ዓመታዊ የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓልና የቤተ መቅደሱ መታደስ በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በድምቀት ተከበረ

ዓመታዊው የአጋእዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓልና የቤተ መቅደሱ መታደስ በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በድምቀት ተከበረ።
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በትናትናው ዕለት የቤተ መቅደሱን መታደስ በዓል የተከበረ ሲሆን በዛሬ ዕለትም የቅድሥት ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የካቴድራሉ ሊቃውንት ማኅሌታውያን “ዮም መላእክት ይየብቡ ወሊቃነ መላእክት ይዜምሩ ሊቃነ መላእክት እስመ መጽአ ውስተ ዓለም ለቢሶ ሥጋ ዚአነ” የሚለውን ወረብ ያቀረቡ ሲሆን በካቴድራሉ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንም “ሃሌ ሃሌ ሉያ ተወልደ ለነ ሕጻን ክብሮሙ ለቅዱሳን” የሚለውን ያሬዳዊ ምስጋና አቅርበዋል። በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መልእክት አስተላልፈው የሚያስተምሩት ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ጋብዘዋል።
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ በመልእክታቸው ላይ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከ81 ዓመታ በኋላ ሙሉ የሚባል ዕድሳት ተደርጎለት በትናትናው ዕለት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ተባርኮ የቤተ መቅደስ ዕድሳት በዓል መከበሩን አስታውሰዋል።
በዚህ ብርቱ ተግዳሮቶች በተበራከቱበት ወቅት ጥንታዊውን ባለታሪኩን ካቴድራል በማድስ ለቡራኬ በዓል ያበቁንት ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የካቴድራሉ አስተዳደርን፣ ሰበካ ጉባኤ፣ ሕንጻ ዕድሳት ኮሚቴንና ስሜን እግዚአብሔር ያውቀዋል ብለው ከሚሰጡት ኦርቶክሳውያን ጀምሮ በርካታ አካላትን በእጅጉ አመስግነዋል።
ትምህርት ወንጌል የሰጡት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓሉ የሚከበርበትን ታሪካዊ ምንነትና በረከት የሚገኝበትን መንገድ አስተምረዋል።
ቀጥለውም የቤተ መቅደሱ የመታደስ በዓል እውን እንዲሆን የጥንት አባቶችን ሕያው ሥራ በተግባር በቀጠሉ የተሰማችን ጥልቅ ደስታ ገልጸዋል።
የዚህ ዘመን ትውልድ ዋነኛ ተግባሩ ታሪክ መሥራት እንኳ ቢከብድ ታሪክ መጠበቅ አማራጭ የሌለው አብነታዊ መንገድ መሆኑን የጠቆሙት ብፁዕነታቸው የካቴድራሉን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት ተጠብቆ ኦንዲቀጥ ላደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም አመስግነዋል።
ዓመታዊ በዓልና የቤተ መቅደስ መታደስ በዓሉ የአገልግሎት ማሰሠሪያው በሆነው በጸሎተ ቅዳሴ ብፁዓን አበው ለሊቃነ ጳሳት ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።
በዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሌሎች ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ክብርት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የኢፌድሪ የቀዶሞ ፕሬዝዳንት፣ የግርማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ቤተሰቦች ፣የመንበረ ፓትርያርክና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የካቴድራሉ ከሌሎች ቦታዎች የመጡ ሊቃውንት፣ ሰንበት ተማሪዎችና በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናትና ምእመናን የበረከቱ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ