የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት 44ኛውን ዓመታዊ ሀገረ ስብከት አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በመንበረ ጵጵስና አዳራሽ አካሄደ

የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት 44ኛ ጠቅላላ ሀገረ ስብከት አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤውን የጀመረ ሲሆን ጉባኤውም ኅዳር 13 ቀን 2018 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አኅጉረ ኤ ሊቀ ጳጳስ መሪነት ተጀምሮ ለቅድስት ቤተክርስቲያን የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ፍጻሜውንአ አግኝቷል።
በጉባኤው ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መለአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሤ ባወቀ፤የሀገረስብከቱ የየመምሪያ ክፍል ኀላፊዎች፤ የወረዳ ቤተ ክህነት ሊቃነ ካህናት ፣ የሆሳዕና ከተማ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ የሆሳዕና የማኅበረ ቅዱሳን ሆሳዕና ማዕከል ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ሀዲያና ስልጤ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት ቃለበረከትና የሥራ መመሪያ አስተላልፈዋል።
ጉባኤው ለአንድ ቀናት የተካሄደ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ የሥራ ክንውን ሪፖርት እና በዋናነት ሕንጻ ስላሴን መሰረት በማድረግ ትኩረት ተሰጥቶባቸው ውይይት ተደርጓል።በዕለቱም በዶ/ር ሳምሶን የኃይለሚካኤል “የሀዲያና ስልጤ ሀገረስብከት ትናንትና ዛሬ በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል።
በመጨረሻም ሲካሄድ የነበረው 44ኛው የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት መደበኛ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ባለ10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣትና በበጀት ዓመቱ አወዳዳሪ ኮሚቴው ባወጣው መስፈርት መሰረት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ወረዳዎችና የከተማ አድባራትና ገዳማት እንዲሁም ለቅድስት ቤተክርስቲያን ዋጋ እየከፈሉ ላሉ አካላት ሽልማት ተበርክቶላቸው መርሐ-ግብሩ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባታዊ ቡራኬና ቃለ ምእዳን ፍጻሜውን አግኝቷል። ዘገባው የብሕንሳ ሚዲያ ነው።