የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ በችግኝ ተከላና ክብካቤ ዙሪያ የቀረበለትን ጥናት ተወያይቶ አጸደቀ

የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ በችግኝ ተከላና ክብከቤ ፕሮጀክት ዙሪያ ተወያይቶ ተግባራዊ እንዲሆን ወሰነ፡፡ በሀገረ ስብከቱ ዕቅድና ልማት ዋና ክፍል በኩል በተጋበዙ ባለሙያ ተዘጋጅቶ የቀረበው “የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የችግኝ ተከላ እና ክብካቤ ፕሮጀክት” በከተማችን ባሉ ገዳማትና አድባራት የነበረው ዐጸደ ቤተ ክርስቲያን ሽፋን በልማትና በተለያዩ ግንባታዎች እየተመናመነ በመምጣቱ የደን ሽፋኑን ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ያለመ ነው፡፡
በባለሙያ የቀረበው የችግኝ ተከላና ክብካቤ ፕሮጀክት፡-
❖ የተራቆቱ አጥቢያዎች ችግኝ ተከላ፣
❖ የተመረጡ አጥቢያዎች ችግኝ ተከላ፣
❖ በጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ዳርቻ ላይ ችግኝ የመትከልና የማልማት መርሐ ግብሮችን የያዘ ነው፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ዕጽዋት ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸው የጉባኤ አባላቱ በማውሳት፤ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ከተለመዱ አጀንዳዎች ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት ጥናት ላይ ትኩረት አድርጎ ውይይት ማድረጉ መልካም ነው ብለዋል፡፡

በፕሮጀቱ ከቀረቡት መነሻ አሳቦች መካከል ዝርዝር አፈጻጸምና መመሪያ የሚስፈልጋቸውን በመለየት፤ ጥንታዊ ከሆኑትና የደን ሽፋናቸው በተራቆቱ አብያተ ክርስቲያን፣ በቅርብ ዓመታት በተተከሉ አብያተ ክርስቲያን እንዲሁም በጥምቀተ ባሕር ቦታ ዳርቻዎች የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንዲከናወን ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራች ካበረከተቻቸው በርካታ አስተዋጽኦ አንዱ የደን ሽፋን እንዲስፋፋ በማድረግዋ መሆኑዋ የሚታወስ ነው፡፡