“ከሰው የሚጠበቀው ማመንና መታዘዝ ነው” ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ 24 በሚባለው አካባቢ በሚገኘው በምዕራፈ ሰማዕታት ቅዱስ ገብርኤልና አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡
የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ክብረ በዓሉን የተመለከተ ትምህርት አስተላልፈዋል።
የሕጻን ቅዱስ ቂርቆስንና የእናቱን የቅድስት እየሉጣን የእምነት ጽናት አብራርተዋል።
በሕይወታቸውና በልባቸው ውስጥ ሰማያዊውን ንጉሥ ስላነገሡ ምድራዊው ንጉሥ በወታደሮቹ ያስጣደውን የፈላ የጋን ውኃና እንደ ክረምት ነጎድጎድ የሚጮኸውን ድምጽ አልፈሩም ብለዋል።
ለንጉሡ ጣዖት ባለመስገድም ፈጣሪያቸውን እግዚአብሔርን አክብረዋል ሲሉ ገልጸዋል።
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ በመምጣት ፈጣን ተራዳኢ መልአክ መሆኑን አብራርተዋል።
እግዚአብሔር እውነተኛና የታመነ አምላክ ስለሆነ በእርሱ የሚታመኑትን ዘወትር ከክፉ ነገር ይጠብቃቸዋል ብለዋል።
አያይዘውም “ከሰው የሚጠበቀው ማመንና መታዘዝ ነው” ሲሉም አጽንዖት ሰጥተዋል።
በቅዱስ ቂርቆስና በቅድስት ኢየሉጣ ሕይወትም የተመለከትነው ይህንኑ እውነት ነው ሲሉ አብራርተዋል።
እንደ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ በእግዚአብሔርና በሰዎች ፊት በጽኑ እምነት መመላለስ አለብን ብለዋል።
በዚህ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ቂርቆስንና የቅድስት ኢየሉጣን ክብረ በዓል ብቻ ሳይሆን የሁለት ወንድሞች ሰማዕትነትን ጭምር ነው የምናከብረው በማለትም ገልጸዋል።
በሕይወታችን ላይ ሰው ሰራሽ የሆነውን ጣዖት ሳይሆን ሕያው የሆነውን እግዚአብሔርን በማንገሥ፣ በማምለክና ለእርሱ በመታመን በጽድቅና በቅድስና ሕይወት በመኖር ለተፈጠርንለት ዓላማ ልንኖር ይገባል ብለዋል።
እንደ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ መከራንና ፈተናን በመታገስና በጽናት በማለፍ የእምነት አርበኞች ልንሆን ይገባል ሲሉም አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው ቤተክርስቲያኑ ሊያሠራ ላቀደው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ በአባቶችና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል።
ቤተክርስቲያኑም የካርታ ይዞታን ስለማግኘቱ ለምእመናን በመድረኩ ላይ ይፋ ተደርጓል።
መልአከ ምሕረት አምሐ መኳንንት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዕቅድና ልማት ዋና ክፍል ኃላፊ የካርታ ይዞታውን አስመልክተው የብፅዕነታቸውን ጠንካራ አመራር ገልጸዋል።
በደብሩ የሚገኙ ወጣቶችም የካርታው ይዞታ እስኪሰጥ ድረስ ያላለሰለሰ ጥረት ማድረጋቸውን አውስተዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብስራት አብርሃም ዲበኩሉ ወደ ደብሩ ተመድበው ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ከሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር በመሆን ያከናወኗቸውን የአራት ወራት የሥራ ሪፖርትና ለወደፊት ሊሠሩ የታቀዱ ዕቅዶችን ገልጸዋል።
የካህናት ወራዊ ደሞዝ እንደተሻሻለ፣ ቤተክርስቲያኑ የካርታ ይዞታን እንዳገኘ፣ ከአከባቢው ምእመናን ጋር በጋራና በሰላም አብሮ መሥራትና ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት በኩል ሥራዎች እንደተሠሩ ከሪፖርቱ ተደምጧል።
በልማት ሥራና በተለያዩ አገልግሎት ለቤተክርስቲያኑ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
ሊሠራ ለታሰበው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በበክረ ትጉሃን ደመላሽ ቶጋ በመድረኩ ላይ የገቢ ማሰባሰቢያ ተካሄዷል።
በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብስራት አብርሃም ዲበኩሉ፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቀ መዘምራን ቴዎድሮስ ዮሴፍ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ ፦መ/ር ዋሲሁን ተሾመ