ወርሐዊው የመልዕልተ አድባራት ቀራንዮ መድኃኔዓለም ጉባኤ በወይ ብላ ማርያም ለተገደሉት ወጣቶች መታሰብያ ሆነ
ጥር 12/2014 ዓ/ም የቃና ዘገሊላ በዓል እየተከበረ ባለበት ሠአት በማህደረ መለኮት ወይ ብላ ያለውን ድርብ የቅዱስ ሚካኤልን ታቦተ ሕግ እያጀቡ የነበሩ ወጣቶች በጥይት መገደላቸውን የሚዘክር ልዩ ጉባኤ በመልዕልተ አድባራት ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተደርጓል።
በጉባኤው የደብሩ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ገብረ ስላሴ በአባታዊ አጽናኝ ምክር ሰጥተዋል።ምንም እንኳን ወጣቶቹ የማህደረ መለኮት ወይ ብላ ማርያም አገልጋዮች ቢሆኑም የአንዲት ቤተክርስቲያን ልጆች በመሆናቸው ይህ መታሰብያ እንደተደረገላቸው ገልፀዋል።
የቅዱስ ሚካኤል ታቦተ ሕጉ በተፈጠረው ግጭት እና ወጣቶች መገደል ሳብያ ወደመንበረ ክብሩ ለመግባት ቢሄድ የበለጠ አደጋ እንዳይደርስ በማሰብ በአደራ በመልዕልተ አድባራት ቀራንዮ መድኃኔዓለም ለአንድ ቀን በአደራ ማደሩ ቤተክርስቲያን በአንድነት ለሰላም የምታደርገውን ትብብር እንደሚያሳይ አንስተዋል።
በመታሰብያ ጉባኤው የተገኙት ሊቀሊቃውንት ዮሴፍ በበኩላቸው የወጣቶች ሞት የጻድቃን ሞት እና ሰማዕትነት ነው በሚል በስፍራው ለተገኙት የሟቾች ቤተሰቦች አጽናኝ ትምህርት ሰጥተዋል።
የወጣት ሟቹ ስመኘው አባት አቶ ዘውዱ መለሰ በጉባኤው ተገኝተው በልጃቸው ግድያ ያዘነው ልባቸው እየተደረገለት ባለው ክብር ደግሞ ሀዘናቸውን እንዳስራቸው ለጉባኤው ታዳሚዎች ተናግረዋል።
ልጄ ምንጣፍ እያነጠፈ ታቦት እየሸኘ ነው የተገደለው የልጄ ሀዘን ከልቤ ባይወጣም ለሞተበት አላማ ክብር ለመስጠት እና እኔን ለማጽናናት ለተሰበሰባችሁ ሁሉ አመሠግናለሁ ብለዋል።
ይህን ጉባኤ ያዘጋጁ የደብሩ ካህናት በበኩላቸው በዚህ ጉባኤ ሟቾችን ከመዘከር ባለፈ ለእንዲህ አይነት ዳግም ግድያ እንዳይፈጠር ምዕመናን እና ካህናት ማድረግ ስላለብን ቅድመ ጥንቃቄ ግንዛቤ ፈጥረንበታል ሲሉ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ ክፍላችን ተናግረዋል
በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ