“እውነተኛው የዓለም ብርሃን”
በመምህር ኪዱ ዜናዊ
ብርሃን÷ ብርሃን የጨለማ ተቃራኒ ነው፤ ለዚያም ነው ብርሃን የሌለበት ጨለማ ተብሎ የሚጠራው። ጨለማ መኖሩ የሚታወቀው ብርሃን ሳይኖር ሲቀር ነው። ብርሃን በሁለት መልኩ ልንገልጸው እንችላለን÷ ውጫዊ(ዓለማዊ) እና መንፈሳዊ(ውስጣዊ)፤ የመጀመርያው ከተፈጥሮአዊው(ፀሐይ) ወይም ከሰው ሰራሽ የሚገኝ ሲሆን ያንን ብርሃን ወደ ዓይናችን ሲያንጸባርቅ ነገሮችን ማየት እንችላለን፤ ዓይናችን ያ ብርሃን ካላገኘ ግን ጨለማ ነው ምንም ማየት አይችልም። ሁለተኛው ግን ከመጀመርያው በእጅጉ የተለየ የረቀቀ ብርሃን ነው÷ መንፈሳዊ ብርሃን፤ ውስጣዊ ብርሃን። እግዚአብሔር መንፈስም ብርሃንም ነው(ዮሐ 4:24፤ 1ዮሐ 1:5) እግዚአብሔር በአማኞቹ ልብም ያበራል፤ እንዲህ ስንል ግን በመካከላቸው የሚጋርድ ነገር(ኃጢአት) ከሌለ ነው። ምክንያቱም አምላክ ኃጢአትን ይጸየፋልና።
እንደ ቤተ- ክርስቲያናችን ሥርዓትና ቀኖና ከገና በፊት ያሉት ሦስት ሰናብት ማለትም ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ አንድላይ ዘመነ ስብከት ተብለው ይጠራሉ፡፡ የዘመነ ስብከት ሁለተኛ እሁድ ብርሃን ይባላል።ሌሊቱን ከቅዱስ ያሬድ መዝሙር «አቅዲሙ ነገረ በኦሪት» በኦሪት መናገርን አስቀደመ ብለው በመጀመር በሊቃውንቱ ሲዘመር በዜማ አምላክን ሲወደስና ሲመሰገን ካደረ በኋላ ጧት ደግሞ በሥርዓተ ቅዳሴ (ሮሜ.13፥11-ፍጻሜ)፣ (1ዮሐ.1፥1-ፍጻሜ)፣ (የሐዋ.26፥12-19) በዲያቆናት እና በካህናት ይነበባሉ። (መዝ.42፥3) በዲያቆኑ በዜማ ይቀርባል፡፡ (ዮሐ.1፥1-19) በካህኑ ይነበባል እንዲሁም የሊቁ የአትናቴዎስ የምስጋና ጸሎት ይደርሳል ፡፡ እነዚህም ሁሉ ስለ ብርሃኑ ሰፋ ያለ መልእክት ያላቸው ከብሉያትና ከሐዲሳት እንዲሁም ከሊቃውንቱ መጻሕፍት የተውጣጡ ብርሃንነቱን የሚመሰክሩ ናቸው ፡፡
ይህ ሳምንት ብርሃን ተብሎ መጠራቱ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበሩ ሰዎች በመንፈሳዊ ጨለማ ተውጠው ይህንን ጨለማ የሚያስወግድ መንፈሳዊ ብርሃን በመሻት አምላክን ሲማጸኑት እንደነበሩ ለማዘከር፤ በአሁን ሰዓት ያሉ አማንያንም ብርሃን መጥቶ ጨለማን በማስወገድ ስለታደጋቸው ለማመስገን ላላመኑትና ላላወቁት ደግሞ <እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ> እንዳለው በዓለም ውስጥ ብርሃን ሆኖው ብርሃኑን እያመሰገኑ ያ ብርሃን መግለጥና ለዓለም ሁሉ መስበክ ነው።
ቅዱሳን ነቢያት ሰው ሁሉ በጨለማ ውስጥ መሆኑን (መኖሩን) አውቀው ተረድተው ይህንን ጨለማ ለማስወገድ ደግሞ ብርሃን እንደሚያስፈልግ በማመን የብርሃን ባለቤት ለሆኖው አምላካችንን ብርሃን እንዲልክላቸው የዘወትር ልመናቸውና ጸሎታቸው እንደነበረና የነፍሳቸውን ብርሃን ይመጣል ብለው መስበካቸውን ከጽሑፋቸው አይተን እንረዳለን፤ ለሰው ልጅ ድኅነት ከጠበቁባቸው እና ከገለጡባቸው መንገዶችም አንዱ ይህንን ብርሃን እንዲላክላቸው ነበር፡፡ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በዘመነ ብሉይ÷ ደዌ-ሥጋ፣ ደዌ- ነፍስ የፀናበት፣ ለሰው ሁሉ አስጨናቂ ዘመን የሆነበት፣ሁሉም ሰው ብርሃን ከሆነው አምላኩ ርቆ በጭንቅ፣ በመከራና በጨለማ ውስጥ በመኖሩ ተስፋ ቢስ ሆኖ ስለነበር ዘመኑን « ዘመነ-ጨለማ» ብለው በመግለጥ ይህንን ጨለማ አስወግዶ ወደ ብርሃን የሚቀይር በጨለማ የሚያበራ ብርሃን እንዲላክላቸውና ከብርሃን የተገኘ እውነተኛ ብርሃን፤አማናዊ ብርሃን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመጣ ዘወትር ሲጸልዩ ነበር፡፡ መዝሙረኛውም ያን ብርሃን መሻቱን እንዲህ ሲል በመዝሙሩ ጸልዮአል÷
<ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ እማንቱ ይምርሐኒ ወይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ> /መዝ. 42.3/አቤቱ ብርሃንህንና እውነትህን (ጽድቅህን) ላክ እነርሱ ይምሩኝ ወደ መቅደስህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይወሰዱኝ፣
ብርሃን የሆነ፣ጽድቅ የሆነ፣ እውነት የሆነውን ቅዱስ ልጅህን(ወልድን) ክንድህን ልከህ ጨለማ ሆኖ የጋረደንና ካንተ የለየን ኃጢአታችን አስወግዶ ከአንተ አስታርቆ ወደ አንተ ይውሰደን ሲል ነው። የዚህ ሁሉ ትንቢትና ጸሎት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ ተልኮና በፈቃዱ ወደዚህ ዓለም በመምጣት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በተዋህዶ ፍጹም አምላክና ሰው ሆኖ በዓለም ሲያስተምር «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» /ዮሐ. 8.12/ በማለት ብርሃንነቱን አረጋግጧል፤ በመቀጠልም እርሱን የሚከተል ሁሉም ያንን ብርሃን እንደሚያገኝ እንዲህ በማለት ተናግሯል‹‹ እኔን የሚከተል ሁሉ የሕይወት ብርሃን ያገኛል በጨለማም አይመላለስም››(ዮሐ 8:12)። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ሁሉ ሕይወት የሆነች ብርሃን ገልጧል፤ ብርሃን መሆኑን ደቀመዛሙርቱም ስለ ብርሃንነቱ እንዲህ በማለት መስከሯል «ሕይወት በእርሱ ነበረ፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም» /ዮሐ. 1.4-5/። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጨለማ ያላሸነፈው ዘወትር የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ነው። ሊቃውንትም ‹ዘዘልፈ ያበርህ፣ብርሃን ዘበአማን› ሁሉ ጊዜ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ‹ዘእንተ ውስጥ አይነነ አብራህከ ወጽልመተ ሐሊናነ፣ብርሃነ_ፍጹማን ወልደ አምላክ ሕያው› የሕሊናችንን ጽልመት ያበራ፣ ዓይነ ልቡናችንን የገለጠው፣ የሕያው አምላክ ልጅ የፍጹማን ብርሃን ብለውታል። ዮሐንስም ስለዚህ ብርሃን ሲመሰክር ለሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ ሲል፣ ቅዱስ ጴጥሮስም ይህ ብርሃን በልቡናችን ውስጥ የሚያበራ ብርሃን ነው ብሎታል(1ኛጴጥ 1:19)።
ቅዱስ ጳውሎስም መጀመርያ በብርሃን የነበረ እንኳ ቢመስለውም ያ ብርሃን ሳይበራለት በጨለማ ሆኖ ይህንን ብርሃን ለማጥፋት የብርሃን ልጆቸና ብርሃን እያሳደደ ሳለ ጌታችንም ትጋቱንና ቅንነቱን በመመልከት ጌታችን በሚያንፀባርቅ ብርሃን አምሳል እንደተገለጠበት ተናግሯል፡፡ « በመንገድ ሳለሁ እኩለ ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ … አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ ” አለኝ(የሐዋ 26:13_15) ቅዱስ ጳውሎስ ያ ብርሃን ከበራለት በኋላ ጨለማ ከእርሱ ውስጥ ስፍራ ስላላገኘ ብርሃንነቱን ለማወጅ ተሯሩጧል፤ ሌሎችም ሲያሰተምር እርሱንም ራሱ ጨምሮ እንደህ ሲል ተናግሯል ‹‹ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፤ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና።
ስለዚህ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል›› (ኤፌ 5:8-14)። ክርስቶስ በአህዛብም ብርሃን እንደሆነ ቀድሞዉኑ ተወስኖ ነበር፤ (ኢሳ 49:6)‹…እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአህዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ› ይላል። በጨለማ የተጓዘ እንቀፋት ሳይመታው አይቀርም፣ ክርስቶስ ግን ይህንን ጨለማ በማስወገድ ብርሃን በመሆን ከእንቅፋትም ከመሰናክልም ሊያድን መጥቷል፤ እንቅፋቱንም ያሳያል። ስለዚህ ከእንቅፋትም ከውድቀትም ለመዳን በዚህ ብርሃን መራመድ ይገባል። እመኑ በብርሃኑ ወአንሰውስዉ እንዘ ብክሙ ብርሃን እንዳለው ሊቁ፤ በብርሃኑ አምነን በብርሃን እንመላለስ። በራሳችን ካልራቅን ጨለማ ካልመረጥን እርሱ ይወደናል ስለ ወደደን ነው ሳያዳላ ስለ ሁሉም ሰው ወደ ዓለም የመጣ‹ ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኲሉ ሰብእ ለእለ ይነብሩ ውስተ ዓለም በእንተ ፍቅረ ሰብእ መጻእከ ውስተ ዓለም ወኲሉ ፍጥረት ተፈስሃ በምጽአትከ› ሁሉም ፍጡር የተደሰተብህ፣ ሰውን ወደህ ወደዚህ ዓለም የመጣህ፣ በዓለም ውስጥ ላለ ሁሉ ሰው የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ነህ ተብሏል። ታድያ እኛስ በመምጣቱ ደስተኞች ነን? ያለ እርሱስ በጨለማ ውስጥ እንደምንኖር ተገንዝበናል?
በዘመነ ኦሪት ለነበሩ ሰዎች እርሱ ራሱ የፈጠራት ፀሐይ ከእነርሱ አልጠፋችም ነበር አሁንም አለች እርሷ ለሁሉም ዓለም የፀጋ ስጦታ ናት፤ነገር ግን በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ሆኖው ብርሃንህን ላክልን ሲሉ የነበረ አሁን በግዙፍ ዓይናችን የምናያት የምንመለከታት ፀሐይ የምትሰጠው ብርሃን አጥተው አይደለም፣ የውስጥን ጨለማ ድንቁርናና ኃጢአትን አስወግዶ ውስጣዊ ሕሊናን በማብራት ያለምንም እንከን አምላካችንን የምናይበትና የምንከተልበት መንፈሳዊ ዓይናችን ሊያበራ የሚችል አማናዊ ብርሃን ፈልገው ነው እንጂ፤ አሁንም እኛ የእውራን ዓይንና አእምሮ የሚገላልጠውን አማናዊ ብርሃን እንጋብዘው፤ እንድያውም እርሱ በበራችን ሆኖ እያንኳኳ ነው እንክፈትለት (ራእ 3:20)፤ እነዚያን ሰዎች ሲለምኑ ነበር እኛ ደግሞ እየተለመንን ነው፤ አንድ ቀን ጌታችን ሐዋርያትን ሲያነጋግራቸው ብዙዎች ለማየት፣ ለመስማት፣ ተመኝተው አላዩም አልሰሙምም እናንተ ግን ብፁአን ናችሁ፤ ዓይናችሁም አይቷል ጆሮአችሁም ሰምተዋል ሲል ዕድለኞች መሆናቸውን መስክሯል። ዮሐንስም እኛም በዓይናችን አይተናል እንመሰክርማለን ብሏል። ውድ አንባብያን ሆይ! እኛም ሁላችን በዚህ ብርሃን አምነን በብርሃኑ ከተመላለስን ለእኛ ብሎ ነው የመጣና የዚህ ክብርና ብርሃን ባለቤቶች ነን። በዚህ ዓለም የምናገኘው የፀሐይ ብርሃን ከሁሉም ዓለም በጋራ ነው የምንጠቀመው ውስጣዊ ማንነታችንም አይደለም አይገልጽምም፤ የሚያስደንቀው ግን የእግዚአብሔር ቸርንት ነው፤ ምክንያቱም ያ ብርሃን ለሚያምኑት ሆነ ለማያምኑት፤ ለጠላቶቹም ሆነ ለወዳጆቹም በእኩል መስጠቱ ነው፤ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ቀኑን በማፈራረቅ ለዓለም ስታበራ የቆየች ፀሐይ እንደ ሌሎቹ ፍጡራን አንድ ቀን ማለፍዋ ስለማይቀር የምትሰጠው ብርሃን የተፈራረቀና ውጫዊ ብርሃን ቢሆንም እንኳ እሱም ቀጣይነት እንደሌለው የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ ብርሃን ከሚጠሉና ጨለማን ከመረጡ ሰዎች መለየት አለብን፤ ከጨለማው ዓለምና አስተሳሰብ ወጥተን በፈጠራት ፀሐይ ዓለምን ያበራ እርሱ ራሱ ብርሃን በመሆን ደግሞ ውጫዊውንና ውሰጣዊውን የሚያበራ የሥጋና የነፍስ ብርሃን የሆነ የሕይወት ብርሃን እንያዝ እንከተል <የመዳን ቀን አሁን ነው> እንዳለው ሐዋርያው ከዓለማዊ አስተሳሰብ ወጥተን ወደመንፈሳዊና ዘላለማዊ ሕይወት ግዜው ሳይመሽ አሁን ተሎ ብለን እንግባ፡፡ ሌላ ጊዜ አንጠብቅ በሆነ አጋጠሚ ሳንዘጋጅ ከዚህ ዓለም ከተለየን የኛ ጊዜ እሱነውና በጸጸት ሰለማይመለስ፤ ከሁሉም ነገር አስቀድማችሁ መንግስቱንና ጽድቁን ፈልጉ እንዳለን ጌታችን ቃሉን አክብረን ተዘጋጅተን እንጠብቀው። ይህንን ማድረጋችን ከመብላት፣ ከመልበስ፣ ከመስራትና ከትዳር አይከለክለንም፤ ከኃጢአትና ሥርዓት አልባ ከሆነ ዓለማዊ ምኞት እንጂ። ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ ብሎ እየመከረን ነው<ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ>።(ሮሜ 13:11-14)። በእርሱ ዘንድ ጨለማ የለም ሁሌም ብርሃን ነው፡፡ ‹‹ከእንግዲህም ሌሊት አይሆንም ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሳሉ››(ራእ 22፡5)፡፡ ያ ብርሃንም ራሱ መድኃኔዓለም ነው፤ «ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም»(ራእ 21:13)፡፡ ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በእውነት ይህንን ክብርና ብርሃን ሊያመልጠን አይገባም፤ በዚህ ብርሃን ከብርሃን አባትና ብርሃን ከሆነው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑምጋር ለዘላለም ለመኖር በብርሃኑ አምነን ከብርሃንና ከብርሃን ልጆች ቅዱሳን ጋር አሁን በትንሳኤ ልቡና በአብ ቀኝ እንቀመጥ (ቈላ3:1-3፤ ኤፌ2:6-7)። በብርሃኑ ልቡናችንና ሁለንተናችንን ያብራ !!!
ወስብሃት ለእግዚአብሔር አሜን!