“ከአሁን በኋላ ከውጪ ሆናችሁ ሳይሆን ከውስጥ ሆናችሁ አስቀድሱ” ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ
የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ “ከአሁን በኋላ ከውጪ ሆናችሁ ሳይሆን ከውስጥ ሆናችሁ አስቀድሱ” በማለት መልእክት አስተላለፉ።
ብፁዕነታቸው መልእክቱን ያስተላለፉት በቀን 6/09/2013 ዓ.ም አዲስ ተገንብቶ የተጠናቀቀውን የኮልፌ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን በጸሎት ከባረኩ በኋላ ነው።
ግዙፍ የሆነው ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በጸሎት ስለተባረከ ከአሁን በኋላ በውጪ ቆማችሁ አታስቀድሱ፣ እንደመቃኞው ጠባብ ስላልሆነ ውስጥ ገብታችሁ አስቀድሱ፣ ለሁላችሁም ይበቃል፣ ወንጌልን ተማሩ፣ ሥጋውና ደሙን ተቀበሉ በማለት ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ የተሠራበትን ዓላማ ለአከባቢው ምእመናን አብራርተዋል።
ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን በኅብረት በመሆን ለሠሩት ለማኅበረ ካህናቱ፣ ለሕንጻ አሠሪ ኮሚቴው፣ ለሰበካ ጉባኤው፣ ለባለሙያዎችና ለምእመናን በሙሉ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
ቤተክርስቲያኑም ከዛሬ ጀምሮ በካቴድራል ማዕረግ እንዲጠራ ብፁዕነታቸው ፈቅደዋል።
ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ለመጠናቀቅ ድፍን አስር ዓመታትን የፈጀ ስለመሆኑም ከመድረኩ ተብራርቷል።
በአባቶችና በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ ዝማሬና ምስጋና ለእግዚአብሔር ቀርቧል።
በመርሐግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የሀገረስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ የሀገረ ስብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ፣ መልአከ ምሕረት በቃሉ ወርቅነህ የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መ/ብርሃን አባ ኤፍሬም ገዳም (ቆሞስ)፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የደብሩ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ