የመ/ፓ/ጠ/ ቤተ ክህነት የደመራ በዓል በሰላም እንዲከበር ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ተወካዮች ጋር ለግማሽ ቀን የቆየ ውይይት አካሄደ
በ2009 ዓ.ም የሚከበረውን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም እንዲከበር ለማድረግ በማሰብ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዓርብ መስከረም 13 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከ1000 ከማያንስሱ ከሁሉም ገዳማትና አድባራት ከመጡ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለግማሽ ቀን የቆየ ምክክርና የውይይት መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
በውይይቱ መርሐ ግብር የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም የመስቀል ደመራ በዓል ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው በዓልነው፡፡ የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ በተዘጋጀው መርሐ ግብር መሠረት ሰዓቱን በማክበር የበዓሉ አከባበር በተያዘለት ሰዓት ሊጠናቀቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ባስተላለፉት ትምህርት አዘል አባታዊ መልእክት “ አንሰ ኢይዜሀር በርእስየ ዘእንበለ በመስቀሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ” በሚል የመጽሐፍ ቃል ተነስተው በዓሉ እኛ የምናከብረው ሳይሆን በዓሉ እኛን ያከብረናል፡፡ የመስቀል በዓል ነፃነት የታወጀበት በዓል ነው ከሌላው ዓለም ጭምር በዓሉን ለማክበር በርካታ ዕንግዶች ይመጣሉ እነዚህ እንግዶች አለባበሳችንን ፣አነጋገራችንንና አረማመዳችንን ቀድተው ወደሀገራቸው ይዘው ሂደው መረጃውን ለሌሎች እስከ መስጠት ይደርሳሉ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እኔ የምመካው በራሴ ሳይሆን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ነው እኔ ብሮጥ አመልጣለሁ፣ ብይዝ አጠብቃለሁ፣ብመታ አደቃለሁ ብየ አልመካም ብሏል፡፡
ሰላም የምናመጣው እኛው ነን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የታደለ እንጨት ነው ያልታደለ እንጨት ከሰል ይሆናል ፣የታደለ እንጨት ከበሮና መቋሚያ ይሆናል፣ያልታደለ እንጨት ሰዎች ይደባደቡበተል፡፡ ታቦት ጽዮን ከምርኮ የመጣችበት ዕፀ ድንባዝ የተባለ የእንጨት ዝርያ ነው፡፡ መስቀሉ የቤተ ክርስቲያን መሠረትና ጉልላት ነው መስቀሉን የምናከብረው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለተሰቀለበት ነው “ ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ሰብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ “ የተባሉት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማረያምና ማስቀለ ክርስቶስ ናቸው” እመቤታችን ጌታን በማህፀንዋ እንደተሸከመችው መስቀሉም ጌታን ተሸክሟል፡፡
ስለዚህ መስቀሉ ሰላም የተመሰረተበትና ሰላም የታወጀበት ስለሆነ የመስቀሉ በዓልም የሰላም በዓል ነው፡፡ የሀገራችን ሰላም የፀና እንዲሆን ተግተን ማስተማር አለብን የሰላም ፍሬ ጣፋጭ ነው ፡፡
ነጋዴው ነግዶ እንዲአተርፍ፣ ገበሬው ዘርቶ እንዲአመርት፣ ካህናትም እንዲዘምሩ ስለሰላም መጸለይና ማስተማር ይገባል በማለት ሰፋ ያለ አባታዊና ትምህርት አዘል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የዘነበ ወርቅ አካባቢ ፓሊስ መምሪያ በክፍለ ከተማው ከሚገኙ ገዳማትና አድባራት ተወካዮች ጋር በዘንድሮው የ2009 ዓ.ም የመስቀል በዓል አከባበር ዙሪያ መስከረም 12 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለግማሽ ቀን የቆየ የጋራ ምክክርና ውይይት መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
በውይይት መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የክፍለ ከተማው ገዳማትና አድባራት ተወካዮች ቁጥር ከአንድ መቶ የማያንሱ ሲሆን በውይይቱ መርሐ ግብር መክፈቻ ወቅት ንግግር ያደረጉት የክፍለ ከተማው ቤተክህነት ጽ/ቤት የሰው ኃይል ክፍል ኃላፊ መምህር ኃይሉ ጉተታ እንደገለፁት በክፍለ ከተማው በሚገኙት የደመራ በዓል ማክበሪያ ቦታዎች ሁሉ የሚካሄደው መርሐ ግብር ሕጻናትና አረጋውያን በጊዜ እንዲመለሱ እና የፀረ ሰላም ኃይሎች በድንገት ለሚፈጥሩት ችግር ማህበርሰቡ እንዳይጋለጥ ለማድረግ የተዘጋጀው መርሐ ግብር መሠረት በዓሉ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት መወጣት ይገባዋል፡፡ ደመራውም በወቅቱ መለኮስ አለበት፡፡
ቤተክርስቲያን የሰላም ምንጭ እንደመሆንዋ መጠን በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ በሁሉም ገዳማትና አድባራት አስፈላጊው ትምህርት ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ በዓሉ በዩኒስኮ ዓለም አቀፍ የቅርስ መዝገብ/ የተመዘገበ በመሆኑ ከተለያዩ ዓለማት ጭምር በርካታ ጐብኚዎች ስለሚመጡ እና በዓሉም የራሳችን ስለሆነ በሰላም እንደከበር ጥረት ልናደርግ ይገባናል በጠቅላይ በተክህነት በኩል ከተዘጋጁት ጽሑፎች በስተቀር በየአካባቢው ምንም ዓይነት በራሪ ጽሑፍ ሆነ ለሕዝብ እንዳይበተኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ በቀረበው እጀንዳ መሠረት የገዳማቱና አድባራቱ ተወካዮች በሰጡት ሐሳብ በየአንድ አንዱ ገዳምና ደብር የሚመደቡ ካህናት፣ዲያቆናት እና የሰንበት ት/ቤት ወጣች የገዳሙ ወይም በደብሩ በኩል በአገልግሎት የሚታወቁ አገልጋዮች ስለሆኑ የሰላም መዝሙር ከመዘመር ውጭ ምንም ዓይነት የፀረ ሰላም ችግር እንደማይፈጥሩ እናምናለን ብለዋል፡፡
የዘነበወርቅ አካባቢ ፖሊስ መምሪያ ተወካይ ኢንስፔክተር በሪሁን ጋዲሳ ባስተላለፉት መልእክት የሰላሙን ውጠት የምናውቀው የምናየው ከበዓሉ በኋላ ነው በሁሉም ገዳማትና አድባራት የፀጥታ ኃይሎች ይመደባሉ፡፡
በተጨማሪ ደግሞ ቅዳሜና እሁድ በየገዳማቱና በየአድባራቱ የሰላሙ መልእክት ሊተላለፍ ይገባዋል ወጣቱ እንዲያአከናውን ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል የበዓሉን ሰላማዊ ውጤት ለማረጋገጥ ሲባል የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል እና የአካባቢ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ በጥምር ይሠራሉ ብለዋል፡፡