“ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኵሎ ጽድቀ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል ” (ማቴ. 3፡15)
ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት እንኳን ለ2018 ዓ.ም በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ፡፡በማቴዎስ ወንጌል ተጽፎ የሚገኘውና ከላይ መነሻችን ያደረግነው ቃል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጥምቁ ዮሐንስ የነገረው ቃል ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ እርሱ በጌታ ሊጠመቅ እንጂ እርሱ ጌታውን ለማጥመቅ እንደማይችል በትሕትና በመግለጽ ሊከለክለው እየሞከረ ነበር፡፡ ጌታችን ግን፣ ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኵሎ ጽድቀ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል በማለት ፍቀድልኝ አለውና ያን ጊዜ ፈቀደለት፡፡ ይህ በክርስትና አስተምህሮ ውስጥ እንደ መዓዘን ድንጋይ የተቀመጡ ቁልፍ ጉዳዮች መነሻ ነው፡፡ ሕግን በመተላለፍ ምክንያት ከሰው የተወሰደው ልጅነት ሕግን በመፈጸም የሚመለስበት ሥርዓት ተሠርቷል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ተገልጧል፡፡ እግዚአብሔር አብም የምወደው፣ በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት በማለት ተናግሮለታል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ሲወርድና በራሱ ላይ ሲቀመጥ የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በግልጽ ታይቷል፡፡ ቅዱስ ያሬድ፡ በዮርዳኖስ ተጠምቀ ፈጺሞ ሕገ ወአስተርአየ ገሃደ በዮርዳኖስ ተጠመቀ ሕግን ፈጽሞ በግልጽ ታየ እያለ የዘመረበትም ምክንያት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ቤተ ክርስቲያናችን በአደባባይ ከምታከብራቸው ዓበይት በዓላት አንዱ ሲሆን ረጅም ዘመንና ታሪክያለው በዓል ነው፡፡ ከበዓሉ ሃይማኖታዊ የአስተምህሮ መሠረት ጋር በባህላዊ መገለጫዎችና በሕዝብ ከሕዝብ ትሥሥር ፈጣሪነቱ በሰፊው የሚታወቅም በዓል ነው፡፡ በዓሉን ለማክበር በሚልየኖች የሚቆጠር ሕዝብ ከቤቱ ወጥቶ የሚገናኝበት ሲሆን ሰላሙንና አንድነቱን የሚጠብቅበት ሥርዓት አለው፡፡ መከባበር፣ መተሳስብና በተገቢው መንፈሳዊ መንገድ ደስታን መግለጽ የበዓሉ በጎ ገጽታዎች ናቸው። አስተምህሯችን “ሁሉ ነገር በሥርዓት ይሁን” እንደሚል ጥምቀት ሥርዓትን መሠረት አድርገን የምናከብረው በዓል በመሆኑ በልዩ ውበቱ የሚታወቅ በዓል
ሊሆን ችሏል፡፡ ስለዚህ ዛሬም በዓሉን በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዓትና በጎ ዕሤቶቻችንን ሁሉ በመጠበቅ ልናከብረው ይገባል፡፡
በበዓለ ጥምቀት በጌታችን የተመሠረተልንን የጥምቀት ምሥጢር እና ከጥምቀት የሚገኘውን የልጅነትና ጸጋ እናስባለን፡፡ በጥምቀት የምናገኘውን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ፣ ከሥጋዊነት ወደ መንፈሳዊነት መለወጥ፣ እንዲሁም ከኃጢአት ማሠሪያና ከዲያብሎስ ግዛት ነጻ መውጣት እያሰብን ነጭ እንለብሳለን፡፡ ስለተደረገልን ሁሉ እግዚአብሔር አምላካችንን በመንፈሳዊ ዝማሬ እናመሰግናለን፡፡ ከዚህ ውጪ ስዎችን በሐሳብ የሚለያዩ መልእክቶችንና ምልክቶችን እንዲሁም ዓርማዎችን መጠቀም ከበዓሉ መንፈስ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ነገሮቻችን ሁሉ ሰላምን ፍቅርንና አንድነትን የሚሰብኩ ሊሆኑና አሉታዊ ውጤት ካላቸው ነገሮች ሁሉ ልንጠበቅ ይገባል፡፡
ስለዚህ ከላይ እንደተገለጸው ነጭ ቀለም ያላቸው አልባሳትን በመልበስ፣ የሀገራችንን ስንደቅ ዓላማና የቤተ ክርስቲያናችንን ዓርማ ብቻ በመያዝ፣ መልእክቶቻችንን ልዩነት ፈጣሪ እንዳይሆኑ በመጠንቀቅ፣ በዓለ ጥምቀትን በሥርዓት እንድናከብርእያልን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በዓሉን የሰላምና የበረከት በዓል ያድርግልን፣ ሀገራችንን በጽኑ ሰላምና በአንድነት ይጠብቅልን።
ጥር 9 ቀን 2018 ዓ.ም. አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
አባ ሳዊሮስ
የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣
የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሽገር አህጉረ ስብከት
ሊቀ ጳጳስ
