“ውስጣዊ ችግሮቻችን በመፍታት ምእመናን ላይ መሥራት ይኖርብናል” “ተቃራኒዎችን ያበዛናቸውን እኛው መሪዎቹ ነን ምእመናኑ ላይ ምን ችግር የለም! ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ፪ኛ ዓመት አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት አጠናቋል።
ኅዳር 01 ቀን 2018 ዓ.ም የጀመረው የሸገር ስቲ ሀገረ ስብከት አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዛሬ ዕለትም የቀጠለ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደን ፣ የደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ትምህርተ ወንጌልና ቃለምዕዳን አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው “ስለኢየሩሳሌም ደኅንነት ተነጋገሩ” በሚል ርዕስ ያስተማሩ ሲሆን ስለሀገራችን ሰላም፣ አንድነት፣ ደኅንነት በመነጋገር ለሀገራችን ሰላም ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት መሥራት እንደሚገባ ገልጿል።
መልአከ ሰላም ዶ/ር አባ ቃለጽድቅ ሙልጌታ በጠቅላይ ቤተክህነት የሰበካ ጉባኤ ማዳራጃ መምሪያ ኃላፊ ለተሰብሳቢዎቹ “ሁለንተናዊ የቤተክርስቲያን አስተዳደር” በተመለከተ ሥልጠና ሰጥተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የራያና ደቡብ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ አገልጋዮች ተገኝተዋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁም ብፁዓን አባቶች በጉባኤችን ስለተገኙልን እጅግ እናመሰግናለን ብለዋል። ለቀጣይ ዓመትም መንፈሳዊ አገልግሎቱን በማጠናከር ቤተክርስቲያንን በምጣኔ ሀብት ለማሳደግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል ።
አክለውም በአሁናዊ የቤተ ክርስቲያናችን ሁኔታ ተቃራኒዎችን ያበዛናቸውን እኛው መሪዎቹ ነን ምእምናኑ ላይ ምን ችግር የለም። ስለሆነም
ውስጣዊ ችግሮቻችን በመፍታትን ምእመናን ላይ መሥራት ይኖርብናል” ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው ቤተክርስቲያን እናቱ ያልሆነችለት ሰው እግዚአብሔር አባቱ ሊሆንለት አይችልም፤ ሀገረ ስብከቱ በመልካም መሪ እየተመራ በመሆኑ ውጤታማ ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል። አክለውም ብፁዕነታቸው ሁላችሁም በአንድነት በመተሳሰብ ለአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት እንድትሠሩ በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሁለቱም ቀናት የነበረውን ቆይታ በማስመልከት ጉባኤው 12 ነጥቦችን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
በሥራቸው፣ በአገልግሎታቸው ውጤታማ አፈጻጸም ላሳዩ ኃላፊዎች፣ አስተዳዳሪዎች፣አገልጋዮች ሽልማትና ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል።
በመጨረሻም በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የጉባኤው ማጠናቀቂያ ሆኗል።
@EOTCTV