ዓመታዊው የወርኃ ጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጀመረ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዓመታዊው የወርኃ ጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቀን 12/2012 ዓ.ም በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመግለጫ ንግግር ተጀመረ፡፡
በምልአተ ጉባኤው የመክፈቻው ንግግር ላይ የቤተክርሰቲያኗ፤የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች ተገኝተው የዘገቡ ሲሆን ፓትርያርኩም ወቅታዊ የሆኑትን የቤተክርስቲያኗን ተግዳሮቶች በመጥቀስ ከምልአተ ጉባኤው ምን እንደሚጠበቅ ሰፋ ያለ መግለጫ አስተላልፈዋል፡፡
“አሁንም በእናንተ ያለውን የእግዚአብሔርም መንጋ ጠብቁ” (1ኛ ጴጥ 2፡6) የሚለውን መለኮታዊ ቃል መነሻ በማድረግ የቤተክርስቲያን ዋና ዓላማ ምእመናን ከጥፋት መጠበቅ፤ማስተማር፤መንከባከብ፤ያላመኑትን በወንጌል ስብከት ማሳመን እንደሆነ ቅዱስነታው አበክረው ገልጸዋል፡፡
የቤተክርስቲያኗ አባልና ተከታይ የሆነ ሁሉ ከዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለቤተክርስቲያኗ የሚጠቅሙና አሁን ካለችበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች የምትላቀቅበትና የምትወጣበት መንፈሳዊ የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንደሚቀርቡ በጉጉት ይጠብቃል፡፡
የቅዱስነታቸው ሙሉ የመግለጫ ንግግር ከዘህ በታች ቀርቧል
መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡- ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ- ብፁዕ አቡነ ዮሴፍየቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊናየምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ- ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የዋጀ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለዓመታዊው የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አደረሰን አደረሳችሁ፡፡
“ወይእዜኒ ረዐዩ ዘሀለዉ ኀቤክሙ መርዔቶ ለክርስቶስ፤ አሁንም በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ (1 ጴጥ 2.6)፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ፣ ጠባቂ፣ መጋቢ፣ አስተናባሪና አስተዳዳሪ ነው፤ በሰማይና በምድር ያለው የሚታየውና የማይታየው ፍጥረት በአጠቃላይ በእግዚአብሔር ጥበቃና አስተዳደር ሥር ነው፤ፍጡራን ከእሱ በተገኘ የአእምሮ ነጻነት በሚፈጽሙት ተግባር የራሳቸው ድርሻና ኃለፊነት እንዳላቸው ቢታወቅም ያለእርሱ ዕውቅና የሚደረግ እንደሌለ ግን ከቅዱስ መጽሐፍ እንማራለን፡፡
እንግዲህ እሱ የጠባቂዎች ጠባቂ ሆኖ ሳለ ከፍጡራን ወገን ደግሞ በልዩ ምርጫው እየሾመ መንጋውን ወይም ፍጥረቱን ያስጠብቃል፤ ይህ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የእግዚአብሔር አሠራር እንደሆነ ቅዱስ ያሬድ ሲገልፅ “ኢኃደጋ ለምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፤ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት አንሥቶ እስከ ዘላለሙድረስ ምድርን ያለካህናት እና ያለ ዲያቆናት አልተዋትም” በማለት ያረጋግጣል፡፡
ይህ የሚያመለክተን እግዚአብሔር ዓለምን ያለ ጠባቂ የተወበት ዘመን ካለመኖሩም ሌላ ጠባቂዎቹ ካህናትና ዲያቆናት መሆናቸውን ነው፤ ካህናት የሚለው ስያሜ የወል ስም ሆኖ ከቅዱስ ፓትርያርክ ጀምሮ ያለው ውሉደ ክህነት በሙሉ እንደሚያጠቃልል ይታወቃል፡፡ከዚህ አኳያ ኰኵሐ ሃይማኖት ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን በተሰጠው የጥበቃ ኃላፊነት መሠረት እሱም በክህነት ለወለዳቸው ልጆቹ በፈንታው “መንጋውን ጠብቁ” እያለ ምእመናንን ሲያስጠብቅ እናያለን፡፡
ትልቁ የእግዚአብሔር ትእዛዝና የቤተ ክርስቲያን ተልእኮም ይህ የጥበቃ ተግባር ነው፡፡እግዚአብሔር እኛ ካህናትን በኃላፊነት የሾመበት ዋና ዓላማ መንጋውን እንድንጠብቅለት ነው፤ ይህ መንጋ ተብሎ የተገለፀው ወገን የተለየ ሕዝብና ጐሳ ሳይሆን ትዝምደ ሰብእን ወይም የሰው ዘርን በሙሉ ነው፡፡ በራሱ እምቢተኝነት ከሚቀርበት በስተቀር የጌታችን ጥሪ ለትዝምደ ሰብእ በሙሉ እንደሆነ “ሑሩ ወስብኩ ወንጌለ ለኵሉ ፍጥረት፤ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጠረት ሁሉ ስበኩ” በማለት አሳውቆናል፡፡
እንዲህም ከሆነ ጠብቁ ተብለን የታዘዝነው ያመኑትን ወይም የተጠመቁትን ብቻ ሳይሆን ያላመኑትንም ያልተጠመቁትንም በአጠቃላይ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ከዚህ አንጻር መንጋችንን ስንጠብቅ ያመኑትን በነፍሳቸውም በሥጋቸውም ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው የተሟላ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ፣ ያላመኑትንም በፍቅር በማቅረብና ዘመድ ዘመድ በማለት፣ውሣጣዊና መንፈሳዊ ስሜታቸውን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በማነቃቃትና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በማምጣት እንደሆነ ለሁላችን ግልፅ ነው፡፡
ሆኖም ይህን የጥበቃ ሥራ በአግባቡ ለማሳካት ትልቁ ትጥቃችን ቅዱስ ወንጌል እንደሆነ ምን ጊዜም መዘንጋት የለበትም፡፡ቃለ ቅዱስ ወንጌልንለፍጥረት ሁሉ ለማዳረስ የተለያዩ ዘዴዎችንና አቀራረቦችን፣ ሥልጠናዎችንና አስተምህሮችን መጠቀምና በዚህም የባዘነውን በግ ወደ መንጋው የምንመለስበት ታሪካዊና ወቅታዊ ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ የሚባክኑና በተኩላ የሚነጠቁ በጎች እጅግ እየተበራከቱ ነው፤ ዛሬ ሁሉም ነገር መልካም ነው ብለን የምንዘናጋበት ጊዜ ሳይሆን የጐደለውን ለመሙላት ቃል የምንገባበት፣ ያንኑም በተግባር ፈጽመን በጎቻችንን የምንሰበስብበት ጊዜ ነው፤ በዚህ አኳኋን በንቃትና በትጋት በኃላፊነትና በቁጭት ከሠራን ከባዘኑት በጎች መካከል ብዙዎቹን ወደ መንጋቸው መመለስ እንደምንችል፣ ያሉትም ባሉበት ጸንተው እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
• ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
የጥበቃ ተግባራችን ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ከውስጥ ጥቅመኞች የተነሣ ተደጋጋሚ እንቅፋት በበዛበት በአሁኑ ጊዜ ‹‹በእንቅርት ላይ…….$ እንደሚባለው በሀገራችን በተፈጠረው ያለመረጋጋት ክሥተት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ካህናትና ምእመናን ተገድለዋል፤ አሁንም ሥጋቱ እንዳለ፣ ከቀረበልን የአህጉረ ስብከት ሪፖርት ሰምተናል፤ በዓይናችንም አይተናል፤ ነባር የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታዎች ሥልጣንን መከታ ባደረጉ ወገኖች እየተነጠቁ ነው፤ ምእመናን በሚደርስባቸው የማያባራ ተፅዕኖና አድልዎ ከቀያቸው እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ ነው፡፡
ለመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ ኢሰብአዊ ድርጊት እስከመቼ ነው የሚቀጥለው? ይህ ድርጊት እንዲቆም እስከሞት ድረስ መሥዋዕት መሆን ከዚህ ጉባኤ አባላት ይጠበቃል፡፡ ይህ ጉባኤ የኃያሉ የእግዚአብሔር ጉባኤ ነው፤ ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ብቻ ከሰባ ሚሊዮን ያላነሰ ሠራዊት ያለው ጉባኤ እንጂ ብቻውን አይደለም፤ ይህ ጉባኤ በሙሉ ዓቅሙ ሥራውን ከሠራና ድምፁን ካነሣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ሁሉ ሰሚው ብዙ ነው፡፡
ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር እየደረሰብን ያለውን የማንታገሠው ግፍ መንግሥት እንዲያስተካክልልን ደጋግመን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እኛም በጸሎት አምላካችንን ከመማፀን ጋር ሁሌም በተጎጂው ሕዝባችን መካከል እየተገኘን በልዩ ልዩ ግፍ ልባቸው የተሰበረውን የልጆቻችን ኃዘን መቅረፍ ይኖርብናል፡፡ ችግራቸውንም መጋራት ይጠበቅብናል፤ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንደገና መገንባት አለብን፤ መንግሥትም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የሃይማኖት ክብር ነጻነትና እኩልነትን በሚሸረሽሩ የታችኛው መዋቅር ባለሥልጣናት ላይ የማያዳግም የእርምት ማስተካከያ እንዲያደርግ ጥብቅ ክትትል ማድረግ አለብን፡፡
• ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሲኖዶስ አባላት!
የመንጋ ጥበቃችን ሥራ እየተሰነካከለ የሚገኘው ከውጭ ሆነው በገንዘብ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ እርስ በርሳችንን በመከፋፈል በሚተነኩሱን ኃይሎች ብቻ አይደለም፤ በውስጣችን ያለው ያልዘመነ አሠራርም የምእመናንን ልቡና እያቆሰለ የሚገኝ ሌላው የጥበቃችን እንቅፋት ነው፤በመሠረቱ ይህንን ችግር ከሥር መሠረቱ ነቅለን በማፅዳት ማስተካከልካልቻልን ችግራችን በወሳኝ መልኩ ሊቀረፍ አይችልም፡፡በመሆኑም ቀደም ሲል የተጠኑትን የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ችግር መፍትሔና የመሪ ዕቅድ ጥናቶች ይህ ዓቢይ ጉባኤ በወሰነው መሠረት ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአስቸኳይ ይተገብር ዘንድ ጠበቅ ያለ መመሪያ ሊያስተላልፍ ይገባል፡፡ከእንግዲህ ወዲህ በብልሹ አስተዳደር አዙሪት የሚታመስ የቤተ ክርስቲያን አሠራር ሊኖር አይገባም፤ በዚህ ዓመት አሠራራችንን ሁሉ አስተካክለን ወደ መንጋ ጥበቃና ወደ ልማት ሥራችንበፍጥነት መሸጋገር አለብን፡፡
በመጨረሻም፡-
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን ዙሪያ መለስ ጥቃት ለመመከትና ለመከላከልብሎም ለማስቆም አንድ የጥቃት መከላከል ግብረ ኃይል እንደዚሁም በየአካባቢው የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች፣ ወከባዎች፣ ተፅዕኖዎችና አድላዊ አሠራሮችን እየተከታተለ ትክክለኛ ኢንፎርሜሽንን የሚያቀርብ የኮሙኒኬሽን ግብረ ኃይል በአሁኑ ጉባኤያችን አቋቁመን ቤተ ክርስቲያናችንንና መንጋችንን ከመከራ እንድንታደግ የሀገራችንን ሰላምና የሕዝባችንን አንድነትምበጽኑ እንድናስጠብቅ አባታዊ መልእክታችንን እያስተላለፍን፣ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መከፈቱን እናበሥራለን፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም
.አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ