ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተሰጠ የኃዘን መግለጫ

መስከረም 21 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡45 በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በአረርቲ ከተማ በምትገኘው የደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ዓመታዊውን የቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል በማክበርና አዲስ እየተሠራ ያለውን ሕንጻ ቤተክርስቲያን በመጎብኘት ላይ የነበሩ ወገኖቻችን የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ርብራብ ተደርምሶ ሕይወታቸው በማለፉና የአካል ጉዳት በመድረሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተሰማው ኃዘን ጥልቅ ነው፡፡
ምንም እንኳን የምንወዳቸው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ባልተጠበቀ ሁኔታ በሥጋ ከእኛ መለየታቸው የሚያስደነግጥና የሚያሳዝን ቢሆንም ከሞተ ሥጋ አስቀድሞ በሚኖረው ሕይወተ ዓለም ኅሊናቸውን ለእግዚአብሔር ዙፋን አድርገው በቤቱ የኖሩት ሁሉ በሥጋቸው ቢሞቱም ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን እንደሌለው ስናስብ እንጽናናለን፡፡
በመሆኑም በቤተ መቅደሱ እያመለኩ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በዓል ለነሢአ በረከት እያከበሩ ባሉበት በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ከመካከላችን ያጣናቸው ወገኖቻችን ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንደነገረን ከድካማቸው አርፈው ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም የሚነግሡ መሆናቸውን ያለ ጥርጥር እናምናለን፡፡(ራእይ 20.6)
በመጨረሻም በአደጋው ምክንያት ለሞቱት ወገኖቻችን እግዚአብሔር አምላክ ዕረፍተ ነፍስን እንዲሰጣቸው ፤ለቤተሰቦቻቸው ሁሉ መጽናናቱን እንዲያድላቸው እና አካላዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችንም ፍጹም ፈውስን ሰጥቶ ወደ ተሟላ ጤንነታቸው እንዲመልስልን እንመኛለን፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
መስከረም 21 ቀን 2018 ዓ/ም
አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ