እንኳን ለእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አመታዊ የመታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ !! ታቦተ ጽዮን ፤ ኅዳር ጽዮን እና አክሱም ጽዮን

m00001

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓላት አንዱ “ኅዳር ጽዮን” ሲሆን የሚከበረውም ኅዳር 21 ቀን ነው፡፡ የበዓሉን አከባበር ፤ ጥንተ ታሪኩን፤ ንግስት ሳባ ፤ቀዳማዊ ምኒልክና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮችን  እንመለከታለን፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  “ታቦተ ጽዮን” የፈጸመችውን ልዩ ልዩ ተአምራት ለምእመናን እያስተማረች በታላቅ ድምቀት የምታከብረው ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በደብረ ሲና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ዐሥርቱ ቃላተ የተጻፈበትን ጽላት /ታቦተ ጽዮን/ ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበለ፡፡  “ታቦተ ጽዮን” የሚለውንም ስያሜ ያገኘችው ጽዮን ተብላ በምትጠራው የእስራኤል ከተማ ስም ነው፡፡ ጽዮን ማለት ተፀወነ፡- ተጠጋ፣ ተማጠነ ማለት ነው፡፡ ክቡረ ዳዊትም ጽዮንን አምባ፣ መጠጊያ አድርጎ ብዙ ጠላቶቹን ተዋግቶ አሸንፎ ድልን ተጎናጽፏል፡፡

ጽዮን የተባለችው የታላቁ የዳዊት ከተማ የተገፉና የተበደሉ ሕዝቦች ሁሉ እውነተኛ ፍርድ ለማግኘት፣ ተሰብስበው የሚሰነብቱባት ከተማ ስለነበረች፣ ጽላተ ሙሴም በዚያ ስለነበረች በርሷ ተማጽነውም ችግራቸው ሰለሚቃለል ታቦቷ “ታቦተ ጽዮን” ተብላለች፡፡
ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ በራእዩ “በሰማይ ያለችው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ

ተከፈተች፡፡ በውስጧም ያለችው ታቦተ ሕግ ታየች፡፡” ራእይ. 11 ሚ 19 በማለት የተናገረውን ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በመጽሐፈ አክሲማሮስ ሲተረጉመው “በሥላሴ ጸዲል በሥላሴ ብርሃን የተመላች ስመ ሥላሴ የተጻፈባት ታቦት በኢየሩሳሌም ሰማያዊት አለች፡፡ በዚህች ታቦት ላይ ከፍጥረተ ዓለም በፊት ስመ እግዝእትነ ማርያም ተጽፎባት ነበር፡፡ ቅድመ ዓለም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመፈጠሯ በፊት በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖረ ነበር የሚለው መሠረቱ ይህ ነው” ብሏል፡፡ ታቦተ ጽዮን የምትኖርበትን ድንኳን ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንዲሠራ እግዚአብሔር ነግሮታል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሲናገር “ደብተራ ኦሪትን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት አርአያና ምሳሌ እንዲሠራ እግዚአብሔር አሳይቶታል፡፡ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ሁለንተናዋ ከብርሃን የተሠራች ናት፡፡ የኢየሩሳሌም ሰማያዊት ቅርጽም ደብተራ ኦሪትን ትመስላለች፡፡” ይላል፡፡ ሕዝቡም ከፈጣሪያቸው ጋር ቃል ኪዳን ገብተው በታቦተ ጽዮን አማካኝነት ሲያመሰግኑ ኑረዋል፡፡
ታቦተ ጽዮን እግዚአብሔርን ለሚያምኑ፣ ሕጉን ትእዛዙን ለሚፈጽሙ ሰዎች ሁሉ ልዩ ልዩ ተአምራትን እንደፈጸመች ከቅዱስ መጽሐፈ እንረዳለን፡፡ እስራኤላውያን ሕጉን ሲጠብቁ ትእዛዙን ሲፈጽሙ እግዚአብሔር በታቦተ ጽዮን እያደረ ይረዳቸውና ጠላቶቻቸውንም ድል ያደርጉ ነበር፡፡ ሕጉን ሲያፈርሱ ደግሞ በጠላቶቻቸው ይሸነፉ ነበር፡፡

በዚያ ዘመን ኤሊ የሚባል ሊቀ ካህናት ነበር፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የሚባሉ ሁለት ልጆች ነበሩት፡፡ እድሜውም 98 ዓመት ነበር፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የአባታቸውን ምክር አቃልለው የማይገባ ኃጢአት ሠርተው አምላካቸው እግዚአብሔርን አሳዘኑ በራሳቸው ፈቃድ ተጉዘው ሕገ እግዚአብሔርን ጣሱ፡፡ በሕዝቡም ላይ የሚያደርሱት በደል እየጨመረ ሔደ፡፡
አፍኒንና ፈንሐስ እግዚአብሔር በኃጢአታቸው ምክንያት በረድኤት ስለተለያቸው ፍልስጥኤማውያን በጠላትነት ተነሡባቸው፡፡ እስራኤላውያን ከኤሊ ልጆቸ ጋር ሆነው በአንድነት ታቦተ ጽዮንን ይዘው ለጦርነት ወደ ፍልስጥኤም ዘመቱ፡፡ ጦርነትም ገጠሙ ታላቅ ግድያም ሆነ፡፡ በጦርነቱ አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ፡፡ ታቦተ ጽዮንም በኤሎፍላውያን እጅ ተማረከች፡፡ ሕዝቡም በጦርነት አለቁ፡፡ ከጦርነቱ ያመለጠ አንድ ሰው ወደ ኤሊ ሄዶ እስራኤላውያን ተሸንፈው መሸሻቸውን፡ ሁለቱ ልጆቹ አፍኒንና ፊንሐስ መሞታቸውን ታቦተ ጽዮንም መማረኳን ነገረው፡፡

ኤሎፍላውያንም ታቦተ ጽዮንን ማርከው ከወሰዷት በኋላ ዳጎን ከተባለው ጣዖታቸው በታች አስቀመጧት፡፡ በማግስቱ የዳጎን አገልጋዮች መጥተው ቢያዩአት ፣ ዳጎን ከእግዚአብሔር ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት፡፡ አንስተው አቁመውት ሔዱና በማግስቱ መጥተው ቢያዩት በግንባሩ ወድቆ እጆቹ ተለያይተው ጣቶቹም ተቆራርጠው ደቀው በወለሉ ላይ ተበታትነው ነበር፡፡ ታቦተ ጽዮን ግን ምን ጉዳት ሳይደርስባት ከላይ ሆና አገኙአት፡፡ አገልጋዮቹም ታቦተ ጽዮን ያደረገችውን ተአምር በማድነቅ ዳጎንን በመናቅና በማቃለል ከዚያ ቀን ጀምረው ከቦታው ፈጽመው አልደረሱም፡፡ 1ኛ ሳሙ 5፤1-7፡፡ ሕዝቡም በሰውነታቸው ላይ እባጭ እየወጣባቸው ሲገድላቸው ሌሎቹንም በሚያንቀጠቅጥና በሚጥል በሽታ እያሰቃያቸው፣ እህላቸው በአይጥ፣ እንስሶቻቸው በበሽታ አለቁባቸው፡፡
ታቦተ ጽዮን በኤሎፍላውያን ላይ እንዲህ ያለ ተአምር እየፈጸመች በፍልስጥኤም አገር ለሰባት ወራት ቆይታለች፡፡ ከሰባት ወራት በኋላ ኤሎፍላውያን ታቦተ ጽዮንን ወደ ሀገሯ ለመመለስ ወርቅ በሳጥን አድርገው በሠረገላ ጭነው በላሞች እያስጎተቱ ወደ ሀገሯ ሰደዷት፡፡ እስራኤላውያን የታቦተ ጽዮንን መመለስ በሰሙ ጊዜ በዕልልታ በሆታና በዝማሬ ተቀብለው አሚናዳብ ቤት አስገቧት፡፡ በዚያም ሃያ ዓመታት ኑራለች፡፡ የአሚናዳብ ቤት በታቦተ ጽዮን ምክንያት ተባርኮለታል፡፡ 1ኛ ሳ. 7፤2፡፡
ንጉሥ ዳዊት ታቦተ ጽዮን ወደ ከተማው በመጣች ጊዜ ከዙፋኑ ተነስቶ እየዘመረ በክብርና በምስጋና ተቀብሏታል፡፡ ብዙ መስዋዕትም ተሰውቷል፡፡ 2ኛ ሳሙ 6፤14፡፡ ታቦተ ጽዮን እስከ ንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ድረስ በድንኳን /በደብተራ ኦሪት/ ከተቀመጠች በኋላ በንጉሡ ሰሎሞን በተሠራው ቤተ መቅደስ ገብታለች፡፡ 1ኛ ነገ. 8፤1-12፡፡

የንግሥተ ሳባ ጉዞ ወደ ኢየሩሳሌም
 ከጌታችን ልደት በፊት በ1ሺ ዓ.ዓ. በኢትዮጵያ የነገሠችው ንግሥት ሳባ ሦስት ስም አላት፡፡ በመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ምዕራፍ 10፤1-10 እና በ2ኛ ዜና 9፤1-8 ላይ “ሳባ” በማለት ትጠራለች፡፡ በክብረ ነገሥት ደግሞ “ማክዳ” ተብላለች፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ትምህርቱ “ንግሥት አዜብ” ብሏታል፡፡ ማቴ 12፤42፡፡ አዜብ ማለት ደቡብ ማለት ሲሆን ኢትዮጵያ በድሮ ግዛትዋ ለእስራኤል ደቡብ ነበረች፡፡ ጌታ ንግሥት አዜብ ያላትም ለዚህ ነበር፡፡
ይህንን ቃል ከእርሷ በኋላ 1500 ዓመት ቆይተው የተነሱት የኢትዮጵያ ነገሥታት ሳይቀሩ ይጠቀሙበት እንደነበር የቤተ ክርስቲያን መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ንግሥት ሳባ ኢትዮጵያዊት ነበረች?? ስለ ንግሥት ሳባ ኢትዮጵያነት የሚያስረዱ የተለያዩ ማስረጃዎች ይገኛሉ፡፡ ከጥንታውያን የታሪክ ጸሐፍት መካከል የሚቆጠረው ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ስለዚህችው ንግሥት “በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያና የግብጽ ንግሥት የነበረችው” በማለት ነበር የጻፈው፡፡ ላዕላይ ግብጽ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ግዛት እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ 

የግብጻውያን ትልቁ የታሪክ መዝገብ የሆነው የፓትርያርኮች ታሪክም እንዲህ ይላል “የታላቁ ሀገር አቢሲኒያ ንግሥት እርስዋም ንግሥት ሳባ የምትባል የደቡብ ንግሥት፣ ወደ ዳዊት ልጅ ሰሎሞን መጣች፡፡” ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያችን ከንግሥት ሳባ ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ የአርኪዎሎጂ /የከርሰ ምድር ጥናት/ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ ወደ አክሱም ጎራ ያለ ሰው የንግስት ሳባ ቤተመንግሥትን መጎብኘት ይችላል፡፡ይህ ቤተመንግስት በአርኪዎሎጂ ጥናት የተገኘ ነው፡፡ ንግስት ሳባ ማን ናት? የንግሥተ ሳባ ትውልድ ቦታ፡- በሰሜን ደንገሎ፣ በደቡብ ፎካደ በተባሉ በሁለት ተራሮች መካከል የሚገኝ ሲሆን ስሙም “ጎሎ ማክዳ” ይባላል፡፡ የንጉሥ ምኒልክ አንደኛ መቃብር፡- አክሱም ከተማ በስተምዕራብ 2 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በ1906 የደች ልዑካን የአርኪዎሎጂ ጥናት በሚያደርጉበት ወቅት ከምድር ውስጥ የተቀበረ ቤት ውስጥ የንጉሥ ምኒልክን ዐጽም ያገኙ ሲሆን የአክሱም ጽዮን ካህናት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር እንዳሳረፉት ይታወቃል፡፡
 በ13ኛው መ/ክ/ዘመን የነበሩት የአክሱም ንቡረ ዕድ ይስሐቅ ከተለያዩ ምንጮች ክብረነገሥትን ሲያዘጋጁ እጅግ ታላቅ ቦታ ከሰጡዋቸው ታሪኮች መሐል አንዱ የንግሥት ሳባ ታሪክ ነው፡፡ ንግሥት ሳባ እግዚአብሔርን በመፍራት በመልካም ሁኔታ ሕዝቡን ታስተዳድር ነበር፡፡ በወቅቱ በእስራኤል ላይ ነግሦ የነበረውን የሰሎሞንን ጥበብ በጆሮ መስማት ብቻ በቂ ሆኖ ስላላገኘችው በዓይን አይቶ መረዳት የበለጠ መሆኑን ተገነዘበች፡፡
 ለንግሥት ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ምክንያት የሆናት ታምሪን የተባለው ነጋዴ ነው፡፡ ይህ ነጋዴ በኢየሩሳሌም በሚቆይበት ጊዜያት ብዙውን ጊዜ የሚያሳልፈው የሰሎሞንን ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበብ በማየት ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በሚመለስበትም ጊዜ እየዘረዘረ ለንግሥት ሳባ ይነግራትና ያስረዳት ስለነበር፤ ንግሥት ሳባ ከዚሁ ነጋዴ በሰማችው ዜና የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብ ለማየት ጓጓች፡፡ በዚህም የተነሣ በታምሪን መሪነት ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፡፡ እግዚአብሔርም መንገዱን አቀናላት፤ ያለአንዳች መሰናክል ተጉዛ ኢየሩሳሌም ደረሰች፡፡ ለታቦተ ጽዮን ክብርና ለንጉሥ ሰሎሞንም ገጸ በረከት አቀረበች፡፡ 1ኛ ነገ. 10 ሚ 1-13፡፡ ንጉሥ ሰሎሞንም እርሷንና ተከታዮቿን በጥሩ መስተንግዶ ተቀበላቸው፡፡ ንግሥት ሳባም የቤተ መንግሥቱን ሥርዓትና ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበቡን ቀሰመች፡፡ በኢየሩሳሌም ቆይታዋ ከንጉሡ ቀዳማዊ ምኒልክን ፀነሰች፡፡
ወደ ኢትዮጵያም ተመልሳ ልጇን ምኒልክን በዛሬዋ አሥመራ ከተማ አጠገብ እንደወለደችው ይነገራል፡፡ የቀዳማዊ ምኒልክ ጉዞና የታቦተ ጽዮን መምጣት ቀዳማዊ ምኒልክ ከአደገ በኋላ በ12 ዓመቱ ከእናቱ የተሰጠውን ለታቦተ ጽዮንና ለንጉሥ ሰሎሞን እጅ መንሻ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ፡፡ ንግሥት ሳባም ለንጉሥ ሰሎሞን “ንጉሥ ሆይ ልጄን ሙሴ የጻፋቸውን ሕግጋት ሥርዓተ ክህነት አስተምረህ ላክልኝ፡፡” የሚል መልእክት ልካ ነበር፡፡
ቀዳማዊ ምኒልክ በኢየሩሳሌም ከአባቱ ዘንድ ለሦስት ዓመት ያህል ቆይቷል፡፡ በዚሁ ዘመን መጻሕፍተ ሙሴን፣ ሕገ መንግሥትን፣ ሥርዓተ ክህነትን የዕብራይስጥን ቋንቋ ከሊቀ ካህናቱ ከሳዶቅ ተምሯል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስም በፈቃደ እግዚአብሔር ታቦተ ጽዮንን ይዞልን መጥቷል፡፡ ይህች ታቦት ለ3000 ዓመታት ያህል እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ በአክሱም ትገኛለች፡፡ ንግሥት ሳባም ታቦተ ጽዮን መምጣቷን ስትሰማ ለእግዚአብሔር መስዋዕት አቀረበች፡፡ ሰዎችን መርጣ ታቦተ ጽዮንን እንዲጠብቁ አድርጋለች፡፡ የመንግሥቱን ሥልጣን በሙሉ ለቀዳማዊ ምኒልክ አስረክባ ከዚህ ዓለም በሞተ በተለየች ጊዜ በዚያው በአክሱም ተቀብራለች፡፡
ቦታውም እስከ አሁን ድረስ የንግሥት ሳባ መቃብር እየተባለ ይጠራል፡፡ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ታሪክ ጸሐፊው አቡሳላህ “አቢሲኒያውያን በእግዚአብሔር ጣቶች አሥርቱ ቃለት የተጻፈባት፣ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ያሉባት የቃል ኪዳኑ ታቦት አለቻቸው፡፡” በማለት ጽፎ ነበር፡፡ በዘመናችን ይህችን ታቦት ፍለጋ ያደረገው ግርሃም ሐንኮክም “The sign and the seal” በተሰኘው መጽሐፉ ይህን ገልጦታል፡፡ (የእንግሊዛዊው የታሪክ አጥኚ ግርሃም ሐንኩክ መጽሐፍ የሆነው “The sign and the seal” በአማርኛ “ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ” በሚል ተተርጉሞ በማንኛውም የመጽሐፍ መደብር ስለሚገኝ ሁላችሁም ገዝታችሁ ብታነቡ የሚያኮራውን ታሪክ ታውቁበታላቹ፡፡ ታቦተ ጽዮን በአክሱም በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ሥፍራ ከያዙት ቦታዎች ግንባር ቀደምትዋ የአክሱም ከተማ ናት፡፡ አክሱም የኢትዮጵያ የታሪክና የሃይማኖት እናት ከተማ ስትሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ሺ ዓ.ዓ. እንደተቆረቆረች መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ አክሱም የቤተ ክህነቱም ሆነ የቤተ መንግሥቱ ማዕከል በመሆን ለብዙ ዘመናት አገልግላለች፡፡ በተለይም እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያተ ሙሴ የሰጠው የታቦተ ጽዮን መንበር በመሆኗ ከተማዋን ድንቅ ሁኔታን ያጎናጽፋታል፡፡ በዘመነ ሐዲስም የክርስትና መዲና፣ የስብከተ ወንጌል ማዕከል ፤ የጳጳሳት መንበር ለመሆን መቻልዋም በቤተ ክርስቲያናችን የታሪክ ክፍል ውስጥ እንደ አጥቢያ ኮከብ እንድታበራ አድርጎአታል፡፡ የአክሱም ከተማ ከ4000 ዓመት ዕድሜ በላይ ያላት ናት:: 
እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ የአምልኮ ሥርዐታትን ይፈጽሙበት ዘንድ የምስክሩን ድንኳን፣ የቃል ኪዳኗ ታቦትንና ለአምልኮ ሥርዐቱ ማከናወኛ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሠሩ በሙሴ በኩል ታዘው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥም በእግዚአብሔር ጣት ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የሕጉ ጽላት፣ አርባ ዓመት ሙሉ እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ የተመገቡትን መና የያዘች መሶበ-ወርቅ፣ አሮን ለክህነት አገልግሎት ስለመመረጡ ምስክር የሆነችው ለምልማና ፍሬ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር ይገኙባታል፡፡(ዕብ.9፡4)

ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የሆነውን ባስልኤልን መረጠ ፡፡(ዘፀ.25፡9) እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋም አንድ ክንድ ተኩል፣ ቁመቷም አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡ በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከሆነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሠራ፤ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝም አደረጋቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ሆኖ እርስ በእርሳቸው የሚተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው ፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል  እግዚአብሔር ለሙሴ በመገለጥ ሰው ከባልንጀራው እንደሚነጋገር ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡ በደመና አምድ ይታያቸው ነበር፡፡(ዘፀ.25፡22፤33፡8-11)

ወደ ትርጓሜው ስንመጣ ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትሆን፣ በውስጡዋ የያዘችው የሕጉ ጽላት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የጌታን እናት ንጽሕናን የሚያመለክት ሲሆን በውጪም በውስጧም በጥሩ ወርቅ መለበጡዋ የቅድስናዋና ድንግል በሕሊና ወድንግል በሥጋ መሆኗን የሚያስረዳን ነው፡፡ ታቦቷን አራት  ሌዋውያን ካህናት ይሸከሟት ዘንድ በግራና በቀን በተዘጋጁ አራት ከወርቅ የተሠሩ ቀለበቶች ሲኖሩአት፤ በነዚያ የወርቅ ቀለበቶች ውስጥ ሁለት መሎጊያዎች ይገቡባቸዋል፡፡ ታቦተ ጽዮንን ለማንቀሳቀስ ሲፈለግ አራት ካህናት በመሎጊያዎቹ ይሸከሟታል፡፡ይህ ሥርዐት በሰማያትም የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የጌታን መንበር ገጸ ንሥር፣  ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ላህም፣ ገጸ አንበሳ ያላቸው አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታል፡፡(ኢሳ.6፡1-5፤ ሕዝ.1፡1-16) እንዲሁም ለአማናዊቷ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም “የምስራች የሚናገሩ፣ ሰላምንም የሚያወሩ፣ የመልካምንም ወሬ፣ መድኃኒትንም የሚያወሩ፣ ጽዮንንም አምላክሽ ነግሦአል የሚሉ እግሮቻቸው በተራሮች ላይ  እጅግ ያማሩ ናቸው” የተባለላቸው የእርሱዋንና የጌታችን ስም ተሸክመው የሚሰብኩ ወንጌላውያን አሏት፡፡(ኢሳ.52፡7)የስርየት መክደኛው ታቹ መቀመጫው ንጹሐን አንስት ላዩ መክደኛው የንጹሐን አበው ግራና ቀኙ የወላጆቹዋ የሐናና የኢያቄም ምሳሌ ነው፡፡  እርሱን በክንፎቻቸው የጋረዱት  ኪሩቤል  የጠባቂ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልና የአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ምሳሌዎች ናቸው፡፡

የስርየት መክደኛው ስርየቱ የሚፈጸምበት ስፍራ ነው፡፡ ነገር ግን እውነታውን ስንመለከት በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት መሥዋዕት ሲቀርብ እንዳልነበር እንረዳለን፡፡ ይህም በጊዜው አማናዊው መሥዋዕት ገና እንዳልተሠዋ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚገለጥበት ቦታ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር በእዚያ ላይ ማረፍ የለበትም፡፡ ይህ በራሱ የሚሰጠን አንድ ማስተዋል አለ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም ሰው በሆነ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት ልዩ ስፍራ እንዳለ ያመላክተናል፡፡ ስለዚህም ይህ ስፍራ ለዚህ እንደተጠበቀ ወይም በዚህ ምሳሌ አማናዊ መሥዋዕት የሚቀርብበት ሥፍራ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ነው፡፡  ይህ እንደሆነ ለማመልከት ሲባል ለኃጢአት የቀረበው መሥዋዕት ከታረደ በኋላ ካህኑ ደሙን በጣቱ በመንከር ሰባት ጊዜ በስርየት መክደኛው አንጻር በመገናኛ ድንኳን ውስጥ ይረጨው ነበር፡፡(ዘሌዋ.4፡6) ነገር ግን ይህ ደም ከዚያ ስርየት መክደኛው ላይ አያርፍም ነበር ምክንያቱም በዚህ ስፍራ መቅረብ ያለበት መሥዋዕት መለኮት የተዋሐደው ነፍስ ግን የተለየው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ነውና፡፡

ይህ የስርየት መክደኛ ሌላም ለእኛ የሚያስተላለፈው መልእክት አለው፡፡ መልእክቱም አማናዊው መሥዋዕት መቅረቡ እንደማይቀርና፣ መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ስፍራ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር በምህረት በሚገለጥበት በጸጋ ዙፋኑ በጽላቱ  ላይ መሆን እንዳለበት  ነው፡፡(ዕብ.4፡16) በዚህም እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና በየስፍራውም ስለስሜ ዕጣንን ያጥናሉ ንጹሕም ቁርባን ያቀርባሉ”(ሚል.1፡11) እንዳለው  የስርየት መክደኛው  በዓለም ዙሪያ ላለችው አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ምሥጢረ ቁርባንን ለምትፈጽምበት ጽላት ወይም ታቦት ምሳሌ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ጽላቱ(ታቦቱ) የሚያርፍበት ስፍራ መንበር ተብሎ ሲጠራ የእግዚአብሔር ስም የተጻፈበትና ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ የሚፈተትበት ደግሞ ጽላት ወይም ታቦት ወይም መሠዊያ ተብሎ ይጠራል፡፡

የስርየት መክደኛው በታቦቱ አናት ላይ መሆኑም ቅዱስ ኤፍሬም “ የእኛን ሥጋ ለነሣኸውና ፣ መልሰህ ለእኛ ለሰጠኸን ፣ ለአንተ ክብር ምስጋና ይሁን ፡፡ ከእኛ በሆነው ሥጋህ በኩል እጅግ የበዛውን የአንተን ስጦታ ተቀበልን፡፡” ብሎ እንዳመሰገነ፤ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን ያሳየናል፡፡ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱት በጥሩ ወርቅ የተሠሩት የኪሩቤል ምስሎችም አማናዊው መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ በዙሪያው ረበው የሚገኙ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፡፡  ይህን ለማስገንዘብ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በመንበረ ታቦቱ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ እንዲቀመጥ ታዝዛለች፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳን  ላስተዋለ ሰው በትክክል የታቦተ ጽዮንን መንፈሳዊ ትርጉምን ይረዳል፡፡

ይህን ድንቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉምን ይበልጥ ለመረዳት አንድ ምሳሌ የሚሆነንን እውነታ እንመልከት፡፡ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢዳር ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ጊዜ በታቦተ ጽዮን ፊት ለእግዚአብሔር በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ መንፈሳዊ መዝሙርን አቅርቦ ነበር ፡፡(2ሳሙ.6፡12-17) ይህን ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት በሐዲስ ኪዳንም ተፈጽሞል ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስት ኤልሳቤጥን በተሳለመቻት ጊዜ የስድስት ወር ፅንስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታችንን እናት የሰላምታ ድምፅ በሰማ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ከእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ በደስታ ዘሎአል(ሰግዶአል)፡፡ (ሉቃ.1፡44) ቅዱስ ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት እንዲያ ደስ መሰኘቱና ለአምላኩ የምስጋና ቅኔን መቀኘቱ ለሰው ልጆች ሁሉ የመዳናቸው ምክንያት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጁዋን ኢየሱስ ክርስቶስን በታቦተ ጽዮን በኩል በማየቱ ነበር፡፡

ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ይህንን እውነታ ይጋሩታል ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም፡- “ከአዳም ጎን በተገኘችው አንዲት አጥንት ምክንያት ሰይጣን ከአዳም ማስተዋልን አራቀ፡፡ ነገር ግን ከእርሱ አብራክ በተገኘችው በቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያት በእርሱ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን እንደ ዳጎን ተሰባብሮ ወደቀ፡፡ ታቦተ ጽዮን በተባለችው በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ባደረው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የድል አዋጅ ታወጀ ፡፡ በቃል ኪዳኑዋ ታቦት ሥር ዳጎን ተሰባብሮ እንደተገኘ እንዲሁ ክፉው ሰይጣን በታመኑበት ፊት ድል ተነሳ፡፡ እግዚአብሔር በቃል ኪዳኗ ታቦት ኃይሉን በመግለጥ ዳጎንን ሰባብሮ እንደጣለው እንዲሁ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ በኃጢአት ምክንያት በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሰይጣንን ድል ነሳው፡፡” (1ሳሙ.5፤6) ሲል ቅዱስ ጀሮም ደግሞ “ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስትና ንጽሕት ነበረች፡፡ በቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥ የሕጉ ጽላት ብቻ እንደነበር እንዲሁ እርሷም በሕሊናዋ ከእግዚአብሔር ሕግጋት ውጪ ሌላ ምንም ሃሳብ አልነበራትም፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በውስጥም በውጪም ነውር የሌለባት ንጽሕት ናት፡፡ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በውጪም በውስጥም በቅድስና የተጌጠችና ሕጉንም ጠብቃ የተገኘች የክርስቶስ ሙሽራ ናት ፡፡ በቃል ኪዳን ታቦቱ ውስጥ ከሕጉ ፅላት ውጪ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁ አንቺም ቅድስት ሆይ በሕሊናሽ ምንም ነውር የሌለብሽ ቅድስት ነሽ፡፡” ብሎ ሲያመሰግናት፤ የእስክንድርያው ዲዮናስዮስ ደግሞ “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን ይሆን ዘንድ በሰው እንዳልተመረጠ እንዲሁ ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታ ማደሪያ ትሆን ዘንድ በእግዚአብሔር የተመረጠችና በመንፈስ ቅዱስ ለእርሱ ማደሪያነት የተዘጋጀች ናት፡፡ የመለኮት ማደሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር የከተመባት ከተማ ሆና ትኖር ዘንድ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ታትማለች” በማለት ስለእርሱዋ ይመሰክራል፡፡

አዳም ድኅነቱ ከሴት ወገን በሆነች በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሆነ ተረድቶ  ለሚስቱ “ሔዋን” ብሎ ስም እንደሰጣት እንዲሁ ንጉሥ ዳዊት በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሚድን በመረዳቱ አምባዬና መጠጊያዬ ነሽ ሲላት “ጽዮን” ብሎ ለድንግል ስያሜን እንደሰጣት በመዝሙራቱ ማስተዋል እንችላለን፡፡ጽዮን የንጉሥ ዳዊት ተራራማዋ ከተማ ስትሆን፣ የስሟ ትርጓሜ አምባ፣ መጠጊያ ማለት ነው፡፡ ይህን ይዘው ብዙዎች ነቢያት ስለድንግል ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም ተጠቅመዋል፡፡

ነቢያት ስለቅድስት ድንግል ማርያም ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም እንደሚጠቀሙ ወደ ብሉይ ኪዳን ሳንገባ በሐዲስ ኪዳን ብቻ ስለ ጽዮን የተጻፉትን በማንሣት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ ከአይሁድ ወገን የሆኑ የራሳቸውን ሥርዐትና ሕግ ለማቆም ሲሉ በክርስቶስ ከማመን ስለተመለሱት ሲጽፍ፡- “እነሆ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ አለት አኖራለሁ”(ኢሳ28፡16፣8፡14) አለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ስለክርስቶስ የተነገረ ነው በማለት በሮሜ 9፡33 ላይ ጠቅሶት እናገኛለን፡፡ስለዚህም ነቢዩ ኢሳይያስና ቅዱስ ጳውሎስ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሆነ በዚህ ኃይለ ቃል  መረዳት እንችላለን፡፡ የማሰናከያ አለት የተባለው ክርስቶስ እንደሆነም “እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ ለእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፡፡”(ሉቃ.2፡34-35) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ስለዚህ የማሰናከያ አለት የተባለውን ክርስቶስን ፀንሳ የወለደችው ቅድስት ድንግል ማርያም ጽዮን መባሉዋን በእነዚህ ጥቅሶች ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

ነቢዩ ዳዊትና ኢሳይያስ ጽዮን ከተሰኘች የሙሴ ፅላት ካህኑ በሚያቀርበው መሥዋዕት አማካኝነት አፋዊ ድኅነት እንደተደረገ፣ ከእመቤታችን ከተወለደው አማኑኤል አማናዊ ድኅነት እንዲፈጸምልን“መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኝነትን ያስወግዳል”(መዝ.13፡10፤ኢሳ.59፡20) በማለት ስለክርስቶስ ትንቢትን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ሰጥቶ በሮሜ.11፡26 ላይ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም ቦታ ጽዮን ያሏት  ቅድስት ድንግል ማርያምን መሆኑን ማስተዋል እንችላለን፡፡ ምክንያቱም እርሱ ከእርሱዋ እንጂ ከሌላ አልተወለደምና፡፡ ነገር ግን “መድኃኒት” የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሆኑ “መልአኩም እንዲህ አላቸው፡-እነሆ ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ በዳዊት ከተማ መድኅኒት እርሱ ክርስቶስ ተወለደ” (ሉቃ.2፡10)በማለት ገልጾልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ማለት “መድኃኒት ማለት ነው (ማቴ.1፡21) የኢየሱስም እናት ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኑዋን ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህም ነቢያቱ “መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል” ሲሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዮን ከተባለችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

ምንም እንኳ ቅዱስ ዳዊትና ሌሎች ነቢያት ስለቅድስት ድንግል ማርያም ለመናገር ሲሉ ጽዮን የሚለውን ስም አብዝተው ይጠቀሙ እንጂ አልፎ አልፎ ግን ጽዮን በማለት ስለ ከተማዋ ተናግረው እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ሚክያስ “ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን ትታረሳለች”(ሚክ.3፡12)ይላል፡፡ ይህ በቀጥታ ስለጽዮን ከተማ የተነገረ ነው፡፡  ቅዱስ ጳውሎስ ስለጌታችን መናገር ሲፈልግ ስለእርሱ የሚናገሩትን ብቻ መርጦ እንደተጠቀመ እንመለከታለን፡፡ እኛም እንዲሁ ለቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩትን አስተውለን ልንለያቸው ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ስለቅድስት ድንግል ማርያም ያልተጻፉ ነገር ግን ጽዮን የሚለውን ስም ይዘው የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አሉና፡፡  ቢሆንም ስለታቦተ ጽዮን የተጻፉ ገቢረ ተአምራት ሁሉ እግዚአብሔር ቃል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለዶ ለፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ገቢረ ተአምራት ለድንግል ማርያምና ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ተርጉማ ለልጆቹዋ ታስተምራለች፡፡ በኅዳር 21 ቀንም በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙት ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ታላላቅ ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር በድኅነታችን ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድርሻ ምን እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ ለምሳሌ ታቦተ ጽዮንን የተሸከሙ ካህናት እግራቸው የዮርዳኖስን ባሕር በመንካቱ ባሕሩ ለሁለት እንደተከፈለ እንዲሁ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ ጥምቀትን በራሱ ጥምቀት በመመሥረት ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት እንዳሸጋገረን እናወሳበታለን(ኢያ.3፤ ማቴ.3፡13-17) ፡፡ ፍልስጥዬማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ውጊያ በገጠሙ ወቅት ታቦተ ጽዮንን ማርከዋት ዳጎን በሚባለው ቤተ ጣዖታቸው ውስጥ አኑረዋት ነበር፡፡ ነገር ግን ታቦቷ ዳጎኑን በፊቷ ሰባብራ እንደጣለችው እንዲሁ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን ድል መነሳቱን እናወሳበታለን፡፡ ((1ሳሙ.5፤6)

በዚህ መልክ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መንጎቹዋን ስለቅድስት ድንግል ማርያምና ስለልጁዋ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም በእርሱ ስለተሰጠን ሰማያዊ የአገልግሎት ሥርዐት፣ ስለታቦት ጥቅምና  አገልግሎት፤ ታቦተ ጽዮንንና ቅድስት ድንግል ማርያምን በማነጻጸር በሰፊው እንደምታስተምር መረዳት እንችላለን ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በእኛ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር አሜን!!

{flike}{plusone}