“ከሰማዕታት እውነተኛ ምስክርነትን ልንማር ያስፈልጋል” ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

ዓመታዊው የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ  ክብረ በዓል በጉራጌ ሀገረ ስብከት በአትርፎ ደብረ ወርቅ  ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል  በድምቀት ታስቦ ውሏል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበዓሉ ላይ ተገኝተው “ከሰማዕታት እውነተኛ ምስክርነትን ልንማር ያስፈልጋል” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

እውነተኛ ምስክርነት የሰማዕታት የዕለት ተዕለት ተግባር እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የሰው ልጆች በሙሉ የፈጠራቸውን እና ከዘለዓለም ሞት የታደጋቸውን አምላካቸውን እንዲያውቁ እና እንዲያምኑ ማስተማር፤ ከጣዖት እና ከሐሰት እንዲጠበቁ ማድረግ የእውነተኛ ምስክርነት መገለጫዎች እንደሆኑ አብራርተዋል።

ሰማዕትነት ራስን ለመድኃኔዓለም አሳልፎ በመስጠት እውነተኛ  አገልግሎትን ማገልገል ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ሰማዕታት የዚህ ምድር ተድላ ሳያታልላቸው ለመለኮታዊው ሃሳብ በመቆሞ እና ሐሰትን በመቃወም መከራን የተቀበሉ ናቸው ብለዋል።

አያይዘውም ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በከሀዲዎች ነገሥታት ፊት ምንም ሳይፈራ እውነትን በመመስከር ለፈጠረው እና ላዳነው ጌታ  በመታመን ሰማዕትነትን እንደተቀበለ አስተምረዋል።

እኛም  የሰማዕታትን በዓል ማክበር ብቻ ሳይሆን ዘወትር በእምነት፣ በፍቅር እና በተስፋ በመመላለስ የተሰጠንን መንፈሳዊ አደራ በአግባቡ ልንወጣ ያስፈልጋል በማለት በአጽንኦት ተናግረዋል።

ያለንበት ዘመን ክፋት፣ ተንኮል እና ራስ ወዳድነት የነገሠበት መሆኑን አውቀን በደግነት እና በርኅራኄ መንፈስ በመመላለስ የሰማዕትነትን ሕይወት መኖር እንደሚገባን መክረዋል።

ሰማዕታት ወንጌልን በመስበክ ያለፍርሃት መከራን እና ስቃይን  እንዲቀበሉ ያደረጋቸው ምሥጢሩ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጣቸውን መድኃኔዓለምን ከልባቸው ማመናቸው መሆኑንም አብራርተዋል።

ይህ ዓለም ጊዜያዊ እና ኃላፊ መሆኑን ተረድተን ለሰማያዊው ሕይወት ቅድሚያ በመስጠት ቃሉ በሚያዘን መሠረት በንስሐ ሕይወት ልንኖር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ብፁዕነታቸው በካቴድራሉ ግቢ ውስጥ ሊሠራ ለታቀደው 40 ሜትር ከፍታ ላለው መስቀል የመሠረት ድንጋይ ጥለዋል።

ይህም በዞኑ የመስቀል በዓልን ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ መልኩ በአንድነት ተሰባስቦ እና  መንፈሳዊ ትርጉሙን በመረዳት ለማክበር እንደሚጠቅም ገልጸዋል።

ሊሠራ የታሰበው መስቀልም 10 ሚሊየን 2 መቶ ሺህ እንደሚፈጅ ተጠቅሷል።

ብፁዕነታቸው ለ 600 ዲያቆናት እና ለ20 ካህናት  ሥልጣነ ክህነትን ሰጥተዋል።

በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ:-
1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
4. ትዊተር :-www.Twitter.com/AddisDiocese