የመንበረ ጸባዖት ቅዱስ በዓለ ወልድ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እድሳት ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኘው የመንበረ ጸባዖት ቅዱስ በዓለ ወልድ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ከዕድሜ ብዛት የተነሣ የሕንጻው መዋቅሮች በመናጋት ደረጃ ላይ የደረሱ በመሆናቸው የካቴድራሉ የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ባደረገው ያላሰለሰ ክትትል በአሥራ አንድ ወራት ውስጥ በተደረገ የጥገና እና የዕድሳት ሥራ 2,990,460.32 ብር ወጪ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ታድሶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም ተባርኮ ሐምሌ 29 ቀን 2009 ዓ.ም በቅዱስነታቸው በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፡፡
የመንበረ ጸባዖት ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን በ1883 ዓ.ም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የተመሠረተ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑ የ127 ዓመት ዕድሜ ባለቤት መሆኑን ከቀረባ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን በባረኩበት ወቅት ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት “ቤተ ክርስቲያን ሆይ ኃይልን ልበሺ” በሚል የመጽሐፍ ቃል ንግግራቸውን ጀምረው ይህን የመሰለ ልማት ስላየን ደስ ብሎናል፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን የረጅም ጊዜ አገልግሎት የሰጠ በመሆኑና ችግሩ የገባችሁ ባለሐብቶችና ምዕመናን ታድሶ በማየታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በማያያዝም ቅዱስነታቸው በሰጡት ትምህርታዊ መልእክት ከመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ግቢ እስከ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለው መንገድ ስፋትና ጥራት ባለው መልኩ የተሠራ በመሆኑ ደስ ብሎናል፤ ገንዘብ አላፊና ጠፊ ነው፤ ታሪክ ግን ለዘለዓለም ይኖራል በማለት አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ተዘጋጅቶ የቀረበውን ሙሉ ሪፖርት ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው እናቀርባለን
የመካነ ሥላሴ (ቅዱስ በዓለ ወልድ) ቤተ ክርስቲያን የዕድሳት ሥራን አስመልክቶ ከካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ አስተዳደር ጽ/ቤት የቀረበ አጭር የሥራ ክንውን ሪፖርት፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክብርት ዶ/ር ኂሩት ወ/ማርያም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር ፣ ክቡር መ/ር ጎይቶም ያይኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ክቡር አቶ ዮናስ ደስታ የቅርስ ጥበቃና ምዘና ባለሥልጣን ዳይሬክተር ፣ ክቡር አቶ ገ/ጻድቅ ሐጎስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የተከበራችሁ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የተከበራችሁ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ክቡራንና ክቡራት በዚህ ምርቃት በዓል ላይ የተገኛችሁ ምዕመናንና ምዕመናት!!!
በቅድሚያ የመካነ ሥላሴ (ቅዱስ በዓለወልድ) ቤተ ክርስቲያን ዕድሳት ሥራ ተጠናቆ ለዚህ ታላቅ ክብረ በዓል ላይ እንድንገኝ ላደረገ ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይድረሰው እያልኩ የዕድሳት ሥራውን በተመለከተ በካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት ስም አጠር ያለ ሪፖርት እንዳቀርብ እንዲፈቀድልኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በዚህ ታላቅ ክብረ በዓል የተገኛችሁ ክቡራን እንግዶች ምዕመናንና ምዕመናት!!
ወደ ዋናው የሥራ ሂደት ዝርዝር ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ከቤተ ክርስቲያኑ ቀደምት ታሪክ በመነሣት ታሪካዊ ምሥረታውን አስመልክቶ አጠር ባለ ሁኔታ አስታውሰን ለማለፍ እንሞክራለን፡፡
የቅዱስ በዓለወልድ /መካነ ሥላሴ/ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተው በ1883 ዓ.ም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ አማካይነት ሲሆን ለምሥረታው የተነሳሱበትም ዋናው ምክንያት አንድ ባሕታዊ መነኩሴ “ከቤተ መንግሥትዎ በስተቀኝ ባለው ከፍታ ቦታ ላይ ሦስት ነጫጭ ርግቦች መጥተው ሲያርፉ በራዕይ አይቻለሁና (መካነ ሥላሴ) የሚል ጽሕፈት ያለበት ጽላት አስፈልገው በማምጣት እንዲተክሉ እግዚአብሔር አዟልና እንዲተከል ይሁን፡፡” ስለተባሉ በዚሁ መነሻነት መካነ ሥላሴ የሚል ጽሕፈት ያለበት ጽላት ሲያስፈልጉ ቆይተው ከአዲስ ዓለም በላይ ፉየታ ከሚባለው ቦታ እንዳለ በጥቆማ ስለደረሱበት ለቦታው ሌላ ጽላት ተፈልጎለት በንጉሡ ትእዛዝ በአለቃ ወልደ ያሬድ ኤላሪዮን አስመጭነት በወቅቱ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት በነበሩት በግብፃዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ እጅ ከተረከቡ በኋላ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ንጉሠ ሸዋ በተባሉ በ25ኛው ዓመት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው በነገሡ በአንደኛው ዓመት ታህሣሥ 22 ቀን 1883 ዓ/ም የአዛዥ ዘአማኑኤል እልፍኝ ተባርኮ በዚሁ ቅዱስ ሥፍራ በመቃኞ /በመቃረቢያ/ ቆይቶ ይህ አሁን ለዕድሳት የበቃው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለ12 ዓመታት በግንባታ ላይ ከቆየ በኋላ በ1895 ዓ/ም በመጠናቀቁ መስከረም 7 ቀን 1895 ዓ/ም ታቦተ ሕጉ ከነበረበት መቃረቢያ ወጥቶ በዓለ ንግሥ ተደርጎለት አዲስ ወደ ታነፀው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቅዳሴ ቤቱ በዛሬው ዕለት ተከብሯል፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ዐቢይ ጉዳይ ደግሞ ቀደም ሲል ጽላቱ ከግራኝ መሐመድ ወረራ በፊት ወረኢሉ ደሴ የነበረ ሲሆን በግራኝ ወረራ ምክንያት ካህናቱ አሽሽተው ወግዳ ወስደው አኑረው ለብዙ ዘመናት ከቆየ በኋላ የራስ ጎበና ባለቤት ወ/ሮ አየለች ከወሎ ወግዳ አስመጥተው አዲስ ዓለም በላይ ፉየታ ከተባለው ቦታ ላይ አስተክለው እንደነበርና ታሪኩ እንደሚያስረዳው በአፄ ምኒልክ ትዕዛዝ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በዚሁ ቦታ ላይ የተተከለ ሲሆን መካነ ሥላሴ የሚለው የደብሩ ስያሜም የተሰጠው ከጽላቱ ላይ ከተገኘው ጽሕፈት በመነሳት እንደሆነ ከታሪኩ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከታሪክም ሆነ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች መረዳት እንደተቻለው ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት ከክርስትና ሕይወታቸው በመነሳት ቀዳሚ ተግባራቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥራትና ማሠራት እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ጎላ አድርገው ያሳያሉ ለአብነት ያህል ለመጥቀስም አብርሃ ወአጽብሃ የተባሉት ወንድማማቾች ነገሥታት ቤተ ክርስቲያን
ከማሳነጽም አልፈው ወንጌልን በኢትዮጵያ ዞረው እየሰበኩ ክርስትናን ያስፋፉ እንደነበረ ከታሪክ የምንረዳው ሕያው ምስክር ነው፡፡
ከዚያም እነ ንጉሥ ላሊበላ ፣ ይምርሃነ ክርስቶስ ፣ ነአኩቶ ለአብና ሌሎቹም ነገሥታት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ አፄ ምኒልክና አፄ ኃይለ ሥላሴ ከከዋክብቱ ነገሥታት መካከል ጎልተው የሚታዩ ናቸው እነዚህ ነገሥታት ራሳቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥራት ብቻ ሳይሆን መኳንንቱና መሣፍንቱ ሕዝበ ክርስቲያኑም ጭምር ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ ያረጀውን እንዲያድሱ፣ የተጎዳውን እንዲጠግኑና አቅማቸው በፈቀደው መጠን ለቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ አዋጅ እስከ ማስነገር ደርሰው እንደነበር ሲወሳ እንደነበር በታሪክ ይነገርላቸዋል፡፡ አፄ ምኒልክ በዚሁ ጉዳይ ለአብነት ያህል ተጠቃሽ ናቸው ከዚህም ሌላ ርስተ ጉልት በመስጠትና በመትከል የመተዳደሪያ ሥሪት ሠርተውላት ቤተ ክርስቲያን ያለምንም ችግር ትተዳደር እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ቤተ ክርስቲያን በአማኞቿ አስተዋጽዖ ብቻ እንድትተዳደር የተደረገ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቤተ ክርስቲያኗ በልማት ራሷን እንድትችል በማሰብ በቅዱስ ሲኖዶስና ቅዱሳን ፓትርያርኮች አመራር ሰጪነት አንዲሁም በመንግሥት ድጋፍ ሰጪነት በልማት ሥራ እየተንቀሳቀሰች የምትገኝ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከላይ እንደተጠቀሰው ቀደም ሲል የነበሩት ነገሥታት የሀገር መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የቤተ ክርስቲያንም መሪዎች እና ጠባቂዎች ጭምር እንደነበሩ የሚታወቅ ሐቅ ነው፡፡
ወደ ቦታው ታሪክ እና ወደ ስያሜውም ስንመለስ ነገሥታቱ ቤተ ክርስቲያን ሲያንፁ ወይም ሲተክሉ በቅድሚያ የሚተክሉት ወይም የሚያንፁት በሥላሴ ስም እንደነበር የታሪክ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
ስለሆነም አፄ ምኒልክ መካነ ሥላሴን የተከሉት ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥታቸውን ከእንጦጦ ወደ መሐል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ካዛወሩ በኋለ አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ያሠሩትን ቀራንዮ መድኃኔ ዓለምን ጨምሮ አምስት አብያተ ክርስቲያናትን እንደሠሩ የሚታወቅ ሲሆን ይህ በአሁኑ ሰዓት 127ኛ ዓመቱን እያከበረ ያለው የዕድሜ ባለጸጋና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ታሪካዊ ቅርስ የሆነው መካነ ሥላሴ (አሁን ቅዱስ በዓለወልድ) ቤተ ክርስቲያን በአሠራረሩ ቅደም ተከተል በ6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡
መካነ ሥላሴ የሚለው ስያሜ ወደ በዓለ ወልድ የተለወጠበት ምክንያትም ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ይህን ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለውን ካቴድራል ከሠሩ በኋላ መንበረ ጸባዖት ቅ/ሥላሴ ካቴድራል የሚለውን ሥያሜ በማግኘቱና በአንድ ቦታና አስተዳደር ሥር አንድ ዓይነት ስያሜ ሊኖር እንደማይገባ ስለታመነበት የተሰየመለት ይመስላል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ሆይ
ይህ የትላንቱ ሲሆን ዛሬም ይኸው ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ከዘመን ብዛትና ከረጅም ጊዜ አገልግሎት የተነሳ የጣሪያው ክዳን ቆርቆሮ በማፍሰሱ ጽላቱንና ቅዱሳት መጻሕፍቱን እንዲሁም በመቅደሱ ውጫዊ የግድግዳ ዙሪያ የሚገኙትን ቅዱሳት ሥዕላትና ሌሎችንም ንዋየ ቅዱሳት ከማበላሸቱም አልፎ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ሊያፈርሰው የሚችል መሆኑን የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ አስተዳደር ጽ/ቤት ስለተገነዘበ እግዚአብሔር በነብዩ ሐጌ አድሮ እንደተናገረው “በውኑ ይህ ቤት ፈርሦ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን?”ሐጌ ፩÷፬ ያለውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ከቅዱስነትዎ አባታዊ መመሪያ በመቀበል፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤቱን በማስፈቀድ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ከካቴድራሉ ዕድሳትና ልማት ኮሚቴ ጋር በመተባበር የሰንበቴ ማኅበራትንና በጎ አድራጊ ክርስቲያኖችን በማስተባበርና እርዳታ በመጠየቅ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና ከቅርስ ጥበቃና ምዘና ባለሥልጣን ባገኘው ፈቃድ መሠረት ቅርሱ ይዘቱን ሳይለቅ ተገቢውን ሁለንተናዊ ጥገናና ዕድሳት ተደርጎለት የተጠናቀቀ በመሆኑ እነሆ ቅዳሴ ቤቱን በዚሁ ዕለት በከፍተኛ ድምቀትና ስነ-ሥርዓት በማክበር ላይ እንገኛለን፡፡
በማያያዝም ዝርዝር የዕድሳት ሂደቱን ለመግለጽ ጠቅለል አድርገን ከዚህ በሚከተለው ሁኔታ እናቀርባለን፡፡
ሀ.የጣሪያውን ዕድሳት በተመለከተ፣
በተመሳሳይና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ የመሐል ወራጆቹ ሙሉ በሙሉ ከነክፈፉ በአዲስ ሲቀየር ማገሩም በአዲስ ሞራሌ ተተክቷል፣ የቆርቆሮ ክዳኑም በባለ 28 ጌጅ ቆርቆሮ ተቀይሯል የቆርቆሮው ብዛትም በቁጥር 552 ሲሆን ሥራውም እጅግ በታወቁና በቤተ ክርስቲያን ሥራ ላይ የብዙ ዓመታት ልምድ ባላቸው አቶ ደምሰው ደገፉ በተባሉ ጠንቃቃ ባለሞያ ተሠርቶ ለዚህ ምርቃት በቅቷል የጣሪያው ጉልላትም ባማረና በተዋበ ሁኔታ እንዲሠራ የተደረገ ሲሆን በጉልላቱና በክፈፉ ዙሪያ የሚገኘው መርገፍም በልዩ ግርማ ሞገስ በአዲስ መልክ ተሠርቶ ተጠናቋል፣ በውጫዊው የጣሪያ ክፍል ማለትም በደረጃው ዙሪያ የሚገኘው የጣሪያ ክፍል ዙሪያው የመስቀል ቅርፅ ባለው ጣውላ ኮርኒስ ተሠርቷል፣ በተዛነቡ ዙሪያ የሚገኘው ክፍልም ቅርስነቱን ሳይለቅ በስስ ጌጠኛ አልሙኒየም መሰል ላሜራ ልምድ ባለው ባለሙያ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡
ለ.ወለሉን በተመለከተ፡፡
ሦስቱም የቤተ ክርስቲያን ክፍሎች ማለትም ቤተ መቅደሱ፣ ቅድስቱና ቅኔ ማኅሌቱ በውስጡ ያለው አፈር ተቆፍሮ ወጥቶ በኮንክሪት ሊሾ የተደረገ ሲሆን እንዲሁም ቅድስቱና ቅኔ ማኅሌቱ በፐርኬ ጣውላ እጅግ በተዋበ መልኩ ተነጥፏል በተጨማሪም ከፐርኬው በላይ ደረጃውን የጠበቀ ምንጣፍ አንዲለብስ በበጎ አድራጊ ተገዝቶ ተዘጋጅቶለታል፡፡
ሐ.የቀለም ሥራን በተመለከተ፡፡
በሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ በውስጥም ሆነ በውጭ የተሣሉት ሥዕሎችና ሐረጎች ቅርፃቸውም ሆነ ሐረጋቸው ባለበት ሁኔታ በጥንቃቄ አስፈላጊው እድሳት የተደረገላቸው ሲሆን እንዲሁም የውጭና የውስጥ ሙሉው የግድግዳ ቀለም የመቀባት ሥራ ተከናውኗል፡፡
መ.የቤተ ክርስቲያኑ ውስጣዊና ውጫዊ ክፍል /ተዛነቡን/ የመብራት ሥራን በሚመለከት
የቤተ ክርስቲያኑ ውስጣዊ ክፍል መብራት ቢኖረውም ደረጃውን ያልጠበቀ በመሆኑ ይህም በጣም በተዋበና ባማረ መልኩ ዙሪያውን በአዲስ መስመር በተንጠልጣይ አምፖሎች ተቀይሯል፡፡ ውጫዊ ክፍሉም (ተዛነቡ) ቀደም ሲል መብራት ያልነበረው ሲሆን በጣሪያው ማለትም አዲስ ኮርኒስ በተሠራው ዙሪያ አዲስ የኤሌክትሪክ የመስመር ዝርጋታ /ኢንስታሌሸን/ ፣ ማቀፊያዎችና አምፖሎቹም ጭምር በአዲስ ተተክቷል፡፡
ሠ.መንበረ ምሥዋዑን (አዲስ የተሠራው መንበርን) በተመለከተ፡፡
በአዲስና በተሻሻለ ይዘት ምሥጢራዊ ትርጉሙን በጠበቀ መልኩ ማለትም ፀወርተ መንበር ኪሩቤል /ዐርባዕቱ እንስሳ/ ፣ 24ቱ ካሕናተ ሰማይ ሱራፌል ምስልና፣ ጌታ በምሴተ ሐሙስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን ራት ያደረገበትንና ሥርዓተ ቁርባንን የመሠረተበትን እንዲሁም ሌሎች ምሥጢራቸውን የጠበቁ ቅርፃዊ ሥዕሎች የተሣሉበት እጅግ የተዋበ ልዩ መንበር ከእንጨት ተቀርፆ ለአገልግሎት እንዲውል ተደርጓል፡፡
ረ. በበዓለ ወልድ ዙሪያ የሚገኙ መካነ መቃብራትንና በቅፅረ ግቢው ዙሪያ የተሠሩ መጠለያዎችን በተመለከተ፡፡
ቀደም ሲል በበዓለ ወልድ ቅፅረ ግቢ የሚገኙት የመካነ መቃብር ቦታዎች የቤተ ክርስቲያኑን ቅፅረ ግቢ በማጣበባቸው ምክንያት ለአገልግሎት የሚመጣው ምዕመን የማስቀደሻም ሆነ የጸሎት ቦታ ባለማግኘቱ ሐውልቶቹን ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህንኑ ጉዳይ በማስመልከት ለቀብሩ ባለቤቶች በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በማስነገርና በተያያዥም ለማየት አመቺ በሆኑ ቦታዎች ላይ ዝርዝራቸውን የያዘ ማስታወቂያ የተለጠፈ በመሆኑ ቤተሰቦች ከመገናኛ ብዙኃን በመስማት እና የተለጠፈውን ማስታወቂያ በማየት ወደ ካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት በመምጣታቸው የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት የውይይት መድረክ በመፍጠር 99% (ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ) ከሚሆኑ ቤተሰቦች ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ያሉት መካነ መቃብራት አጽማቸው ሳይነሳ
ባለበት ሆኖ በተለያየ ቅርፅ የተሠሩት ሐውልቶችና ዙሪያቸውን የታጠረው አጥር ብቻ እንዲነሳ ተደርጎ ዛሬ ዙሪያውን አምሮና ተውቦ የሚታየው መጠለያ “በአንድ ወንጭፍ ሁለት ወፍ” እንዲሉ ሕያዋኑ ለሙታኑ እንዲጸልዩ ሆኖ መጠለያው ለሁለት አገልግሎት እንዲውል ሆኖ ተሠርቷል፡፡
ሰ. ካቴድራሉንና የቅዱስ በዓለወልድ ቤተ ክርስቲያንን በአስፋልት ለማገናኘትና ውበቱን የጠበቀ ግቢ ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ተግባር በሚመለከት፡፡
ቀደም ሲል የካቴድራሉና የመካነ ሥላሴ (ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን) ቅፅረ ግቢ ቦታው በመካነ መቃብር ተይዞ ካቴድራሉና ቅዱስ በዓለወልድ ቤተ ክርስቲያን ግቢው ተለያይቶ የነበረ ሲሆን በተለይም የመካነ መቃብር ሥፍራው እጅግ ከመጣበቡም በላይ ጽዳቱ ያልተጠበቀና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኑ እንደ ታሪካዊነቱና ቅርስነቱ አንፃር ሲታይ እንኳንስ በቱሪስት ሊጎበኝ ቀርቶ ምዕመናኑ በወርኃዊና ዓመታዊ ክብረ በዓል ወደዚህ ቦታ ለመምጣት እጅግ በጣም እየተቸገሩ እንደሚገኙ ለሁላችንም ግልጽ ቢሆንም ሕዝበ ክርስቲያኑን ለመቀስቀስና ለማንቃት እነዲሁም የግቢውን ውበትና ጽዳት ለማስጠበቅ ያህል በመቃብር የተጨናነቁ ሥፍራዎችን በማንሳት የካቴድራሉንና የቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያንን ለማገናኘት ጥረት ተደርጓል፡፡
ቅጽረ ግቢውን ለማስዋብና ለማጽዳት እንዲሁም ለማገናኘት በተደረገው ጥረት ቅዱስ በዓለ ወልድ የመረጣቸው ባለሀብት ለአምስት ተከታታይ ቀናት ግሬደር በማስመጣት የቁፋሮና የማስተካከል ሥራ ያሠሩልን ሲሆን በተለይም እንይ ኮንስትራክሽን የተባለው ድርጅት ሙሉውን የአስፋልት ሥራ ለማከናወን በገባልን ቃል መሠረት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ ከቁፋሮና አፈር ከማንሳት ሥራ ጀምሮ አሁን አምሮ የሚታየውን የሰብ ቤዝ ሥራ አከናውነው ለቀጣይ አስፋልት ሥራ ምቹ አድርገውት ይገኛሉ፡፡
ሸ. ከላይ ለበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ዕድሳት፣ የመጠለያ ሥራ ከካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት ወጪ የተደረገና ከበጎ አድራጊ ምዕመናንን የተሰጠ ገንዘብ ከዚህ በመቀጠል አቀርባለሁ፡፡
1.ከተለያዩ ግለሰቦች በሞዴል 30 ገቢ የሆነ ብር—–300,175.00
2.ከአቶ ኃ/ሚካኤል ወ/ገብርኤል ብር————–305,000.00 የፐርኬ ሥራ
3.ከታላቁ ሰንበቴ ማኅበር ብር ————— —-447,300.00 የጣሪያ መዋቅር ሥራ
4.ከአቶ ድረስ አስፋው ብር ———————-26,350.00 የመንበርና ኮርኒስ ሥራ
5.ከአቶ አያሌው ወ/ትንሳኤ ———————-70,000.00 የቆርቆሮ ግዥ
6.ከአቶ ሰሎሞን እንግዳ ————————-106,000.00 ምንጣፍ ግዥ
7.ከወ/ሮ በላይነሽ አድማሱ ———————-130,000.00 ቆርቆሮ፣ሲሚንቶና አሸዋ
8.ከወ/ሮ ፋንታዬ አድማሱ ———————-75,000.00
9.ከአቶ ብርሃኑ ኃ/ማርያም —————– —-28,000.00
10.ከወ/ሮ ወይንሸት በጅጋ —————– —-43,335.00
11.ከእህተ ገብረኤል —————————-38,000.00
12.ከወ/ሮ ደብረወርቅ ብር —————– —-62,000.00 ለመጠለያ ሥራ
13.ከአቶ ጳውሎስ ባራኪ ብር ——————–33,000.00 ለመጠለያ ሥራ
14.ከምሥራቀ ጸሐይ ሰንበቴ ማኅበር ————15,200.00 ቆርቆሮ ግዥ
15.ከተለያዩ ግለሰቦች ————————–362,694.00
16.ከካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት ————–748,394.32
ጠቅላላ ድምር ————2,990,460.32 መሆኑን እየገለጽኩ ቅዱስነትዎ ለዚህ ሥራ አስተዋጽዖ ያደረጉልንን በጎ አድራጊዎች እንዲባርኩልን በቅዱስ በዓለ ወልድ ስም እጠይቃለሁ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ክቡራን እንግዶች፣ ምዕመናንና ምዕመናት !!
ይህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደምትነት ያለውና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ካቴድራል እንደመሆኑ መጠን ማንኛውም ታላላቅ ሃይማኖታዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ስነ-ሥርዓቶች
የሚናወኑበት ከመሆኑም በላይ ሁለት ታላላቅ ቅዱሳን የሃይማኖት አባቶችና፣ ሁለት ታዋቂ የሀገር መሪዎች፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የንጉሣውያን ቤተሰቦች፣ ሚንስትሮች አርበኞች፣ የሌሎችም ታዋቂና የሀገር ባለውለታዎች አፅም ያረፈበትና የሚገኝበት ታላቅ ቦታ ስለሆነ መንግሥትን ጨምሮ ከቅዱስ ሲኖዶስ አንስቶ እስከ ሕዝበ ክርስቲያኑ ድረስ ያሉ አካላት ለካቴድራሉ ችግር ትልቅ ትኩረት ሊሰጡበት ይገባል ስንል እግረመንገዱን መልእክታችንን ለማስተላለፍ እንፈልጋለን፡፡
ትኩረት ሊሰጥባቸው ከሚገባቸው ችግሮች መካከልም
1ኛ. በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረው ይዞታ በካርታ ላይ እንደሚያሳየው 142,000.00 (አንድ መቶ አርባ ሁለት ሺህ ካሬ ሜትር) በደርግ ዘመነ መንግሥት የተወረሰውን ጨምሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የካቴድራሉ ይዞታ በግለሰቦችና በድርጅቶች ተይዞ ስለሚገኝ የኢፌዲሪ መንግሥት በ1987 ዓ.ም ባወጣው መመሪያ በካርታ ቁጥር 5634 ተመዝግቦ የሚገኘው ከላይ የተጠቀሰው የካቴድራሉ ነባር ይዞታ እንዲከበርላቸው ተብሎ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የሰርኩላር ደብዳቤ የተላለፈልን ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ነባር ይዞታችን እንዲከበርልን ለጠቅላይ ሚኔስቴር ጽ/ቤትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አቤቱታ በማቅረብ ላይ የምንገኝ ቢሆንም እስከአሁን ድረስ ጥያቄያችን መልስ ሳያገኝ በእንጥልጥል ላይ የሚገኝ መሆኑ፣
2ኛ. ከ50 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረውና ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶችንና በተለይም ቅዱስነትዎንና ሌሎች ምሁራንን በማፍራት የሚታወቀው የካቴድራሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት በአዲስ መልክ ዘመናዊ የመማሪያ ሕንፃ ለመገንባት ያስችለን ዘንድ በግቢው ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸው በከተማው አስተዳደር መመሪያ ቢተላለፍም እስከ አሁን ድረስ አፈጻጸሙ መዘግየቱ ለካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ክቡራንና ክቡራት!!
በአጠቃላይ በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ የመካነ ሥላሴ (ቅዱስ በዓለወልድ) ቤተ ክርስቲያን እና ካቴድራሉ በመጠኑም ቢሆን ግቢው መገናኘቱ ለካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤቱም ሆነ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚያስደስት ጅምር የልማት ተግባር መሆኑን ለመግለጽ ያህል እንጂ በቀጣይም የካቴድራሉ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንም እድሳት፣ በካቴድራሉ ቅፅረ ግቢ ያለውን የምዕመናን መገልገያ ሥፍራ ደረጃውን የጠበቀና ሳቢ በሆነ የላንድ እስኬፕ ለማስዋብና ለማስጌጥ በተጨማሪም በበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያንን ዙሪያ የሚገኘውን የመካነ መቃብር ሥፍራ መልሶ ለማልማትና ውበቱን የጠበቀ የመካነ መቃብር ሥፍራ ለማዘጋጀት የካድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት ቅድመ ሁኔታውን እያጠናቀቀ ስለሆነ በዚህ በቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን እድሳት ላይ እንደተረባረባችሁ ሁሉ በቀጣይም በካቴድራሉ እድሳት እና በሌሎቹም ተያያዥ ሥራዎች ላይ በማቴሪያልም ሆነ በገንዘብ እርዳታ እንድታደርጉልን መልካም ትብብራችሁ እንዳይለየን በአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ስም እየጠየኩ ሪፖርቴን በዚህ ላይ አጠናቅቄአለሁ፡፡
የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰኝ፡፡