የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ሰላሳ ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባ ተጀመረ

2007

በየዓመቱ ጥቅምት ወር ላይ ሲካሄድ የቆየው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈዊ ጉባኤ በዘንድሮውም ዓመት ከጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም እስከ ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ በመንበረ ፓትርያርክ የሰብከተወንጌል አዳራሽ ይካሄዳል፡፡
ጉባኤው በተከፈተበት ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት የመክፈቻ መልእክት ዓመቱ የሥራ ዓመት እንዲሆንልን፣ ስብከተወንጌል እንዲሰፋፋ፣ በመቀነስ ላይ የሚገኘው የምዕመናን ቁጥር እንዲጨምር ተግቶ መሥራት እንደሚገባ፤ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሀብት የቤተ ክርስቲያን ባልሆኑ ወገኖች እንዳይያዝ፣ በዘመናችን እየተስፋፋ የሚታየው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲቆም፣ በአፍሪካ ሀገሮች የሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ  የሚገኘው የኢቦላ ቫይረስ ወደ ሀገራችን እንዳይገባ ተግቶ መጸለይ እንደሚገባ፣ በአሁኑ ጊዜ ቤተክርስቲያናችን በቅኝ ግዛት ውስጥ በመሆንዋ ሁላችንም ተረባርበን ነፃ ማውጣት እንደሚገባን፣ ቤተክርስቲያን አንዲት ስትሆን አሁን ግን በእኛ ስም ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ሆነው ስለ ሚገኙ የአንዲት ቤተክርስቲያን መሪ ብቻ መሆን እንደሚገባ፣ በገንዘብ ምክንያት ቤተክርስቲያንን የሚፈታተነው ማህበር ሥርአት መያዝ እንዳለበት፣ ቀደም ሲል ማለትም በ2006 ዓ.ም የተወሰነው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አንዲከበር፣ ይህ ጉባኤ መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል  በማለት  ለጉባኤው ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከቅዱስ ፓትርያርኩ መግለጫ በመቀጠል ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ በተክርስቲያን ላለፉት ሰላሳ ሶስት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ በሃይማኖታዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚአዊ ጉዳዮች ዙሪያ የከናወነቻቸው ዓበይት ተግባራትና ያስመዘገባቻቸው ተጨባጭ ውጤቶች በዚህ ምልአተ ጉባኤ እየቀረቡ ተገቢው ውይይት ከተደረገባቸውና የጋራ መግባባት ላይ ከደረሱ በኋለ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በግብአትነት በመቅረብ ለውሳኔ የሚበቁበት ሁኔታ በመፈጠሩ ቤተክርስቲያናችን በሁለንተናዊ መልኩ ላስመዘገበችውና ለምታስመዘግበው ውጤት የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤያችን ወደር የማይገኝለት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ እውን ነው በሚል የመግቢያ መግለጫ በመነሳት የጠቅላይ ቤተ ክህነትን፣ የአህጉረስብከቶችን እና የድርጅቶችን የስብከተ ወንጌል እና የልማት እንቅስቃሴ ጠቅለል ባለ አገላለፅ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ከብፁዕነታቸው ሪፖርት በኋላ እያንድአንዳቸው አህጉረ ስብከቶች በበጀት ዓመቱ ያከናወኑአቸውን ዝርዝር የሥራ ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

{flike}{plusone}