ዓመታዊው የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከበረ
ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ አረጋዊው አባት ብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ፣ የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መ/አሚን አባ ላዕከ ማርያም፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሲራክ እንዲሁም የደብሩ ማኅበረ ካህናትና እጅግ በርካታ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናን በተገኙበት የእግዚአብሔርን ክብር በሚገዳደር መልኩ በሰናዖር ሜዳ ላይ የተሠራውን ሕንጻ ሰናዖር እግዚአብሔር ያፈረሰበትንና መግባቢያ ቋንቋቸውንም የደባለቀበትን ዕለት በሚዘከርበት ሁኔታ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የዕለቱን ታሪክ የተመለከተ ሰፊ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በእኛም ዘመን የእግዚአብሔርን ክብር የሚጋፋ የትኛውም ዓይነት ክፉ ተግባር እንዳናከናውን ደግሞም በሕይወታችን ያለውን የኃጢአት ክምር በንስሐ እናፈርሰ ዘንድ መልእክት ተላልፏል፡፡
በመቀጠልም ካቴድራሉ በ1924 ዓ.ም ተመስርቶ በ1936 ዓ.ም መንፈሳዊ አገልግሎት መጀመሩና ለረጅም ጊዜያት ማለትም ለሰባ ሰባት ዓመታት ያክል አገልግሎት በመስጠቱ የተነሣ በከፍተኛ ጉዳት ውስጥ እንደሚገኝ ተገልፆ በአሁኑ ስዓት ግን ይህንን ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርስ ለመታደግና የዕድሳት ሥራ ለመሥራት ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገርና ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች እንደ ተዋቀረና በእንቅስቃሴ ላይም እንደሚገኝ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተደምጧል፡፡
በመጨረሻም የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የዕለቱ ትምህርት በሰፊው ተሰጥቷልና ይበቃናል፣ የሰማነውን በሕይወት እናኑረው፣
ይህ ትልቅ ካቴድራል ከመንፈሳዊ ቦታነቱም ባሻገር የቤተ ክርስቲያናችንን ብሎም የሀገራችንን ታሪክ ጠገብነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፣ ስለሆነም የተጀመረው የዕድሳት እንቅስቃሴ የሕንጻውን ታሪካዊ ማንነት በጠበቀ መልኩ መታደስ ይኖርበታል፣ ለዚህም መልካም ተግባር ሀገረ ስብከታችን በአስፈላጊው ነገር ሁሉ ከእናንተ ጋር ነው በማለት አረጋግጠዋል።
የጥምቀት በዓልም ኦርቶዶክሳዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ እንዲከበር ለሕዝበ ክርስቲያኑ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀ/ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ