የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል በመንበረ መንግሥት ግቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በድምቀት ተከብሮ ዋለ

የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል በመንበረ መንግሥት ግቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ ውላል።

በበዓሉ በሊቃውንት ‘ወረደ መልአክ ሊቀ መላእክት ኃበ ሠለስቱ ደቂቅ’ የሚል ያሬዳዊ ዝማሬ ሲቀርብ፣በገዳሙ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ‘ገብርኤል ምልአኒ መንፈሰ ልሳን፣ ለተናብቦ መንፈሰ ድርሳን፣ ሞጣኅተ ብርሃን፣ ዘይገለብቦ ሞጣኅተ ብርሃን’ የሚል ያሬዳዊ ዝማሬ ተዘምሯል።

በዕለቱ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ‘ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ ለእለ ይፈርሕዎ ወያድኅኖሙ’=የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል። (መዝ 33:7) በሚል መነሻነት ዕለቱን በተመለከተ ሰፉ ያለ ትምህርት አስተምራል።

ብፁዕነታቸው ለበዓሉ መነሻ የሆነው በዳንኤል ምዕ (1-3) ያለ ታሪክ በማውሳት ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል።

በታሪኩ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠለስቱ ደቂቅን እያባባለ ለማታለል ከዚያም አልፎ ለማስገደድ ቢሞክርም እነሱ ግን አምነን እንሞታለን እንጂ አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም በማለት ወደ እሳት ቢጣሉም እሳት ውስጥ ሆነው በጸሎት መጽናታቸው አውስተዋል፤ በተመሳሳይም ነቢይ ዮናስ በመከራ ውስጥ/ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ‘ወደ ቅዱስ መቅደስህ ደግሞ እመለከታለሁ’ በማለት ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር እንደጸለየ በማውሳት( ዮና2፡5) የሚያስገርም እምነት ነው ብለውታል።

ጠቅለል ባለ መልኩ በዓሉ፦

  1. የእግዚአብሔር ቸርነት፣ ምሕረትና ርህራሔ፤ 2. የመልአኩ ተራዳኢነት፣ ጠባቂነትና ፈጥኖ ደራሽነት፤ 3. የሠለስቱ ደቂቅ ፍጹም እምነት፣ በመከራ ጊዜ ሁሉን ታግሰው በእግዚአብሔር መታመናቸውንና የእግዚአብሔር ግብረ መልስ አይተን እኛ ከእነርሱ በመማር አምላካችን እንደነርሱ ለማምለክ የምንማርበት በዓል መሆኑን አስረድተዋል። የእምነት ሰው የእምነት ሥራ ብቻ ይሠራል ያሉት ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ እኛ የዘመኑ ሰዎች ከሠለስቱ ደቂቅ፦ አናንያ፣ አዛሪያ፣ ሚሳኤል እና ከነቢይ ዳንኤል የምንማረው ነገር፡ ፍጹም እምነት እንዲኖረንና በመከራ ጊዜም ቢሆን በእርሱ ተማምነን እስከ መጨረሻ መጽናት እንደሚያስፈልግ አስተምረዋል።

በመጨርሻም እርስ በእርሳችን ተስማምተንና ተዋድደን አንድነታችንን አጠናክረን እንደአባቶቻችን እምነታችንና ሃገራችን አስከብረን ልንኖር ያስፈልጋል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በበዓሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና አንደሰማይ ከዋክብት ደምቀውና አምረው የሚታዩ እጅግ በርካታ የተዋሕዶ ልጆች ምእመናንና ምእመናት ተገኝተዋል።

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!

  1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
  2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
  3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese

በመ/ር ኪደ ዜናዊ