ዜና እረፍት

1599

የመንበረ ፖትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ማርያም የበላይ ኃላፊ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ሊቀ ጳጳስ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለዩ፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ሊቀጳጳስ ከአባታቸው ከመምህር ሀብተ ማርያም ደስታ ተክሌና ከእናታቸው ከወ/ሮ በስሙ ቸርነት ታኅሣሥ 19 ቀን 1925 ዓ.ም በድሮው አጠራር ሸቸ ጠቅላይ ግዛት ሰላሌ አውራጃ እንሳሮ ወረዳ እየተባለ ይጠራ በነበረው በአሁኑ አጠራር በውጨሌ ወረዳ ልዩ ስሙ በርጋፈት ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ተወለዱ፡፡ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በታላቁ ገዳም በጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳም ገብተው ከመምህር ደነቀ ወልደ ኪሮስ ከፊደል ጀምሮ የዳዊት የንባብና የቃል ትምህርት ተምረዋል፡፡
ከመምህር ገ/ጊዮርጊስ እንግዳወርቅ መዝገበ ቅዳሴን ተምረው አጠናቀዋል፡፡ በመቀጠልም በ1945 ዓ.ም ወደ ታላቁ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም በመሄድ ከአለቃ ዐምደ ሥላሴ ኃ/ማርያም ቅኔ ከእነአገባቡ እንዲሁም በባሕረ ሃሳብ ትምህርት አጠናቀው ተምረዋል፡፡ በ1950 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፖትርያርክ መልካም ፈቃድ ከመልአከ ገነት አፈወርቅ ገ/ሥላሴ እና ከአለቃ ታመነ አግደው የብሉያትን ትርጓሜ ተምረዋል፡፡
የሥራ ሁኔታን በተመለከተ
1.ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ሊቀ ጳጳስ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት በሚያስተዳድራቸው መሥሪያቤቶች እየተዘዋወሩ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል በዚህ መሠረትም በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የስብከተ ወንጌል ማሕበር ሲቋቋም የትምህርት ክፍል ኃላፊ በመሆን
2.በጽርሐ አርአያም ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት በመምህርነት
3.በኢሊባቡር ሀገረ ስብከት በጎሬ ወረዳ በስብከተ ወንገል እና የአውራጃው ቤተክህነት ኃላፊ በመሆን፡፡ እንዲሁም በካህናት ማሰልጠኛ ተቋም በመምህርነት አገልግለዋል፡፡
4.ከ1953-1978 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የጎሬ አውራጃዎች ወንጌልን በማስተማር አገልግለዋል፡፡
5.ከ1978-1983 ዓ.ም ድረስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል፡፡
6.ከ1983-1987 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የቅዱስ ፖትርያርክ ግቢ ንብረት ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል፡፡
7.ከ1987-1991 ዓ.ም ድረስ የቅዱስ ሲኖዶስ ማህበራዊ ኑሮ መጋቢ ሆነው ሰርተዋል፡፡
8.ሐምሌ 5 ቀን 1991 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አምስተኛ የኢትዮጵያ ፖትርያርክ አብሮተእድ የኤጴስ ቆጰስነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ እንዲሁም የመንበረ ፖትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የበላይ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
9.የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ በመሆን ለ6 ዓመታት አገልግለዋል፡፡
የተለያዩ የትሩፋት ሥራዎችን በተመለከተ
1.ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ሊቀ ጳጳስ ከራሳቸውና ከሚረዷቸው ቤተሰቦች ጥቅም ይልቅ የሌሎች ችግረኞችን ጥቅም የሚያስቀድሙ ቸር ርኀሩኀ አባት እንደመሆናቸው ልማትን ማዕከል ያደረገ የተለያዩ የትሩፋት ሥራዎችን አበርክተዋል ለማስረጃም ያህል
2.በበርጋፈት ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በመክፈት ለመምህራንና ለደቀ መዛሙርቱ ሰርክ ኀብስት የሚሆን ገንዘብ ከደመወዛቸው በመደጎም የአካባቢው ልጆች ተምረው ክህነት ተቀብለው ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲበቁ አድርገዋል፡፡
3.ብፁዕነታቸው ትምህርት እንዲስፋፋ የቤተክርስቲያን የሊቃውንት ምንጭ እንዳይደርቅ ተተኪ ደቀመዛሙርት እንዲጠሩ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ በጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳም የንባብ መምህር በግል ገንዘባቸው ቀጥረዋል፡፡
4.ሰው ለሰው እየተባለ ከሚጠራው በጎ አድራጊ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ገጽ ለገጽ በመነጋገር ከመርጋፈት መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ጎን ለጎን ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከ1-8 እንዲሰራ በመጠየቅ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ትምህርት ቤት እንዲሰራ አድርገዋል፡፡ የመምህራን መኖሪያ ቤትም አብሮ እንዲሰራ የሶላር ሲስተም መብራት እንዲገባላቸው በማድረግ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በዚህ መሠረትም በአሁኑ ወቅት ከ4000 ያላነሱ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
5.ብፁዕነታቸው ድንቁርና ጠፍቶ እውቀት እንዲሰፋፋ፣ በሽታ ጠፍቶ ጤንነት እንዲረጋገጥ፣ የመኪና መንገድ፣ የጤና ኬላ ተሰርቶ ኅብረተሰቡ እንዲረዳ በማድረግ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ አገልግለዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ሊቀጳጳስ ባደረባቸው ሕመም ምክህያት በልዩ ልዩ ሆስፒታሎች በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለድ በ82 ዓመታቸው ሐምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸውም በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ብፁዓን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት የጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ወዳጅ ዘመድ የትውልድ አካባቢ ነዋሪዎች በተገኙበት አቶ ጌታቸው ዓለማየሁ የተባሉ የቅርብ ወዳጃቸው ባሠሩላቸው መካነ መቃብር በተወለዱ በ82 ዓመታቸው ሐምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ተፈጽሟል፡፡
እግዚአብሔር አምላከችን ነፍሳቸውን ለቅዱሳን አበው ባዘጋጀው መካነ ዕረፍት ያሳርፍል፡፡

{flike}{plusone}