቸው እና ለራሳቸው ዝንባሌ ለማዋል ጥረት ያደርጉ ስለነበር ነው፡፡

ሆኖም ግን የሥነ ጽሑፍ አገልግሎት በየዘመኑ በሚፈጠሩ የሥነ ጽሑፍ ምሁራን አማካኝነት እየተጠናከረ ሊመጣ ችሏል፡፡የሥነ ጽሑፍ አገልግሎት ውጤቶች ናቸው፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያም በመጽሔቶች በጋዜጦች እና በበራሪ ጽሑፎች ለምዕመናን ስታበረክት የቆየችው አገልግሎት እንዲህ በቀላሉ የሚገለፅ አይሆንም፡፡ በቃለዓዋዲ ሬድዎም ስብከተ ወንጌልን ስታስፋፋ እንደነበር የረጅም ጊዜ ትዝታ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በተለይም በአሁኑ ዘመን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን እና በቅዱስ ሲኖዶሳችን አርቆ አሳቢነት የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን አገልግሎት ሥርጭት ቤተ ክርስቲያኗ ተጠቃሚ ለመሆን ችላለች፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ አንጋፋው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን በመሥራት እና ጣሪያ የነካ የፐርሰንት ዕድገት በማስመዝገብ ተወዳዳሪ የሌለው ሆኗል፡፡ ከዚህም ጎን ቀደም ሲል በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ተቋቁሞ በመጠኑም ቢሆን አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የሕትመትና ሥርጭት ክፍል በያዝነው ዓመት በሰለጠነ የሰው ኃይል ተጠናክሮ የቀጠለ በመሆኑ ሀገረ ስብከቱ እያስመዘገበ ላለው የልማት እና የመልካም አስተዳደር የላቀ ውጤት የበኩሉን ተጨማሪ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በታቀደው የጊዜ ሰሌዳ በመሠረትም በቋሚ አምዶች በተደገፈ የሥነ ጽሑፍ አገልግሎቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ለዚህም የሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ ባለድርሻ አካላት ሁሉ ድጋፍና እገዛ ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ፡-ኆኅተ ጥበብ ዘኦርቶዶክስ ጥር 2010ዓ.ም ታትሞ ከወጣው መጽሔት ርዕሰ አንቀፅ ላይ የተወሰደ