የሁለት ቀን የአድባራትና ገዳማት ተወካዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በውጤት ተጠናቀቀ

0149

ከሰኔ 10 ቀን እስከ ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ፣ የሙስና አደጋና ሰብአዊ መብት፣ መልካም አስተዳደር እና ቤተክርስቲያን በተሰኙ አርዕስቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተላኩ 3 አባላት የባለሞያ ቡድን እና ሌሎች ምሁራን በተካተቱበት ስልጠናው ተካሂዷል፡፡
በሁለቱ ተከታታይ ቀናት ስልጠናውን የተሳተፉት የ160 አድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፍያንና ሒሳብ ሹሞች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የክፍል ኃላፊዎች፣ ሠራተኞች እና የየክፍላተ ከተማ ቤተክህነት ተወካዮች ሲሆኑ በሁሉም የዝግጅቱ አቀራቢዎች ገንቢ የሆነ እውቀት ማግኘታቸውን ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት አብራርተዋል፡፡
የስልጠናው ዋና አስተባባሪ የሆኑት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ዘመናዊትን በተላበሰ አገላለጽ በተሰጡት የትምህርት አርስቶች ጥልቅ የሆነ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተለይም ከሙዳየ ምጽዋት ጥገኝነት በመላቀቅ እና ወደ ልማት አቅጣጫ በመጓዝ ከሙስና አደጋ እራስን መከላከል እንደሚገባ ባብራሩበት ወቅት በአሁኑ ሰዓት አጠገባችን ያሉ ሰዎች የመጋፋት ተግባር እያከናወኑ የሚገኙ ከመሆናቸው ባሻገር እነዚህ ክፍሎች የቄስነት ማዕረግ ይዘው የመቀደስ ችሎታ የሌላቸው በመሆናቸውና እነዚህ ጽንፈኞች መበየጃ እየያዙ ቤተክርስቲያንን ለማሸግ እየፎከሩብን በመሆናቸው ነቅተንና ተግተን ቤተክርስቲያናችንን ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡
በስልጠናው ማጠናቀቂያ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የተገኙ ሲሆን በሁለቱ ተከታታይ የስልጠና ወቅት ከተሰጡት የትምህርት አይነቶች በተጨማሪ የሠራተኛ ደመወዝ በባንክ እንዲከፈል ስምምነት የተደረገ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ157,000 ብር የስልጠና ስፖንሰር ያደረገ መሆኑን ወደፊትም ንግድ ባንኩ ከቤተክርስቲያናችን ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ቃል መግባቱንና በተሰጠው ስልጠና በራስ የመተማመን ስሜት መፈጠሩን፤ ይህ ስልጠና ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንና ለስልጠናው አገልግሎት የሚሰጡ ማቴሪያሎችና የስልጠና ማዕከል መዘጋጀቱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ለቅዱስነታቸው ከገለጹ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አያይዘው ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት እግዚአብሔር እኛን ሲፈጥር ከተስማሚ አየር ጋር ነው፤ ምድሪቱን አሳምሮ ሰጥቶናል፤ ዘመናችን የተወሰነ ቢሆንም ምድሪቱን አልምተን ሕይወታችን የተመቻቸ እንዲሆን በርትተን መሥራት አለብን፡፡

0118

በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ህልውና ማወቅ አለብን፤ በተሰጠን እውቀትም እራሳችንን ልናስተዳድር ይገባናል፤ አእምሮአችንን ልናሰፋው ይገባናል፤ በየቀኑ ሥራን መሥራት አለብን ሀይማኖትን መጠበቅ አለብን፤ ምዕመናን የሚረኩበትን ሥራ መሥራት ግዴታችን ነው፤ ስልጠና የማናውቀውን ያሳውቀናል፡፡
“ምንት ብከ ዘኢነሳእከ እምካልእከ ወምንት ብከ ዘኢኮነ ውህበ ለከ” ከሌላው ያላገኘኸው የራስህ የሆነ ምን ነገር አለ እንደተባለው የራሳችን ብቻ የሆነ ነገር የለንም፤ እርስ በእርሳችን ልንወያይ ይገባናል፤ አእምሮአችን የጠበበ እንዳይሆን ስልጠና ያስፈልገናል፡፡ 
ይህ ስልጠና ትልቅ እውቀት የሚሰጥ ነው፤ ስልጠና ባለን እውቀት ላይ ተጨማሪ እውቀት መጨመር ማለት ነው፤ እውቀት እርካታን ይሰጣል፤ በራስ መተማመንን ይፈጥራል፤ በሰልጣኞቹ እጅግ ተደስቻለሁ፤ ትምህርትን እድሜ አይገድበውም፤ የስነ ምግባር ጉድለት የሚወገደው በስልጠና ነው፤ በአንድ ጊዜ ሶስት ደረጃ ላይ መውጣት አይቻልም፤ ድርሻን ማወቅም ያስፈልጋል፤ የሌላውን ድርሻ ለመውሰድ መንጠራራት አያስፈልግም፤ ኦዝያን ያለ ድርሻው ገብቶ በለምጽ ተመቷል፤ ሰንበት ት/ቤቶች ተጠሪነታቸው ለሰበካ ጉባኤ ነው፤ የሰንበት ተማሪ ልቅና ሥርአት አልባ ከሆነ ለቤተክርስቲያን አይጠቅማትም፤ ቤተክርስቲያን ወጣቶችን መቆጣጠር አለባት፤
 የሽብር ቡድንና የጥፋት ሐይሎችም ተነስተዋል፤ እነዚህ የጥፋት ሀይሎች የራሳቸውን ታሪክ ጭምር ያጠፋሉ፤ እነዚህ የጥፋት ሀይሎች በዙሪያችን ያንዛብባሉ፤ ስለዚህ እኛ በጸሎት መትጋት አለብን፤ ወገኖቻንን ያረዷቸው እኛ ጋር መድረስ ስላልቻሉ ነው፤ እኛ እንደ አባቶቻችን መንቃት አለብን፤ ቤተክርስቲያን የማስተማር ድርሻ አላት፤ ሀገራችን በነጻነት የቆየች ሀገር ናት፤ ሥራችን ሁሉ ኮምፒውተራይዝድ መሆን አለበት፤ በዓለም ላይ እየኖርን ስለሆነ ዓለም የሚጠቀምበትን መሳሪያ ለመጠቀም ጥረት ማድረግና መፍጨርጨር አለብን፤ ሠራተኞቻች ደመወዛችሁን በባንክ በመቀበላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ቅዱስነታቸው ሰፊ ትምህርት ከሰጡ በኋላ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

{flike}{plusone}