የሚዘራና የሚያጭድ አብረው ደስ ይላቸዋል
ጠቢቡ ሰሎሞን “ለሁሉም ጊዜ አለው” ብሎ እንደተናገረው የዘርና የመከር ወቅቶች የተለያዩ ናቸው፡፡ በግብርና ሥራ ተመድበው የሚሠሩ ገበሬዎች በዘመነ ክረምት ይዘራሉ፡፡ በዘመነ መፀው ደግሞ በክረምት የዘሩትን ሰብል ያጭዳሉ፣ ይሰበስባሉ፣ ይከምራሉ፣ ይወቃሉ፡፡ ገለባውን ከፍሬው ለይተው በጎተራ ያከማቻሉ በዚህም ሥራቸው ራሳቸውን ችለው በልተው፣ ጠግበው ለሌላውም ይተርፋሉ፡፡
የመዝሪያ የማጨጃና የመሰብሰቢያ ጊዜያት የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የሠራተኞችም የዕለት ኑሮ የተለያየ ሁኔታ አለው፡፡ በዘመነ ክረምት እየተቸገሩ እየተራቡ ያርሳሉ፣ ይዘራሉ፣ በዘመነ መፀው ደግሞ እንደልባቸው እየበሉ እየጠጡ ይሠራሉ፡፡ ይህንንም ነቢዩ ዳዊት ሲገልጽ “በለቅሶ የሚዘሩ በደስታ ያጭዳሉ፣ ይሰበስባሉ፣ ወደ እርሻቸው በሄዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ” ብሏል፡፡ (መዝ. 125፡5-6)
በዚህ አንጻር ሊቃውንት አባቶቻችን ነቢያትን በክረምት ገበሬ ሐዋርያትን በበጋ ገበሬ መስለው ተናግረዋል፡፡ ምሳሌውንም ሲያብራሩ የክረምት ገበሬዎች ጧት ከቤታቸው ሲወጡ ምሳ አያገኙም ሞፈር ቀንበር፣ ዘርና የበሬ ዕቃዎችን በትከሻቸው ላይ አነባብረው ተሸክመው በሮቻቸውን እየነዱ ወደ እርሻቸው ይሄዳሉ፡፡ ከዚያም ከላይ ዝናቡ ከታች ጭቃው ወዠቦውና ነፋሱ ሲያንገላታቸውና ሲያዋክባቸው ይውላሉ፡፡ ማታ ወደ ቤታቸው በተመለሱም ጊዜ የረባ ምግብ አያገኙም፡፡ ጎመን ጨምቀው በልተው ያድራሉ፡፡ ክረምቱ አልፎ እህል የሚያልቅበት የወደፊት አዝመራ የማይደርስበት የቅጠል ጊዜ ነውና በቂ ምግብ ለማግኘት ያስቸግራል፡፡
የበጋ ገበሬዎች ግን ማለዳ ከቤታቸው ሲወጡ ምሳቸውን በሚገባ በልተው ይወጣሉ ቀን በሥራ በሚውሉበትም ቦታ እሸቱንና እንኩቶውን እየተመገቡ ሲሠሩ ይውላሉ፡፡ ማታ ወደ ቤታቸውም ሲመለሱ እንጀራው በሌማት ጠላው በማቶት ተዘጋጅቶ ይቆያቸዋል፡፡ ያንን እየበሉና እየጠጡ ይደሰታሉ፡፡
በክረምት ገበሬዎች የተመሰሉት ነቢያት ትንቢት በሚናገሩበትና በሚያስተምሩበት ጊዜ ከብሌት ሳይታደሱ በመንፈስ ቅዱስ ሳይጎለምሱ ልጅነትን ሳያገኙ ስለሆነ መከራው ጸንቶባቸዋል፡፡ በበጋ ገበሬዎች የተመሰሉት ሐዋርያት ግን በሚያስተምሩበት ጊዜ ከብሌት ታድሰው በአእምሮ ጎልምሰው በልጅነት ከብረው ስለሆነ የሚደርስባቸውን መከራ ሁሉ ከምንም አይቆጥሩትም ነበር፡፡ እንዲያውም በአደባባይ አቁመው ወቅሰው ገርፈው ስለክርስቶስ እንዳያስተምሩ አስጠንቅቀው ሲያሰናብቷቸው ደስ እያላቸው ይሄዱ ነበር፡፡ (የሐዋ. ሥ. 5÷40-41)
ነቢያት ስለክርስቶስ ሰው መሆንና ከድንግል ማርያም በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና መወለድ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ሰው ሆኖ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት መምረጡን ዓለሙንም በጠቅላላ ከፍዳና ከመርገም ማዳኑን ተናግረዋል፡፡ ምሳሌን መስለዋል ሱባዔንም ቆጥረዋል፡፡ ከተናገሯቸውም ትንቢቶች ጥቂቶችን ቀጥሎ እንመልከት፡፡
ከዓበይት ነቢያት ኢሳይያስ “እነሆ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፡፡ እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” /ትን. ኢሳ 7፡14/
“ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ፤ መካር፤ ኃያል አምላክ የዘለዓለም አባት፤ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡” (ትን. ኢሳ 9÷6) በተጨማሪም ይኸው ነቢይ “ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዓርግ ጽጌ አምጒንዱ” ከእሴይ ግንድ በትር ትወጣለች ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል፡፡” (ትን. ኢሳ. 11፡1) ሲል ነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሌሎችም ነቢያት ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን ብዙ ምሳሌ መስለዋል ብዙ ሱባዔም ቆጥረዋል፡፡ ብዙ ትንቢትም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ዓረፍተ ዘመን ስለጋረዳቸው ከዘመኑ ሳይደርሱ ሲያልፉ ሐዋርያት ከዘመኑ ደርሰው ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተምረዋል፡፡ ከእርሱም ጋር አብረው በልተዋል፤ ጠጥተዋል በዓይናቸውም ተመልክተዋል፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን መርጦ በሚያስተምርበት ጊዜ “እነሆ እላችኋለሁ ዐይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ-ደረሰ እርሻውን ተመልከቱ የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፡፡ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘለዓለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባሉ፡፡ አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውን ሆኗልና፡፡ እኔም እናንተ ያልደከማችሁትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ ብሏል፡፡” /የዮሐ. ወን. 4÷35-38/ እንዲሁም /በሉቃ ወን. 10÷23/ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው፡፡ እላችኋለሁና እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩም እናንተ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወድደው አልሰሙም፡፡” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል፡፡
“አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው” እንደሚባለው ከልደተ ክርስቶስ በፊት የተነሡት አባቶች ነቢያት የተናገሩት ቃለ ትንቢት በጊዜው የነበሩትን ሐዋርያት ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ ቀጥለው የተነሡትን የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ አስደስቷቸዋል፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት የሚነሱትና የተነሱት ትውልዶች የሚያስተምሩትናየሚማሩት ስለክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ መወለድና ስለዓለም ድኅነት የተነገሩትን ትንቢቶች፤ የተመሰሉትን ምሳሌዎች፤ የተቆጠሩትን ሱባዔዎች መሠረት በማድረግ ነው፡፡
ነቢያት ትንቢት የተናገሩባቸው ጊዜያት ወይም ዓመታት የተለያዩ ቢሆኑም ትንቢታቸው የሚታወስበት ጊዜ ግን ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ በመባል ይታወቃል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከድንግል ማርያምም ተወለደ” (ገላ. 4÷4) ብሎ እንደገለጸው የትንቢቱ ቀጠሮ በደረሰ ጊዜ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶልናል፡፡
ገበሬ የጣረበት፤ የጋረበት ለብዙ ጊዜ የደከመበት የእርሻ ሰብል ደርሶለት ፍሬውን በተመገበ ጊዜ እንደሚደሰት ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ያስተማሩለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሐዋርያት በአካለ ሥጋ ተገኝተው ወረደ ተወለደ ብለው አስተምረው ደስ ሲላቸው ይወርዳል ይወለዳል ብለው ያስተማሩ ነቢያትም በአካለ ነፍስ ደስ ተሰኝተዋል፡፡ የሚዘራና የሚያጭድ አብረው ደስ ይላቸዋል የተባለውም ስለዚህ ነው፡፡ የሐዋርያትን አሠረ ፍኖት ተከትለን የምንማርና የምናስተምር ሁላችንም በዚህ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አዘጋጅ፡- ላእከ ወንጌል በእደማርያም ይትባረክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ትምህርት ሥርጭት ኃላፊ