የሀገረ ስብከቱ ጽ /ቤት ከከተማው አስተዳደር የዕውቅና ሽልማት ተበረከተለት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ /ቤት በ2012 ዓ. ም ላከናወናቸው በጎ የማኅበራዊ አገልግሎት ተግባራት የእውቅና ምስክር ወረቀት ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እጅ ተበርክቶለታል።
ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሸራተን አዲስ ሆቴል ባዘጋጀው የምስጋና መርሐ ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በማኅበረሰብ አገልግሎት ላደረገው አስተዋጽኦ የተበረከተለትን ስጦታ የተቀበሉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ፣ ሽልማቱ በቀጣይ ለሌሎች የተጀመሩ በጎ ሥራዎች ብርታት እንደሚሆን ለዝግጅት ክፍላችን አስረድተው በቀጣይ ቤተክርስቲያናችን ከፍ ብላ የምትታይበትን ሥራ ለመሥራት የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገረ ስብከቱ ጽ /ቤት በቋሚነት ለደብረ ሊባኖስ ገዳምና ለታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ፣ በሀገር ደረጃ ለሚቀርብለት የበጎ አድራጎት ጥሪ በጎ ምላሽ መስጠቱ የሚታወስ ነው።