የሕንጻ ግንባታው ከመሠረቱ እስከ ጉልላቱ በአርማታ ብቻ ተሠርቶ የተጠናቀቀው የአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ታሪካዊ አመሠራረት!!
በደቡብ የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም፣ በምዕራብ የእንጦጦ ርዕሰ አድባራት ቅ/ማርያም፣በሰሜን የገነተ ኢየሱስ ገነተ ማርያም፣ በምሥራቅ የአሜሪካ ኢንባሲ የሚአዋስኑት፣ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጡ ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ የሚታየው የአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በተለምዶ አጣራር ጭቁኑ ሚካኤል በተለያዩ የታሪክ ሰነዶች ተጽፎ እንደሚገኘው ክህነትን ከልዑልነት ጋር አጣምረው በመያዝ ይታወቁ በነበሩት በልዑል ራስ ከሣ ኃይሉ አማካኝነት በ1968 ዓ.ም ተመሠረተ ÷ ልዑሉ የቅዱስ ሚካኤልን ፅላት በግል ቤታቸው ይዘውት ይኖሩ ነበር ÷ ከዚያም በኋላ ጉባ ቤት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በግል ይዞታቸው ላይ መቃኞ አሠርተው ፣ ታቦቱን በዚያ አስቀምጠው ፣ በአንድ ካህን እየታጠነ ይኖር ነበር ÷ ካህኑ ልዑል ራስ ካሣ የግል ይዞታቸው የነበረውን ቦታ ለመልአኩ ለቅዱስ ሚካኤለ ቤተክርስቲያን ማሠሪያ ሆኖ ለምዕመናን አገልግሎት እንዲሰጥና ቦታው የቤተክርስቲያን ይዞታ ሆኖ እንዲቀጥል በቃለ ኑዛዜ አስተላለፉ ÷ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል ፅላቱ ጉባ ቤት በሚገኘው በልዑሉ የግል ቤት መቃኞ ተሠርቶለት ሲሰለስ፣ ሲወደስና ሲቀደስ የቆየ ሲሆን በ1995 ዓ.ም ህዳር 10 ቀን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ኘሬዝዳንት፣ በዓለም ሃይማኖቶች የሰላም የክብር ኘሬዝዳንት አሁን ለውጤት ለበቃው የካቴድራሉ ሕንጻ የመሠረት ደንጊያ ተጣለ ÷/ተቀመጠ/
ለሕንጻው የተነደፈው የመጀመሪያው ዲዛይን አመርቂ ሆኖ ባለመገኘቱ በወቅቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጥብቅ ክትትል መሠረት ጥራቱን የጠበቀ ሌላ ዲዛይን ተዘጋጀ ÷ ከመሠረቱ እስከ ጉልላቱ በአሸዋ፣ በጠጠርና በሲሚንቶ ብቻ ተገንብቶ ለፍጻሜ የበቃው የአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ለአሥራ ሁለት ዓመታት ያህል ሲገነባ ቆይቷል፡፡
በግንባታ ሥራው በአካባቢው ማኀበረ ምዕመናን፣ በአንድ አንድ በጐ አድራጊ ባለ ሀብቶች፣ከሀገር ውጪ የሚኖሩ የእምንቱ ተከታዮች የገንዘብ፣የሐሳብ፣ የማቴሪያል ድጋፍ በእነ ኢንጂነር ኃብተ ማርያም የሙያ ክትትል መሠረት ግንባታው ከ33,747,220.00 ባለነሰ ገንዘብ ወጪ ተገንብቶ ተጠናቀቀ ÷ ከመሠረቱ እስከ ጉልላቱ በአሸዋ፣ በጠጠርና በሲሚንቶ ተገንብቶ ለፍጻሜ የበቃው የአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ማካኤል ካቴራል መልአከ ሰላም ውበት ታመነ የተባሉት የዚሁ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ በግል የገንዘብ ወጪ የገዙትን የደንጊያ ወፍጮ ለቤተ ክርስቲያኑ በስጦታ በማበርከታቸው መሆኑን ከካቴድራሉ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል ÷ የደንጊያ ወፍጮው ሙሉ በሙሉ በባለ24፣ በባለ20፣ በባለ16 በኮንክሪት ለ12 ዓመታት ያህል ያለማቋረጥ አገልግሎት የሰጠ መሆኑን የመረጃ ምንጮቻችን አክለው አብራርተዋል ÷ የግንባታ ሥራው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ በመሆኑ ሐምሌ 5 ቀን 2007 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፖትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግሥት ተወካዮች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ በቅዱስነታቸው ተባርኮ የቅዳሴ ቤቱ በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ የሕንጻው ውበት፣ ዘመናዊነት፣ጥራትና ታሪካዊነት አቻ የሌለው በመሆኑ ካቴድራል እየተባለ እንዲጠራ በብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩ ተሰይሟል፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ውበት ታመነ በሥራ ወዳድነታቸውና በታማኝነታቸው የተመሠከረላቸው ካህን በመሆናቸው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፖትርያርክ መልካም ፈቃድ መሠረት የአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ ለስምንት ዓመታት ያህል ደብሩን በአስተዳዳሪነት ከመምራት ጐን የቤተ ክርስቲያኑን ይዞታ ለማስከበር ከሁለት ዓመታት ያላነሰ የፍርድ ቤት ክርክር ያደረጉ አባት መሆናቸው ከካቴድራሉ ያገኘናቸው መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
{flike}{plusone}