“እውነተኛው የዓለም ብርሃን”
ብርሃን ሁሉን የሚያሳይና ለፍጡራን ሁሉ የሚጠቅም የተፈጥሮ ፀጋ ስለሆነ መልካሙ ነገር ሁሉ በብርሃን ይመሰላል፡፡ ይሁን እንጂ ከስነ ፍጥረት የሚገኝ ብርሃን ተቃራኒ ስላለው ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂና አስተማማኝ አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡ – ከፀሐይ፣ ከጨረቃና ከክዋክብት እንዲሁም ከእሳት ወይም ከኤሌክትሪክና ከመሳሰሉ የተፈጥሮ ውጤቶች የሚገኝ ብርሃን ጊዜያዊ እንጂ ቋሚና አስተማማኝ ስላልሆነ አንድ ጊዜ ይበራል ሌላ ጊዜ ደግሞ ይጠፋል፡፡ ምክንያቱም የፀሐይ ብርሃን በቀን በርቶ በሌሊት ጨለማ ይጋርደዋል፤ በቀንም ጥላ ይከልለዋል፡፡ ከጨረቃና ከክዋክበት የሚገኘውም ብርሃን በሌሊት እንጂ በቀን ደምቆ ሊታይ አይችልም፤ ሌሊትም ቢሆን ጊዜና ወቅት ይወስነዋል፡፡ ከእሳት የሚገኘው ደግሞ ተቀጣጣይ ነገሮች ሲታጡ ወይም በውኃ ኃይል እሳቱ ሲጠፋ ብርሃኑም አብሮት ይጠፋል፡፡ የኤሌክትሪኩም እንደዚሁ መስመሩ ሲቋረጥና አምፖሉ ሲቃጠል ብርሃኑም አብሮ ይቋረጣል፡፡ ስለሆነም በተፈጥሮ ሂደቶች የሚገኘው ብርሃን ሁሉ ተቃራኒ ስላለው እውነተኛ ብርሃን ሊባል አይችልም፡፡
ታዲያ እውነተኛ ብርሃን ማነው? መልሱን ከቅዱሳት መጻሕፍት ማግኘትና መረዳት እንችላለን፡፡ ሐዋርያውና ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈው የመረጀመሪያ መልእክቱ “መንዜንወክሙ ከመ እግዚአብሔር ብርሃን ውእቱ መጽልመትሰ አልቦ ኃቤሁ ወኢ አሐተኒ” (ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት እግዚአብሔር ብርሃን ነው፣ ጨለማም በእሱ ዘንድ ፈጽሞ የለም፤ የምትል ናት) በማለት እውነተኛ ብርሃን እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ በግልጥ ጽፎአል (1ዮሐ. 1÷5)፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣትና ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ ሰው ሆኖ የመወለዱ ምስጢር እንደ እንግዳ ደራሽ እንደውኃ ፈሳሽ በድንገት የሆነና የተፈጸመ ሳይሆን ገና ከመሆኑ አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት ትንቢት የተነገረለትና ሱባዔ የተቆጠረለት ከመሆኑም በላይ በልዩ ልዩ ምሳሌዎች የተገለጠ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ከምሳሌዎቹም አንዱ ‹‹ብርሃን›› በመሆኑ ይህ ብርሃን የሚለው ስም ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወጣለት ገና ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ከልደቱ በፊት በዘመነ ነቢያት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት መሠረት ከበዓለ ልደቱ አስቀድሞ ያሉት ሦስት ሳምንታት የመጀመሪያው ስብከት ሦስተኛው ደግሞ ኖላዊ በመባል የሚከበሩ ሲሆኑ በስብከትና በኖላዊ መካከል ያለው ሳምነት ደግሞ ‹‹ብርሃን›› በመባል እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ ‹‹ብርሃን›› ተብሎ በሚጠራው በዚሁ ዕለተ ሰንበት የሚቆመው ማኅሌት የሚዘመረው መዝሙርና የሚነበቡት ምንባቦች ሁሉ የሰውን ልጅ ለማዳን ከሰማይ ወደምድር የወረደውና ወደዚህ ዓለም የመጠው ኢየሱስ ክርስቶስ እውንተኛ የዓለም ብርሃን እንደሆነ የሚገልጡና የሚያስረዱ ናቸው፡፡
ወንጌላዊውና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈው ወንጌል እውነተኛ ብርሃን የተባለ ማን እንደሆነ ሲገልጽ “ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበር እሱም ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምን ለምስክርነት መጣ፡፡ ስለብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም” በማለት ስለመጥምቁ ዮሐንስ ማንነት ከገለጠ በኋላ፡ – “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃንስ ወደ ዓለም የመጣው ነው” በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ከጨለማ፤ የሰውን ልጅ ደግሞ ከጥፋት ለማዳን ወዲዚህ ዓለም የመጣ እውነተኛ ብርሃን እሱ እንደሆነ በሚገባ አረጋግጦ ጽፎት ስለሚገኝ በዚሁ “ብርሃን” እየተባለ በሚከበረው ዕለተ ሰንበት ይነበባል፤ ይተረጎማልም (ዮሐ. 1÷6-13)፡፡
ልበአምላክ የተባለ ነቢዩ ዳዊትም ዓለም በጨለማ ውስጥ በነበረበት በዚያ የኲነኔና የፍዳ ዘመን “ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ፤ እማንቱ ይምርሃኒ ወይሰጻኒ ደብረ መቅደስከ፤ ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ” በማለት ዘምሮአል፡፡ ትርጓሜውም “ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፣ እነሱም ይምሩኝ፤ አቤቱ ወደ መቅደስህ ተራራና ወደማደሪያህ ይውሰዱኝ” ማለት ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ሰው ሆኖ ከድንግል ማርያም ከመወለዱ አስቀድሞ የተነገረና እውነተኛ ብርሃን የተባለውም እሱ ራሱ ክርስቶስ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ትንቢታዊ ቃል ነው (መዝ. 42÷3)፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስም ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት የነበረውን 5500 የፍዳና የመከራ ዘመን በጨለማ፤ ከጌችን ልደት በኋላ ያለውን ዓመተ ምሕረት ተብሎ የሚጠራውን ዘመን ደግሞ በብርሃን መስሎ በተናገረው የትንቢት ቃል “ሕዝብ ዘይብር ውስተ ጽልመት ርእየ ብርሃነ ዐቢየ፤ ወለእለ ይነብሩ ውስተ ጽልመት ወጽላሎተ ሞት ብርሃን በርሀ ሎሙ” (በጨለማ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ብርሃንን አዩ፤ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገረርም ለነበሩ ሰዎች ብርሃን ወጣላቸው) በማለት ትንቢት የተናገረውም ቦታና ጊዜ ስለሚወስነውና ጨለማ ስለሚጋርደው ከፀሐይ ወይም ከእሳትና ከመሳሰሉት ነገሮች ስለሚገኘው ብርሃን ሳይን ሕፀፅና ጉድለት ስለሌለበት ስለእውነተኛው የዓለም ብርሃን ስለኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ኢሳ. 9÷2)፡፡
የተነገረው ትንቢትና የተቆጠረው ሱባዔ ሁሉ ተፈጽሞ ዓለምን ለማዳንና የጨለማውን ዘመን አሳልፎ በዓለም ውስጥ እውነተኛ ብርሃን ለመሆን ወደዚህ ዓለም የመጣውና ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ ሰው ሆኖ የተወደለው መድኃኔዓለም ክርስቶስም በመዋዕለ ትምህርቱ ስለራሱ ሲናገር “ብርሃን ወደዓለም መጥቶአልና ሰውም ሥራው ክፉ ስለሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጦአልና፡፡ ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና ክፉ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደብርሃን አይመጣም” በማለት ሰዎች ሁሉ “እውነተኛ ብርሃን” እሱ እንደሆነ አውቀውና ተረድተው ወደእሱ እንዲመጡና በእሱም አምነው በብርሃኑ እንዲመላለሱ በምሳሌ ከማስተማሩም በላይ ወደ እውነተኛው ብርሃን የማይመጡና ጨለማውን የሚመርጡ ሁሉ መጥፎ ሥራቸው እንዳይገለጥባቸው የሚሹ ሌቦችና ወንበዴዎች ነፍሰገዳዮችም እንደሆኑ ገልጦና በሰፊው አረጋግጦ አስተምሮናል (ዮሐ. 3÷19-21)፡፡ ከዚህም ሌላ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” እያለ ይናገርና ያስተምር እንደነበር ወንጌላውያን በጻፉት ቅዱስ ወንጌል መስክረዋል፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም የተባለው ታላቅ ሊቅም ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ባቀረበው የምስጋና ድርሰቱ “ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኲሉ ሰብእ ለእለ ይነብሩ ውስተ ዓለም፣ በእንተ ፍቅረ ሰብእ መጻእከ ውስተ ዓለም”፤ “በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን፣ ስለሰው ፍቅር ስትል ወደ ዓለም መጣህ” በማለት ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርጎ ስልጇ ስለኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን የምስጋና ቃል በዘወትር ጸሎታችን ሁል ጊዜ እየደገምነው እንገኛለን፡፡
በ4ኛው ምዕት ዓመት በደገኛው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዘመነ መንግሥት “ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር እንጂ አምላክ አይደለም” በማለት በሰው ልቡና እንክርዳድ እየዘራ የክህደት ትምህርት በማስተማር ላይ የነበረውን እርጉም አርዮስን ለማውገዝ በኒቅያ የተሰበሰቡ “ሠለስቱ ምዕት” በመባል የሚታወቁ በዕውቀት የበለፀጉ፣ ሃይማኖታቸው የፀና ምግባራቸውም የቀና 318 ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንም “…. ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር የነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፤ እሱም ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፣ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚስተካከል፤ ሁሉ በእርሱ የሆነ ያለእርሱ ምንም የሆነ የለም …” በማለት በጸሎተ ሃይማኖት ወስነዋል ይህንንም በዘወትር ጸሎታችን በቃልም በመጽሐፍም እየደገምነው እንገኛለን፡፡
ስለዚህ ሁላችንም ቃሉን መድገም ብቻ ሳይሆን ምሥጢሩ ምን እንደሆነ በመመርመር ዓለምን ለማዳን ወደዚህ ዓለም የመጣው መድኃኔዓለም ክርስቶስ እውነተኛ የዓለም ብርሃንና እውነተኛ አምላክ መሆኑን ገልጠን በማስተማር ያላመኑትን ሁሉ ለማሳመን ብርቱ ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡
( ከሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ)