“እግዚአብሔርን አምኖ መኖር ሕይወታችን ባቢሎን እንዳይሆን የሚጠብቅ የልብ ማረፊያ በመሆኑ እርሱን በማመን ልጸና ይገባል። ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ

እግዚአብሔርን አምኖ መኖር ሕይወታችን ባቢሎን እንዳይሆን የሚጠብቅ የልብ ማረፊያ በመሆኑ በእንምነት ልጸና ይገባል በማለት ብፀለዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።
ብፁዕነታቸው ይህንን ያሉት የቅድስት ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በዛሬው ዕለት በተከበረበት በዓል ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓላት የምታከብርባቸው መሠረታዊ ጉዳይ ከመዳን ጋር ግንኙነት ባለው መልኩ እንደሆነ ታስተምራለች።
እርሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ” እኔ እሕይወት እንዲሆንላቸውና እንዲበዛላቸው መጣሁ “(ዮሐ.10:11) እንዳለው የእርሱ ስም በሚጠራበት ምስጋናው በሚቀርብት የንስሐ አዋጅ በሚነገርበት ቦታና አገልግሎት ለዘለዓለም ሕይወት ጥቅምና ረብ ይሆን ዘንድ ሕይወት_እንዲሆንልን_እንዲበዛልን በዓላትን እናከብራልን።
በዚህ መነሻነት የዛሬው የጥር ፯ ቀን በዓል የእግዚአብሔር ክብሩ የታወጀበት እግዚአብሔርን የመፈተን፣ ያለማመምንና ያለማወቅ ሥራ የፈረሰበት ቀን በመሆኑ በኦሪት ዘፍጥረት 11:1 በሰናዖር ሜዳ የተፈጸመን ታሪክ መነሻ በማድረግ የቅድስት ሥላሴን አንድነትና ሦስትነት ይነገርበታል።
ይህ ዓመታዊ ቅድስት ሥላሴ በዓል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲከበር ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ሰብሳቢ ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የቤቶች አስተዳዳርና የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሊቀ ጳጳስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሐላፊዎች፣ ሊቀ ሥልጣና አባ ሲራክ አድማሱ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የካቴድራሉ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፣ ከቅርብና ከሩቅ የመጡ በርካታ ምእመናን ለበረከት ተገኝተዋል።
በበዓሉ ትምህርት ውንጌል የሰጡት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበበባና ሀዲያ ስለጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓሉን አስመልክተው በአጭር ደቂቃዎች ውስጥ ትምህርትና አባታዊ መልእከት አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው ስለ ቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት መሠረታዊ የእምነት ትምህርት ምእመናንን ባሳተፈ መልኩ አስተምረዋል።
አክለውም በዓሉ በናምሩድ መሪነት በሰናዖር ሜዳ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሕንጻ ሲገነቡ ቋንቋቸውን እንደባለቀባቸውና ባቢሎን እንደተባለ ተርከው በዚህም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ጫፍ በነካ ራስ ወዳድነትና እችላለሁ ባይነቶች ሁሉ መጨረሻቸው ውድቀትና ውጤት አልባ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በየዘመናቱ የሰናዖር ሜዳን ሐሳብ ይዘው የተነሱ ዕውቀት አለን ባዮች፣ ዝና አለን ባዮችና ሥልጣን አለን ባዮችን ዓመታቸው አልቆ፣ ሀብታቸውንም ሳይከተላቸው፣ ሥልጣናቸውም ጋሻ ሳይሆናቸው ቀርቶ ታሪካቸው ተዘግቷል የእግዚአብሔር መኖርና እሱንም ማመን ግን ዛሬም እስከ ዘለዓለም ድረስ የሚነገር እውነት ሆኖ ይኖራል ብለዋል ብፁዕነታቸው ።
ብፁዕነታቸው አክለውም እግዚአብሔር በማመን መጽናት በመታመንም መኖር ትርጉሙ ብዙ፣ ምስጢሩ ረቂቅና ትርፉ ክብር መሆኑን በመገንዘብ በእግዚአብሔር አምኖ ከእርሱ ጋር መኖርን የምርጫችን አውራ ልናደርገው እንደሚገባም አስተውሰዋል።
በልባችን የተመላለሰው የፍቅሩ ኮቴ በችግራችን እንባ ውስጥ መልስ የመለሰልን ጌታ ብቸኞች ነን ስንል ሳይታየን ሞገስ የሆነን አምላክ፤ ሰዎች ከበቡን መከራ በዛብን ስልን ከስካር እንደሚነቃ ሰው በሕይወት ያቆመን በቸርነት የልብ መገዛትን የሰጠን እግዚአብሔር ነው። እርሱ እግዚአብሔርን አምኖ መኖር ዓለም ከምትሰጥን ሁሉ የሚበልጥ የማይወሰድ ሽልማት፣ የማይጎድፍ ስምና የማይሻር ክብር መኖር እንደሆነ በመረዳት በእምነት ልንጸና ይገባልም ብለዋል።
በበዓሉ ላይ ካቴድራሉ ሊቃውንትና ሰንበት ትምህርት መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል።
የካቴድራል አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሲራክ አድማሱ በዓሉ ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ለአባታዊ ለቡራኬ በመገኘታቸው በእጅጉ አመስግነው ካቴድራሉ እየሠራቸው ስለሚገኙ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ አብራርተው ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ከዚሁ ጋር ካቴድራሉ በተመረቀበት ወቅት ያላለቁ ቀሪ ሥራዎች በመኖራቸው በተለይም የአብነት ትምህርት ቤትና የካቴድራሉን ግቢ ለሕያው መንፈሳዊ አገልግሎት ምቹ የማድረግ ሥራዎች እንዳሉ አስታውሰው ትብብር እንዲያደርጉ መልእክት አስተላልፈዋል።
አያይዘውም ለበዓሉ አከባበር የበኩላቸውን አስተዋጽዖና መልካም ያደረጉት ሁሉ አመስግነዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ በረከትና ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።