“ከእግዚአብሔር ጋር ያልታረቀ የሕይወት ሰልፍ ውጤቱ ሽንፈት ነው” ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር ፳፩ ቀንን በዋናነት የጽዮን ቅድስት ማርያም ዓመታዊ በዓል መሆኑን በማሰብ በተለያዩ መንፈሳዊ ድንቅ ሥርዓታት ታከብረዋለች።
በዓሉ ከብሉይ እስከ ሐዲስ፣ ከታቦተ ጽዮን እስከ ድንግል ማርያም ፣ ከደብረ ሲና እስከ ሴሎ ፣ ከምርኮ እስከ ድል፣ ከደብተ ኦሪት እስከ ቤተ መቅደስ፣ ከዳዊት እስከ ቀዳማዊ ምኒልክ ፣ ከምሳሌነት እስከ አማናዊነት ፣ ከእስራኤል እስከ ኢትዮጵያ ፣ ከኢየሩሳሌም እስከ አክሱም ፣ ከነገሥታት አብርሃ ወአጽብሃ እስከ አጼ ፋሲለደስ ድረስ ሕያው ታሪክ፣ የእግዚአብሔር የማደን እጅ ድንቃድንቅ ተአምራት፣ በምሳሌ ጥላነት በትርጉም ብርሃንነት የተገለጠ ስመ ብዙ ባለታሪክ በዓል መሆኑን ሊቃውንት ይናገራሉ የታሪክ ድርሳናትም ይመሰክራሉ።
በመሆኑም ይህን ድንቅ በዓል ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ባለችበት ሁሉ ከዋዜማ ጀምሮ በማኅሌት፣ በትምህርት ወንጌል፣ በቅዳሴና ታቦታቱን ከመንበረ ክብራቸው በማውጣት “ታቦተ ሕጉ ለእግዚአብሔር በካህናት ሕፅርት ወበመንፈስ ቅዱስ ክልልት” በሚለው የቅዱስ ያሬድ ምስጋና በማጀብ በድምቀት ታከብረዋለች።
በዓሉ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በደምቀት ተከብሯል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በአጭር ደቂቃ በዓሉን አስመልክተው ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን ከእግዚአብሔር ያልታረቀ የሕይወት ሰልፍ ውጤቱ ሽንፈት መሆኑን የእሥራኤላውያን ታሪክ ዋቢ አድርገው አስተምረዋል።
ብፁዕነታቸው ሀገር የሚጠፋው ትውልድ የሚከስመው የቤተ ክርስቲያንን ተግዳሮቶች የሚበዛው ዕውቀት በጎደላቸው በአፊኒንና ፊንሐሳ ሳይሆን አዋቂ በሆነው በካህኑ ኤሊ ዝምታ መሆኑን የታቦተ ጽዮን በአማሌቃውያን እንዴት እንደተማረከች በምስክር ተርጉመዋል።
ዛሬም “#በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል ተብሎ እንደ ተጻፈ።” (ሮሜ 2፥24) በዘመናችን ታቦቱ የሚደፈረው በእኛው በደልና ኃጢአት ነው።
በመሆኑም ይላሉ ብፁዕነታቸው የሕይወታችን ሰልፍ በድል የምናጠናቅቀው፣ ትከሻችንን ካገበጠው መከራ ነጻ የምንሆነው፣ ለቅሷችን ሰሚ ጭኆታችንን አድማጭ የሚያገኘው “ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴ ፮፥፴፫) እንዲል ከመስዋዕታችን በፊት ይቅርታ፣ ከትግላችን በፊት ንስሐ ፣ ከሥራችን በፊት ጸሎት ስናስቀድም መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል ብለዋል።
ካልሆነ ግን “የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም።” (አሞጽ ፭፥፳፫) የሚለው ቃል ይፈጸምብናል በንስሐ ወደ ልባችን እንመለስ በማለት አሳስበዋል።
በዓሉ ላይ ሊቃውንቱ “#ወይቤላ ኢትሬእዩኑ ላሐ ዚአነ እንተ ረከበተነ (በእንተ ጽዮን )(፪)
ዕዝራኒ ርእያ ወተናገራ(፪) የሚለውን ያሬዳዊ ወረብ በማቅረብ አመስግነዋል።
በመቀጠልም የካቴድራሉ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን
“ሃሌ ሃሌ ሉያ ወሪድየ ብሔረ ሮሜ(፪)
ለቤተ ክርስቲያን ርኢክዋ አእምክርዋ አፍቀርክዋ ለቤተ ክርስቲያን (፪) የሚለውን ወረብ በጥሩ አቀራረብ አመስግነዋል።
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ የቤተ ክርስቲያኑ የምሥረታ ጊዜ በቅርብ ቢሆንም በዓይን በሚታዩት በእጅም በሚዳሰሱት በርካታ ሥራዎች ዋቢነት ምክንያት በእጅጉ የሚያስደንቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
አክውም ካቴድራሉ ባለፈው ነሐሴ 29/2017 ዓ/ም በብፁዓን አባቶች ቡራኬ ተመርቀው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትን ባለ 64 መጠመቂያ ያለው ቤተ ሳይዳ የጸበል ቦታ ፣ የሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ ደረጃውን የጠበቀ የአስተዳደር ቢሮ እንዲሁም የአዳራሽ፣ የመማሪያ፣ የሚዲያ፣ የጥበብና ኪነጥበብ ሞያ ማስፋፊያ፣ የራስ አገዝ ልማትን ሁሉ ያጠቃለለው የሰንበት ትምህርት ቤት ሁለገብ ሕንጻ በማስታወስ ካቴድራሉ በምንነ ዓይነት የዘመነ አሠራርና ተግበራ ላይ እንዳለ አስታውሰዋል።
በአሁኑ ሰዓትም የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ክብር የጠበቁ የመግቢያ በሮች እንዲሁም የግቢው ወለል ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸው በዚህ ሁሉ ሥራ ለተባበሩት ለሁሉም አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ቃለ በረከትና ቡራኬና የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።
በበዓሉ ላይ ከብፁዕነታቸው ጋር መጋቤ ሃይማኖት አባ አብርሃም ገረመው የቅዱስ ሲኖዶስ ምክትል ጸሐፊና የሰሜን አፍሪካ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ መጋቤ ስብሐት ዐቢይ ዘለቀ የብፁዕነታቸው ልዩ ጸሐፊ፣ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ተወካዮች ፣ የካቴድራሉ የሰበካ ጉባኤ አባላት ፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እጅግ በርካታ ምእመናንንና ምእመናት ተገኝተዋል።
የወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት የእናትነት ፍቅር አማላጅነት አይለየን።