የሀገረ ስብከት ቅድመ ታሪክ
- ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የምትጓዘው ሐዋርያት በተጓዙበት መንገድ ነው፤ ሥርዓቷም ትወፊቷም፣ አሠራርዋም ሐዋርያዊ ነው፡፡ አባቶቻችን ሐዋርያት ወንጌል ሰብከው ሃይማኖት ያስፋፉት አህጉረ ስብከትን እየመሠረቱ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ባለበት ሁሉ ሀገረ ስብከትን መመሥረት እና ማጠናከር ሃይማኖታዊ ግዴታ በመሆኑ ነው፡፡
- የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት በወጥነት ለማስጠበቅ፡ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ሥርዓት እና ትውፊት ወጥ በሆነ መልኩ ሊጠበቅ የሚችለው አንድ ወጥ የሆነ የማስጠበቂያ መንገድ ሲኖራትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን፤ ልዩ ልዩ ተቋማትን፤ ካህናትና ምእመናንን በአንድነት ማስተባበር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
- የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን አንድነት እና ትብብር ለማጠናከር፡— በአዲስ አበባ የሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከሀገረ ስብከቱ መመሪያ በመቀበልናበመመካከር የተመሠረቱ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በመካከላቸው የሚኖረውን ግንኙነት የሚያስተባበር፣ እንዲረዳዱ፤ እንዲተባበሩ እና ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በጋራ እንዲሠሩ የሚያደርግ ማዕከላዊ አካል አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
- ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው ኢኮኖሚካል ግንኙነት መንገድ ለመጥረግ፡- በአኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለሚደረገው ሃይማኖታዊ ግንኙነት፣ ከሌሎች ጋር ለሚደረገው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ሲኖዶስን ወክለው መሥራት አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ግንኙነቱ በሊቀ ጳጳስ ደረጃ መደረግ ያአለበት በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ግንኙነት መልከ ለማስያዝ፣ ደረጃውን ለማስጠበቅና ውጤታማ ለማድረግ የተጠናከረ እና ከሌሎች በእኩልነት የተደራጀ ሀገረ ስብከት ያስፈልገናል፡፡
- በገጠርና በከተማ የሚገኙ ገዳማት እና አድባራትን በተጠናከረ መንገድ ለመርዳት፡- በችግር ላይ ያሉትን ገዳማት እና አድባራት በተበታተነ መንገድ ሳይሆን አንድ ወጥ እና ውጤት ሊያመጣ በሚችል መንገድ ለመርዳት እንዲቻል በማዕከላዊነት የሚያስተባበር እና የሚከታተል አካል ያስፈልገናል፡፡ ይህ አካል በሀገረ ስብከቱ ያለውን አስተዋጽዖ የሚያስተባብር፣ ሠንሠለቱን ጠብቆ ከመንበረ ፓትርያርኩ ጋር በመገናኘት ሥራው እንዲፈጸም የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና መሠረት ጉዳዩ የሚመለከተው በሀገረ ስብከት ደረጃ ነው፡፡
- ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለማስተባበር፡— አንድነትን ለማምጣት እና ተባብሮ ለቤተ ክርስቲያን ለማገልገል በማሰብ የተደራጁ አያሌ ማኅበራት፣ ተቋማት እና በጎ ፈቃደኞች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራት እና አንድነቶች ከአጥቢያዎች ዐቅም እና ወሰን በላይ በመሆናቸው ላቅ ያለ አስተባባሪ እና አጋዥ አካል ያስፈልጋቸዋል፡፡ የእነዚህ ማኅበራት እና አንድነቶች አገልግሎት የተቃና፣ የተሳካ እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ ደግሞ ከሀገረ ስብከቱ የተሻለ መዋቅር አይገኝም፡፡ ሀገረ ስብከቱ ተደራጅቶ የአገልግሎት መሥመሩን በሚገባ ካልዘረጋ በቀር የእነዚህ ማኅበራት እና አንድነቶች አገልግሎት ዝርው ይሆናል፡፡ ከዋናው ግንድ የተለየ ቅርንጫፍ ነውና፡፡
- ኢትዮጵያውያን የሆኑ ወገኖችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማቅረብ፡— ኢትዮጵያውያን የሆኑና ያልሆኑ ወገኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርበው፤ ወንጌል ተምረው፣ አምነው እና ተጠምቀው የዚህች ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ ኃላፊነታችን ነው፡፡ የእነዚህ ወገኖቻችን ሱታፌ ደግሞ በማመን እና በመጠመቅ ማብቃት የለበትም፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ነባር ትምህርት ተምረው አሠረ ክህነቱንም መከተል አለባቸው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ከገዳማት አድባራት፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ት/ቤቶች እንዲሁም ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚያገናኛቸው አካል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሀገረ ስብከቱ መጠናከር ወሳኝ ነው፡፡
- ገዳማት እና ማሠልጠኛዎችን ለማቋቋም እና ለመምራት፡— አዲሱ ትውልድ ከገዳማዊ ሕይወት እና ሥርዓት ጋር እንዲተዋወቅ፣ ምእመናን ሱባኤ እንዲይዙበት፣ ጠበል ለመጠመቅ፣ ጸሎት ለማድረግ እና ከዚህ ዓለም ጭንቀት ራስን ለመፈወስ የሚያስችሉ ገዳማትን በምንኖርበት ዓለም ለመመሥረት እና ለማስተዳደር፣ ከዚያውም ጋር አያይዞ ማሠልጠኛዎችን በማቋቋም ካህናትን፣ ዲያቆናትን እና መምህራነ ወንጌልን ለማፍራት የበላይ ሆኖ የሚከታተለውና ሥርዓቱን የሚያስጠብቀው ሀገረ ስብከት ቀድሞ መደራጀት ይገባዋል፡፡