የሊጋባው በየነ ልጅ ባሠሩት በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በተገኙበት የተለያዩ የራስ አገዝ ልማት ሥራዎች ተመረቁ

የሊጋባው በየነ ልጅ ባሠሩት በአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በተገኙበት የተለያዩ የራስ አገዝ ልማት ሥራዎች ተመረቁ።
በመርሐ ግብሩ ላይ ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ መጋቤ አእላፍ ማሙየ ሸዋየ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ፣ መጋቤ ስብሐት ዐቢይ ዘለቀ የብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ልዩ ጸሐፊ፣ መልአከ ገነት ልሳነወርቅ ተስፋ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት የሥራ ሐላፊዎች፣ ሊቀ ጉባኤ አባ ኅሩይ የደብሩ አስተዳዳሪ ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የደብሩ ማኅበረ ካህናት ሰንበት ተማሪዎች እንዲሁም ምእመናንና ምእመናን ተገኝተዋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ለመንፈሳዊ አገልግሎቱን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩና ዘመኑን የዋጁ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
ከነዚህም መካከል በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ ቡራኬ የተመረቁት የG+1 ደብሩ ሙዚየምና መጠለያ፣ በG+1 ቤተ ልሔምና ከሥሩ መጠለያ ያለው ሕንጻ እንዲሁም ከሥር መጠለያ የሆነ G+1 የብፁዓን አባቶች ማረፊያ ማሳያዎች ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም ለደብሩ ዓለማዊ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ G+4 ሕንጻ ለመሥራት በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ አባታዊ መምሪያ በመልአከ ምሕረት አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር በደብሩ የተሠሩ ሥራዎችን ያጠቃለለ አጭር ሪፖርት አቅርበዋል ።
በመቀጠልም በሁሉን አቀፍ መንፈሳዊና የራስ አገዝ የልማት ሥራዎችን ላይ አርአያነታቸው የጎላ፣ ኃላፊነትን ለተገለጠ ሥራ ላረጋገጡና በበጎ ሥራ ለተሣተፉ አካላት ከደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ጉባኤ አባ ኅሩይ ጀምሮ የደብሩ ምክትል ሊቀ መንበር የደብሩ ስብከተ ወንጌል ኃላፊ መጋቤ ሐዲስ ምንያህል እንዲሁም ሌሎች የደብሩ አባቶች፣ አገልጋዮች ካህናትና በጎ አድራጊ ክርስቲያኖች የምስጋና ሽልማትና የመልካም ሥራ ዕውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ አባታዊ መልእከትና የሥራ መመሪያ አስተላልፍዋል።
በመልእክታቸውም የተሠሩ ሥራዎች ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዘመን የምትጠበቃቸው ፣ የተሠጠ ኃላፊነት በአግባቡ የመጠቀምና ለዋጋ የማድረግ እንዲሁም በምእመናኑ የመታዘዝና የኔባይነት መንፈስ የተሠሩ መሆናቸውን የሚያመለከት ነው ብለዋል።
አክለውም ቤተ ክርስቲያኑን ያሠሩት የሊጋባ በየነ ልጅ የደጃዝማች በቀለ በየነ ልጅ ክቡር አቶ አርአያ ሥላሴ በቀለን በአካል በማግኘታቸው ደስታቸው ገልጸው የአካባቢው ክርስቲያን ሕያው ታሪክን ሳይቆራረጥ ጠብቆ በመቆየቱም በእጅጉ የሚደንቅ ነው ብለዋል።
በመጨረሻም የትናንት አባቶቻችን ሥራ ማስቀጠል እንኳ ቢያቅተን መጠበቁን ልንበረታበት እንደሚገባ አሳስበው በዚህ ሁሉ መልካም የልማት ሥራ አርአያነት ባለው መልኩ ለመሩ ለሊቀ ጉባኤ አባ ኅሩይ ፣ለታዘዙ ምእመናን ፣ ለተባበሩ ሰበካ ጉባኤና ማኅበረ ካህናትና ለረዱ በጎ ክርስቲያኖች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በ፲፱፻፶፭ ዓ.ም ተመሠረተ ሲሆን በሊጋባው በየነ ወንድማገኝ ልጅ በደጃዝማች በቀለ በየነ የታነጸ ቤተ ክርስቲያን መሆኑ የደብሩ ታሪክ ያመለክታል።