‹‹የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው›› /1ኛቆሮ. 1÷18/

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ታላላቅ ብሔራውያን በዓላት መካከል አንዱ የመስቀል በዓል ነው፡፡

በተለይ ይህ በዓል በዩኒስኮ መመዝገቡ የቤተ ክርስቲያናችንን ታላቅነትና ጥንታዊነት ከመግለጹ ባሻገር በሀገር የልማት ዕድገት ላይ የሚያበረክተው ጥቅም ዘርፈ ብዙ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡

መስቀል ስንል ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሲል የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ እናስታውሳለን፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከተሰቀለ በኋላ የተለያየ ደዌ ያለባቸው ሕሙማን መስቀሉን እየዳሰሱ በመስቀሉ እየታሹ ይፈወሱ ነበር፡፡ በዚህ በመስቀሉ በሚደረገው ተአምራት እየተሳቡ ብዙዎች ክርስቲያን ሆኑ፡፡ ይህንን ያዩ አይሁድ መስቀሉን ቀበሩት ለሦስት መቶ ዓመታት ተቀብሮ ቆየ፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በ327 ዓ.ም የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ይህን ታሪክ ትሰማ ነበርና መስቀሉን አስቆፍራ ለማስወጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ እዚያም ደርሳ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን አላገኘችውም፡፡ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅላት አላገኘችም፡፡ በመጨረሻ ግን የመስቀሉ መውጣት የእግዚአብሔር ፈቃዱ ነበርና አንድ ኪራኮስ የሚባል ሽማግሌ የዕሌኒን መቸገር አይቶ እንደሚከተለው ይመክራታል፡፡ እንጨት አሰብስበሽ ደመራ አስደምረሽ ዕጣን ጨምሪበት የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሸ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኝዋለሽ አላት፡፡ እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አሳያት ይህንንም አስመልክቶ መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ በዜማ ድርሰቱ ‹‹ዘዕጣን አንጸረ ሰገደ ጢስ›› (የዕጣኑ ጢስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ አሳየ) ሲል ተናግሯል፡፡ በዚህ መሠረት ከመስከረም 17 ቀን ጀምሮ ስታስቆፍር ቆይታ መጋቢት 10 ቀን መስቀሉ ከተቀበረበት ቦታ ወጥቷል፡፡

መስቀልን የምናከብርበት ምክንያት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ዓለምን ስላዳነበትና በክቡር ደሙ ያከበረው በመሆኑ ነው፡፡

መስቀል በብሉይ ኪዳን ብዙ ምሳሌ አለው የኖኅ መርከብ የተሠራችበት እንጨት፣ የሙሴ በትር የመስቀል ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶ መስቀል እንጂ በሌላ አልመካም››/ገላ 6÷14/ ሲል የተናገረው የመስቀሉን ክብርና ኃይል የሚገልጽ ነው፡፡

በአገራችን ክርስቲያኖች በግንባራቸውና በሌላውም አካላቸው በመስቀል ቅርጽ ይጠቆራሉ  ( ይነቀሳሉ ) እንዲሁም ልብሳቸው ላይ በጥልፍ የመስቀል ቅርጽ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ክርስቲያኖች ለመስቀሉ ልባዊ ፍቅር ያላቸው መሆኑን ነው፡፡

መስቀል በሕይወተ ሥጋ ሳለን ብቻ ሳይሆን ከሞትንም በኋላ ከእኛ አይለይም አጽማችን በሚያርፍበት በመቃብራችን ላይ ይደረጋል ይህም የትንሣኤያችን ምልክት ነው፡፡

“ዘወትር እንደምነግራችሁ ልዩ አካሄድ የሚሄዱ ብዙዎች አሉና አሁንም እነርሱ የክርስቶስ የመስቀሉ ጠላቶች እንደሆኑ በግልጥ እያለቀስሁ እነግራችኋለሁ፡፡ እነዚህም ፍጻሜያቸው ለጥፋት የሆነ፣ ሆዳቸውን የሚያመልኩ፣ ክብራቸውም ውርደት የሆነባቸው፣ ምድራዊዉንም የሚያስቡ ናቸው፡፡ እኛስ ሀገራችን በሰማይ ያለችው ናት ከዚያም እርሱን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፡፡”/ፊልጵ 3፡18-20/  ሲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ለመስቀሉ ትልቅ ፍቅር እንዲኖረን ነው፡፡

ለመስቀል መስገድ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አለ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ‹‹ወንሰግድ ውስተ መካን ጎበ ቆመ እግረ እግዚእነ›› (እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን) (መዝ. 131÷7) ሲል የተናገረው ለመስቀል መስገድ እንደሚገባ የሚገልጽ ነው፡፡ የሰላም ንጉሥ መድኃኔዓለም ክርስቶስ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ ሲሰቀል እግሮቹ ከመስቀሉ ጋር ተቸንክረዋል በዚህ መሠረት እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን ሲል ለመስቀሉ እንሰግዳለን ማለት ነው፡፡

በኦሪት ዘጸአት (14÷15-31) እንደተጻፈው በሙሴ በትር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተደርገዋል በሙሴ በትር ተአምራት ከተደረገ አምላካችን በተሰቀለበት መስቀል እንዴት ተአምራት አይደረግ? በዚህ መሠረት መስቀል በቤተ ክርስቲያናችን ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ክብር አለው፡፡ መስቀል የድልና የነጻነት ምልክት ነው፡፡

‹‹የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ በረከተ መስቀሉ የሚደርሳቸው ላመኑ ሰዎች እንጂ ላላመኑ አይደለም፡፡ ስለዚህ በረከተ መስቀሉ እንዲደርሰን ጽኑ እምነትን ገንዘብ እናድርግ፡፡

ጽኑ እምነትን ገንዘብ አድርገን ሕጉን ትእዛዙን ጠብቀን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በላእከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ትምህርት ሥርጭት ኃላፊ