እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል በዓታ ለማርያም በዓል አደረሳችሁ

2400

እመቤታችን 3 ዓመት ሲሆናት  ቅድስት ሐና ለባሏ ጌታዬ ልጃችን አድጋለች በተሳልነው መሰረት ለቤተ እግዚያብሔር እንስጣት አለችው፤ ይዘዋት ወደ ቤተመቅደስ ሲሄዱ ካህኑ ዘካርያስ ጉባዬ ዘርግቶ ህዝቡን ሰብስቦ እያስተማራቸው ነበር፤ እመቤታችንን ቢያያት ከጸሐይ አብርት ከመብረቅ አስፈርታ ታየችው፤ ይህችን የመሰለች ፍጡር ምን ልንመግባት ነው ብለው ተጨነቁ፤ በዚህ ጊዜ መልአኩ ፋኑኤል ህብስት ሰማያዊ ጽዋ ሰማያዊ ይዞ ተገለጸ አንድ ክንፉን ጋርዶ አንድ ክንፉን አጎናጽፎ ከመሬት አንድ ክንድ ከስንዝር ከፍ አድርጎ ህብስቱን አብልቶ ወይኑን አጠጥቶ እመቤቴ መንገድ ባስመታሁሽ ማሪኝ ብሎ አርጓል፤ ይህ የሆነው በታህሳስ 3 ነው::

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአራዳና ጉለሌ ክፍላተ ከተማ የምትገኘው የታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም መሥራች የሆኑት ታላቁ የሥልጣኔ በር ከፋች ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ያረፉበት መቶኛ ዓመት የዐልማዝ ኢዮቤልዩ ዝክራቸው ብፁዕ ወቅድስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ታህሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም በታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም በታላቅ ድምቀት የተከበረ ሲሆን ዕለቱ የቅድስት ድንግል ማርያም በዐል በመሆኑ በዚህ በዐል ላይ የተለየ የበዓል የስነ ስርዓት ድምቀት የታዬ መሆኑን ከቦታው ድረስ በመገኘት አረጋግጠናል::

በዚሁ በዐል ወቅት ልብሰ ተከህኖ የለበሱ ሊቃውንት እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የበዐሉን ገፅታ የሚያአንፀባርቅ ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡ የኢዮቤልዩ በዐሉን በተመለከተ የተዘጋጁ የሕትመት ውጤቶች ለምዕመናን ተሰራጭተዋል፡፡

በታዕካ ነገሥት በዐታ ለማርያም ገዳም አስተዳዳሪ በሊቀ ሊቃውንት አባ ኃይለ መስቀል ውቤ፣ በአራዳ ጉለሌ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በሊቀ ትጉኃን ታጋይ ታደለ እና በታዕብ ነገሥት በባዕታ ለማርያም ገዳም ጸሐፊ በሊቀ ሕሩያን ሲሳይ ገ/ማርያም እንዲሁም ለበዐሉ በተዘጋጀው የዝግጅት ኮሚቴ አስተባባሪነት የተመራው የበዐሉ መርሐ ግብር ለምዕመናን መንፈሳዊ ደስታን ያጐናጸፈ እና መንፈሳዊ እሴትን የያዘ ነው፡፡

በየዓመቱ ታህሳስ 3 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ዕንብርት ላይ በምትገኘው ለከተማው እንደ ዕንቁ ፈርጥ በምታበራው ታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም የሚከበረው ሥነ በዐል በብዙ መልኩ ታሪካዊነት ጐልቶ ይታይበታል፡፡

ከሁሉ በፊት (ርግበ ሰሎሞን) ድንግል ማርያም እመቤታችን በ3 ዓመቷ ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት የተቀደሱ ኢያቄምና ሐና አንዲት ብላቴና ልጃቸውን አርሷን ለቤተ መቅደስ በመስጠት የከንፈራቸው ፍሬ እሙን የሆነበት ታላቅ በዐል ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግነታቸውን የሚመሠክርላቸው የስልጣኔ በር ከፋች የሆኑት ደገኛው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ያረፉበት ዕለት በጸሎት በያሬዳዊ ማህሌት የሚታወስበት ቀን እንደሆነ ተገልጾአል፡፡ዝክረ ምኒልክ መቶኛ ዓመት

በሦስተኛ ወገን ደግሞ ንግሥተ ነገሥታት ዘወዲቱ ታዕካ ነገሥት ተብላ የተሰየመችውን ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ለዓፅማቸው ማረፊያ ለስማቸው መዘከሪያ በልዩ መልክ እና ውበት በራሳቸው አክሊለ ክብር ዘውዳቸው ዐይነት በጥራት አሳንፀው ታቦተ እግዝእትነ ማርያምን በመንፈሳዊ እና በደማቅ ሥርአት አሳንፀው አስገንብተው ቅዳሴ ቤቱን በፍጹም የደስታ ማህሌት ያከበሩበት ታሪክ የሚታወስበት ዕለተ ክብር ሆኖ ይታያል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ገንዘቦታችን እና ንብረቶቻችን ምዕመናን ናቸው፡፡ የካህናት የኑሮ መተዳደሪያቸው ምዕመናን ናቸው ካህናት ከሌሉ አገልግሎቱ ይቆማል፡፡ ምዕመናን በየጊዜው የሚአስገቡት ገቢ በትክክል ከተያዘ ብዙ ሥራ ልንሠራበት ዕንችላለን፡፡ ገንዘቡ በትክክል መግባት አለበት፣ በትክክልም መውጣት አለበት፣ ገንዘባችንን ዕንወቅበት ምዕመናን አሥራት በኩራቱን ማውጣት ይገባቸዋል፡፡ አስራት በኩራት የእግዚአብሔር ድርሻ ነው ምዕመናን አሥራት ካወጡ በጧት በማታ የሚለመን ገንዘብ አይኖርም፡፡

ይህንን በዐል ስናከብር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በላያችን ታንዣብባለች ትባርከናለችም አሁን እመቤታችን በመላእክት ታጅባ እየባረከችን ነው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን ይገኛል፡፡ በቅዱስ ወንጌል ሁለትም ሶስትም ሆናችሁ በስሜ በምትሰበሰቡበት እኔም በዚያ እገኛለሁ ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት በመካከላችን ሆኖ እየባረከን ነው ምክንያቱም ይህ ጉባኤ ጉባኤ እግዚአብሔር ነውና በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ መልእክት አስተላልፈው የበዐሉ መርሐ ግብር በቅዱስነታቸው ቡራኬና ጸሎት ተጠናቋል፡፡

{flike}{plusone}