“ከምክርቤት እስከ መምሪያ” የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መዋቅር

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ኅዙናን ገዳም የበላይ ኀላፊ፣ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፣ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ እና የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ የበላይ ኀላፊ
ክቡር ንቡ እድ ኤልያስ አብርሃ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህነት ጽ/ቤት መንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ
ክቡር ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ግርማ ባቱ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህነት ጽ/ቤት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ
ክቡራን የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኀላፊዎች እና የየድርጅቱ ሥራ አስኪያጆች
ክቡራን የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች
የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ “መሪነትና ተልእኮአችን” በሚል ርእስ ላዘጋጀው የምክክርና የውይይት መድረክ ለመሳተፍ እንኳን ደኅና መጣችሁ እያልሁ መድረኩ የተዘጋጀበትን ዓላማና ምክንያት እንዳቀርብ ስለተፈቀደልኝና እግዚአብሔርም ይህን እድል ስለሰጠኝ ክብር ምስጋና ይድረሰው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ነጻ መውጣቷን ተከትሎ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ሊቀመንበርነት፣ በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የጉባኤመሪነት፣በ14 ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና በተመረጡ ካህናትና ምዕመናን አባልነት የመጀመሪያው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ምክር ቤት በ1952 ዓ.ም ተቋቋመ።
ማስፋፊያ ምክር ቤቱ በዓመት ሁለት ጊዜ ጉባኤ ከማድረጉም ባሻገር የ1% ወርኃዊ መወጮን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን በመሥራቱ የቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ቅዱስ ወንጌልን ማስፋፋት መሆኑን አረጋግጦ ነበር።
የቤተክህነቱ አስተዳደር እየሰፋና እየጠነከረ ሲመጣ ከማስፋፊያ ምክር ቤት ወደ መምሪያነት የመጣው የስብከተ ወንጌል መምሪያ ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያን ጨምሮ ሌሎች መምሪያዎችን ቢወልድም የነበረው ትልቅ ትኩረት እየተነፈገ መምጣቱን ብዙዎችይመሰክራሉ።
ይህንን ክፍተት የተመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 2017 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ምልዓተ ጉባኤ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ራሱን ችሎ የሚመራው በጀት ፈቅዶለት ራሱን በራሱ በበጀት እንዲመራ ያሳለፈውን ውሳኔ መምሪያው ተግባራዊ ለማድረግ የ1% ወርኃዊ መዋጮን በአግባቡ መሰብሰብንጨምሮ በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
መምሪያው በሥሩ የሚገኙ ሰባክያንና ልዩ ልዩ ሠራተኞች በተደጋጋሚ ከማወያየትና የሐሳብ አንድነት ከመፍጠር ጀምሮ አስፈላጊ የጽ/ቤት የሥራ መሣሪያዎችን ማሟላት፣ ዘርፉን በተጨማሪ የሰው ኃይል ማደራጀት እና በድጋፍ/በስፖንሰር/ በተገኘ ገንዘብ የቢሮ ማስተካከል ሥራዎችን በአጭር ጊዜ አከናውኗል።
በ1984 ዓ.ም ተዘጋጅቶ እና ጸድቆ ሥራ ላይ በዋለው የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ጽ/ቤት መተዳደሪያ ደንብ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያን የተመለከተውን አደረጃጀት መነሻ በማድረግ ዘመኑን የዋጀና የትውልዱን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ አዲስ አደረጃጀት አዘጋጅቶ በማቅረብ ጸድቆ ሥራ ላይ የሚውልበትን ሂደት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ከዚህም በተጨማሪ የወንጌል አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት እና የሚዲያ ቴክኖሎጅ ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ ማኅበራዊ ሚዲያ የማስጀመር እና ድህረ ገፅ የማበልጸግ ሥራ እንዲሁም ለመምሪያው ሰባክያንና ልዩ ልዩ ሠራተኞች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መጠነኛ ቤተመጻሕፍት ማደራጀት በዋናነት በትኩረት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ናቸው።
በሌላ መልኩ መምሪያው የያዘውን የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ በሚጠበቀው ልክ ተግባራዊ ለማድረግና የቀድሞውን የመምሪያውን ክብር ለመመለስ ከሁሉም የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክርና ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ የውይይትና የምክክር መደረክ ሊዘጋጅ ችሏል፡፡ ይህ የውይይትና የምክክር መድረክ ሲዘጋጅ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተደራሽነትና ውጤታማነት እንቅፋት የሆኑ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች ተብለው በተወሰነ መልኩ በተለያዩ ጥናቶች የተገለጡ ችግሮችን በተመለከተ ለመወያየትና መፍትሔ ለማስቀመጥ ነው፡፡
ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች
ውስጣዊ ችግሮች
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጥራትና በብዛት የሠለጠኑ የወንጌል አገልጋዮች አለመኖር
እርስ በርስ ኅብረት ፈጥሮ አለመንቀሳቀስ
የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን በከተሞች ብቻ ማተኰር
ወጥነት ያለው በእስትራቴጂክ ዕቅድ የሚመራ የስብከተ ወንል አገልግሎት አለመስጠት
የሰባክያነ ወንጌል የሕይወት መሰጠትና ቅድስና ማጣት ( ለምሳሌ፣ የሞራል ውድቀትና የሚናገሩትን አለመፈጸም )
የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት እንደ ገንዘብ ምንጭ አድርጎ መጠቀምና የእግዚአብሔርን ሐሣብ ከማገልገል ይልቅ በቁሳዊ ጥቅም ላይ ማተኰር
ሰባክያነ ወንጌል የተሰጠን የማስተማር ኃላፊነት ከእንጀራ በላይ መሆኑን መዘንጋት ወይም ተገቢውን ትኵረት አለመስጠት
በሀገራችን የሚታየውን መንፈሳዊ፣ማኅበራዊ፣ ፓለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ጥናቶችን አለማድረግ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ መድረክ ያላት ቢሆንም ይህን በአግባቡ አለመጠቀም ፡፡
ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ የሆነው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች አንጻር ሲታይ በዝቅተኛ ደረጃ መገኘቱ
ያመኑትን እያጸኑ ከማገልገል ባለፈ ላላመኑት የክርስቶስን ወንጌል ለማስተማር ብርቱ ጥረት አለማድረግ
በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚስተምሩ፣የሚቀድሱ የማስተማርያ መጽሐፍትን የሚያዘጋጁ አገልጋዮችን በሚፈለገው ደረጃ አለማፍራት
ስብከታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ሥራ ማእከል የሚያደርግ፣ የሰውንም ሕይወት በሁለንተናዊ መልኩ የሚለውጥ ይዘት ያለው አለመሆኑ
ሕዝባችን በቀላሉ ሊረዳው በሚችል ቋንቋ ወንጌልን አለመስበክ
በዐውደ ምሕረት ወንጌልን ከመስበክ ይልቅ ራስን መስበክ (ውዳሴ ከንቱ ፣ ግብዝነት ወዘተ ………..)
በበዓላት ጊዜ ለሚመጣው ሕዝብ ተገቢውን የወንጌል አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ሰፊውን ጊዜ ለልመና መስጠት
ማኅበራዊ ሚዲያውን በአግባቡና በሚፈለገው ልክ አለመጠቀም
ያለ ቤተክርስቲን ፈቃድ ሳይማሩ ተምረናል ሳይላኩ ተልከናል የሚሉ አጉራ ዘለል ሰባክያን ነን የሚሉ መኖራቸው
ወጥነት ያለው ምእመናንን ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ተከታታይ ትምህርት አለመስጠት
በተለያዩ አድባራት የሚሰጠውን የሰርክ ጉባኤ ክትትል አለማድረግና አለመቆጣጠር
ጊዜውን የሚዋጅ ተከታታይ የሆኑ ስልጠናዎችን ለሰባክያነ ወንጌል በበቂ ሁኔታ አለመስጠት
አገልጋዮችን በጸጋቸው ተለይተው ተፈትነውና ተመዝነው ሳይረጋገጥ ወደ ስብከተ ወንጌል አገልግሎት በቅጥርም ሆነ በዝውውር መድቦ ማሠራት
አንዳንድ የቤተክርስቲያን አስተዳደር አካላት በደብራቸው ከሚገኙ ሰባክያነ ወንጌል ጋር ሳይመካከሩ በጣልቃ ገብነት አገልጋዮችን መጋበዝ
ለስብከተ ወንጌል በቂ የሆነ በጀት አለመመደብ፣
የአብነት ትምህርት ቤቶች መዳከም፣
የመልካም አስተዳደር መጥፋትና የብልሹ አሠራር መስፋፋት ለወንጌል ስብከት እንቅፋት መሆን፣
ጠንካራ የትሩፋት አገልጋዮችን በእግድ ከመድረክ ማግለል
ችግር ፈቺ የሆነውን የማማከር አገልግሎት ከወንጌል አገልግሎት ጋር አጣምሮ አለመስጠት፣
በተለይ በከተማ አካባቢ በአንድ ቦታ ላይ ብዙ ሰባብያነ ውንጌል የተከማቹ መሆኑና የአገልግሎቱ ስብጥር ለሌሎች ተደራሽ እንዳይሆን ማድረግ፣
ለሕዝቡ የሚመጥኑ ሰባክያነ ወንጌልን ከመጋበዝ ይልቅ በመቀራረብ በጓደኝነት የአገልግሎት ግብዣ ማድረግ
ውጫዊ ችግሮች
የድኅረ ዘመናዊነት ፍልስፍና እውነትን አንጻራዊ አድርጎ ያቀረበበት መንገድ ፍጹም እውነት የሆነውን ወንጌልን ሰዎች በአንጻራዊ እውነትነት እንዲያዩ ማድረግ
የሉላዊነት መስፋፋት፣ ይህንም ተከትሎ የሰው ልጆች በባእዳን ባህል ወረራ ውስጥ መውደቃቸው
የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊትና ታሪክ የማያውቁ በማኅበራዊ ሚዲያ ለማስተማር መነሣታቸውና እነርሱንም ተቈጣጥሮ ሥርዐት ማስያዝና በአግባቡ እንዲያገለግሉ የሚያደርግ አሠራር እስከ ዛሬ አለመዘርጋቱ
ከቤተ-ክርስቲያን ተወግዘውም ሆነ ሳይወገዙ የወጡ የመነኩሴ፣ የሰባኪ ቀሚስ በመልበስ ኦርቶዶክሳዊ ሳይሆኑ በመምሰል አማኞችን ማታለላቸውና የመከላከል ሥራው በበቂ ደረጃ አለመሠራቱ
የአጽራረ ቤተ-ክርስቲያን ድጋፍ (በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር የሚገኙ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ጠላቶች የመናፍቃንን እንቅስቃሴ በሥልጠና፣ በፋይናንስ እና በዲፕሎማሲ መደገፍ
የቋንቋ ተግዳሮት (በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚያስተምሩ፣ የሚቀድሱና የሚያገለግሉ አገልጋዮችን አለማፍራት)
ማኅበራዊ የአስተሳሰብ ተግዳሮቶች (የቤተሰብ፣ የልጆች አስተዳደግ፣ የሥራ፣ የጾታ፣ የህክምና፣ የአወላለድ ወዘተ ሁኔታ እየተቀየሩ አዳዲስ ጥያቄዎች መፈጠራቸው)
የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ግቦችና ዓላማዎች
የቤተ ክርስቲያናችን ዋና ዓላማና ግብ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋትና በማጠናከር በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ምእመናንን ማብዛት፣ ሁሉን ተደራሽ ያደረገ እና ዘመኑን የዋጀ ስብከተ ወንጌል ፤ትምህርት እና ሐዋርያዊ ተልእኮን ማስፋፋት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሠረት በሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ በቃለ ዐዋዲና በቤተ ክርስቲያናችን ሕጎችና እቅዶች የተቀመጡ ዓላማዎችን መነሻ በማድረግ መምሪያው የሚከተሉትን ዓላማዎች ለማሳካት በትጋት እየሠራ ይገኛል፡፡
ስብከተ ወንጌል ባልተስፋፋባቸው እና አብያተ ክርስቲያናት በሌሉባቸው የገጠር እና ጠረፋማ አካባቢዎች የስብከተ ወንጌልና የሐዋርያዊ ተልእኮን ማስፋፋት፣ የስብከተ ወንጌልን ተደራሽነት በከተማና በገጠር እንዲሁም በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ማስፋፋት፣ ጥራትና ውጤቱን መከታተልና አፈጻጸሙን በየጊዜው መገምገም፣ ስብከተ ወንጌል በተዳረሰባቸው ቦታዎች አገልግሎቱ የተሻለ ጥልቀትና ጥራት እንዲኖረው መሥራት እንዲቻል አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ
የቋንቋ ብዙኅነትን በመጠቀም፤ ሁሉም አህጉረ ስብከት በሥራቸው በሚነገሩ ቋንቋዎች ሊያስተምሩ የሚችሉ አገልጋዮችን ማፍራያ የሚያስችል የትምህርት እና ሥልጠና ማእከል እንዲከፍቱና ሰባክያነ ወንጌልን እንዲያሠለጥኑ ማድረግና መደገፍ
ሕዝባዊ ጉባኤያት ኦርቶዶክሳዊ ሥርዐታቸውን ጠብቀው በስፋት እና በምልአት እንዲስፋፉ እና ሁሉን ተደራሽ ያደረጉ እንዲሆኑ ማድረግ
ወንጌልን ለምእመናን በመስበክ የምእመናንን መንፈሳዊ ሕይወት መጠበቅና በልዩ ልዩ ችግሮች እያዘኑ ያሉ ምእመናንን ማጽናናት
በየደረጃው በማገልገል ላይ የሚገኙ ሰባክያነ ወንጌልን ማሰልጠንና ዕውቀትና ችሎታቸውን በማዳበር የስብከተ ወንጌል ተልእኮን በተሻለ ዐቅም እንዲወጡ ማድረግ በየደረጃው ባለው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚታዩ ችግሮችንና መልካም ተግባራትን በመገምገም የስብከተ ወንጌል መዋቅርንና አሠራሩን ማጠናከር የዕቅበተ እምነት ሥራዎችን መሥራትና አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን መከላከል ለአብነት መምህራንና ለተማሪዎች የስብከት ዘዴን እና መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርትን በዘመናዊ መንገድ በማስተማር ለስብከተ ወንጌል ተልእኮ ማዘጋጀትና ማሰማራት፣ እንዲህም ካህናትን፣ የሰ/ት/ቤት አባላት ወጣቶችንና ምእመናን በማሠልጠን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ባለቤቶችና ባለድርሻ አካላት መሆናቸውን በተገቢው እንዲረዱት ማድረግና በአገልግሎት ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ ፣ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና አገልግሎቶች ከስብከተ ወንጌል ጋር የተሳሰሩ ስለሆኑ ይህን የአገልግሎት ትስስር በማጠናከር ስብከተ ወንጌልን በጋራ የማስፋፋት ልምድን ማዳበርና ማጠናከር ሁሉም ካህናትና ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለስብከተ ወንጌል ማጠናከሪያ እንዲውል በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን የ1% (አንድ በመቶ) ክፍያ እንዲከፍሉና በአግባቡ እንዲሰበስቡ ማድረግ ፣ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በሚዲያ ምእመናንን በማስተባበር ለስብከተ ወንጌል የሚያስፈልገውን የገንዘብ ዐቅም ማሰባሰብ ናቸው፡፡
ከጠ/ቤ/ክህነት እስከ አጥቢያ ባለው መዋቅር የስብከተ ወንጌል አሠራር ተናብቦ እንዲሠራና አገልግሎቱ እንዲጠናከር ማድረግ፣
ስብከተ ወንጌልን የሚመለከቱ የሕግ፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ክፍተቶችን በማጥናት መገምገምና ተወያይቶ የውሳኔ ዐሳቦችን ለሚመለከተው አካል በማቅረብ አፈጻጸማቸውን መከታተል፣
ለስብከተ ወንጌል ተልእኮ መሳካት ወሳኝ ሚናን የሚወጡ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መሪዎችን ማፍራትና ማብቃት፣
በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚርቁትንና የሚወጡትን ምእመናን መጠበቅ፣ የወጡትን (የጠፉትን) መፈለግና የራቁትን ማቅረብ፣
በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተሰማርተው የሚገኙ ሁሉም ሰባክያነ ወንጌል መዋቅር ጠብቀው የማገልገልና የማስገልገል አስፈላጊነትን በተመለከተ መወያየት፣ ችግሮችን መለየትና የመፍትሔ ዐሳቦችን ማስቀመጥ፣
የአገልጋዮችን አቅምና ብዛት ለይቶ በመመዝገብ ማሳወቅ እንዲቻል የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከር፣
በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቋንቋዎች የተለያዩ ኅትመት እና ትርጉም ሥራዎችን መሥራት፣
ስብከተ ወንጌልን በመደበኛ እና በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ማስፋፋት የሚሉ ዝርዝር ዓላማዎችን ይዞ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋትና በከፍተኛ ተነሣሽነት እየሠራ ይገኛል፡፡
የውይይት መድረኩን ማዘጋጀት ያስፈለገባቸው ምክንያቶች
ይህን የውይይትና የምክክር መድረክ ማዘጋጀት ያስፈለገባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
የተቀመጡ ግቦች፣ የተያዙ እቅዶችና ዓላማዎች የሚፈጸሙት በዋናነት በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ መሪነትና አስተባባሪነት ፣ በአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች የሥራ አስፈጻሚነት እንደሆነ ይታወቃል፤ አህጉረ ስብከት ከመምሪያው ጋር ተናበው በጥምረት የመሥራት ልምድን ከአሁን በፊት ከነበረው በተሻለ መልኩ ማጠናከርና ማስፋት ያስፈልጋል፤ የስብከተ ወንጌል ተደራሽነት በሁሉም ስፍራ የሚዳረሰው በዋናነት በሥራ አስኪያጆች የሥራ መሪነትና አስፈጻሚነት ነውና የተያዙ ግቦችን፣ እቅዶችንና ዓላማዎችን በውይይትና በምክክር ማስረጽና የጋራ ግንዛቤ መያዝ የዚህ መድረክ አንድ ዓላማ ነው፡፡ የሥራና የአገልግሎት ጤታማነትን ከፍ ለማድረግ በቀጣይ በመምሪያው በኩል በሚደረጉት የአገልግሎት ሥምሪቶች ዙሪያ ተመካክሮ የጋራ ተግባቦት ላይ መድረስና የጋራ አቅጣጫ መስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይህ ጉባኤ ሊጠራ ችሏል፡፡
በዚህ መድረክ የሚቀርቡ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች አሉ፤ አንደኛው “የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትና አስፈላጊነት” የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “መሪነትና ተልእኮአችን” የሚል ነው፤ እነዚህ ርእሶች የተመረጡት የስብከተ ወንጌልን አስፈላጊነት በማወቅ ተደራሽነትን የማረጋገጥ ኀላፊነት ያለባቸው የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች በመነሣት በሥራ ልምድ ያገኙትን ዕውቀትና ጥበብ በውይይትና በምክክር በማዳበር የጋራ ግንዛቤና አቅጣጫ ይዘን ስብከተ ወንጌል ለሁሉም በገጠርና በከተማ እንዲሁም በሁሉም ቋንቋዎች ተደራሽ ይሆን ዘንድ የመሪነት ድርሻችሁን እንድትወጡ ለማሳሰብ፣ የጋራ ተግባቦትና የውሳኔ ዐሳብ ላይ ለመድረስና ወደ ተግባር ለመግባት ነው፡፡
እግዚአብሔር ዐሳባችን ያስፈጽመን!!!
የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ይድረሰኝ!!!
……..
መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ
የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሐላፊ