የመስቀል አደባባይ ባለቤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሆኗ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ….ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ
ዛሬ ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም 9:00 ሐዋርያ ዘለዓለም የተባለ የወንጌላውያን አማኞች ኅብረት አባል የሆነ ፓስተር መስቀል አደባባይ ላይ ለጠራው የአምልኮ ፕሮግራም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በጽህፈት ቤታቸው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ብፁዕነታቸው የፓስተሩ የመስቀል አደባባይ ፕሮግራም እንዲሰረዝ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ገልፀው ማሰረዝ ግን አልተቻለም ብለዋል።
እንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች ሲኖሩ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት በኩል ተፈቅዶ መሆን ሲገባው ነገር ግን በአንድ ግለሰብ ጥሪ ከሃይማኖት ተቋማት ዕውቅና ውጭ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ጥሪ መተላለፉ አሳዝኖኛል ብለዋል።
ሐዋርያ ዘለዓለም የተባለን ሰው የወንጌላውያን ኅብረትም እንደማያቀው አጣርተው ለዚህ ፕሮግራም መንግሥት ዕውቅና መስጠት የለበትም በሚል ከፍተኛ ጥረት እንዳረጉ አውሰተዋል።
ሆኖም ግን መርሐ ግብሩ ቀድሞ የተያዘና ዓላማውም በጦርነቱ ለተጎዱ ድጋፍ ማሰባሰቢያ የሚል ሽፋን ይዞ በመንቀሳቀሱ ጥረታቸውን ክቡድ እንዳደረገው ተናግረዋል።
ክብርት ከንቲባዋ ጋር በአጭር ቀን ውስጥ ለመነጋገር ቀጠሮ እንዳላቸው የገለፁት ብፁዕነታቸው በስመ ሃይማኖት እኩልነት ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው ድርሻዋን ማጣት የለባትም ብለዋል።
የመስቀል አደባባይ ባለቤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለመሆኗ ዓለም የመሰከረው በዩኔስኮ የተመዘገበው ከማይዳሰስ ቅርሷ በተጨማሪ ከጥንት ጀምሮ የደመራ በዓልን ማክበሯ እና ለስሙ ያላት አበርክቶዋ ምስክር ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል ለባለብዙ አገልግሎት የታደሰው መስቀል አደባባይ ሲታደስ ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ጋር የገባነው ውል አድሰው ለቤተክርስቲያን ሊያስረክቡ የነበረ መሆኑን አውሰተው ደብዳቤው በእጃችን ያለ በመሆኑ ይሄው ውል እንዲከበር ለመንግሥት ጥሪ አቅርበዋል።
በመስቀል አደባባይ እንደ የሕዝብ ስፖርት፣ ኮንሰርት እና ሌሎች ኩነቶች ፈቃጁ ሌላ መሆኑን ገልፀው ሃይማኖታዊ ከንዋኔ ሲሆን ግን የሚመለከታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ብቻ ናት ብለዋል።
ቤተክርስቲያን ለልማት እና ለአብሮነት ያላት አስተዋጽኦ በጽኑዕ አቋም ከቃላት በላይ በተግባር የተገለፀ ነው ያሉት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በ2011 ዓ.ም የአዲስ ከተማ አስተዳደር ቤተሰብ ለሌላቸው ተማሪዎች ለምገባ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ በጠየቀን ጊዜ ያለ ሃይማኖት ልዩነት ለሁሉም ተማሪዎች ምግብ የሚሆን 10.000.000 (አስር ሚሊዮን ብር) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መለገሱን የቤተክርስቲያኒቱን ለሁሉ አዛኝ መሆኗንም አስታውሰዋል።
በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese