“እሱ እንደ ተዋሐደን እኛም እርስ በርሳችን ተዋሕደንና አንድ ሆነን በፍቅርና በሰላም እንድንኖር ነው” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደትን አስመልክቶው በመላ ዓለም ለሚኖሩ አማንያን የእንኳን አደረሳችሁ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው “እሱ እንደ ተዋሐደን እኛም እርስ በርሳችን ተዋሕደንና አንድ ሆነን በፍቅርና በሰላም እንድንኖር ነው” ብለዋል።

እርስ በርሳችን ተዋሕደንና አንድ ሆነን በፍቅርና በሰላም ስንኖር በዚህ ከእርሱ ጋር እንዋሐዳለን፥ ለወደፊቱም እግዚአብሔር ሁሉን አዋሕዶ በሚመጣው ዓለመ መንግሥቱ እውን የሚያደርገው ጣዕመ ሕይወት ይኽ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

መላእክት በቤተልሔም ለተወለደው ሕፃን ምስጋናና አምልኮ እንዳቀረቡ እኛም ለምስጋናና ለአምልኮ ተጠርተናል፣ እሱ ዓለመ ፍጥረትን በእጁ ጨብጦ የያዘ አምላክ ሲሆን፣ በከብቶች በረት ከእረኞች ጋር ውሎውና አዳሩ እንዳደረገ የገለጹት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እኛም ሁሌም ውሎአችንና አዳራችን ከምስኪኑ የኅብረተሰብ ክፍል ጋር በማድረግ የተራበውን በማብላት፣ የተጠማውን በማጠጣት፣ የታረዘውን በማልበስ፣ የታመመውንና የታሠረውን በመጠየቅ የጣፈጠ ጣዕመ ሕይወትን መምራት እንደሚያስፈልግ አውስተዋል።

በመጨረሻም በዚህ ወቅት ሀገራችን በመከራ እየተፈተነች ያለችበት ወቅት ከመሆኑ አንጻር ብዙ የተፈናቀሉ፣ የተጐዱና ኑሮ የተመሰቃቀለባቸው ወገኖች በየአካባቢው በብዛት መኖራቸው በማስታወስ በቤተልሔም የተወለደው ሕፃን ክርስቶስም ከእነሱ እንደ አንዱ ሆኖ በመካከላቸው እንደሚገኝ እሱ ራሱ ነግሮናልና እኛም እዚያው ተገኝተን እንድናስተናግደው ያስፈልጋል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመ/ር ኪደ ዜናዊ

ሙሉውን የበዓሉ መልእክት ታነቡ ዘንድ ከታች አያይዘን እነሆ ብለናል፦

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

ታኅሣሥ ፳ ፰ ቀን ፳ ፻ ወ ፲ ፬ ዓ.ም
አዲስ አበባ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፣

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣

የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣

በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ፡-

እኛን ለማዳን ሥጋችንን ተዋሕዶ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው በመሆን በዚህ ዓለም የተወለደው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

“ወውእቱ ቃል ሥጋ ኮነ ፥ ያ ቃል ሥጋ ሆነ” (ዮሐ. 1:14)
ቅዱስ እግዚአብሔር በአንድነት በሦሥትነት ኖላዊው፣ ጥንት በሌለው ጥንት የነበረ፣ አሁንም ያለ፣ ወደፊትም ፍጻሜ በሌለው ህላዌ የሚኖር አምላክ ነው፡፡

ከሦስቱ አካላት “ቃል” ተብሎ የተገለፀው አንዱ አካል ማለትም እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ በብሥራተ ገብርኤል፣ በግብረ መንፈስ ቅዱስ መጋቢት ሃያ ዘጠኝ ቀን በአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመተ ዓለም በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ተጸነሰ፡፡

“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ያ ቃል እግዚአብሔር ነበረ” ተብሎ ማንነቱ በቅዱስ ወንጌል የተረጋገጠለት “እግዚአብሔር ቃል” በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድሰት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ በመዋሐድ እንደኛ ፍጹም ሰው ሆነ፡፡

“እግዚአብሔር ቃል” ሰው ከሆነበት ቅፅበት አንሥቶ መለኮትነቱ ከሰውነቱ፣ ሰውነቱም ከመለኮትነቱ ባለ መለያየት፣ ባለ መጠፋፋት፣ ባለ መለዋወጥ፣ ባለ መከፋፈልና ባለ መቀላቀል አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ በመሆን የተፈጸመው የአምላካችን ምሥጢረ ተዋሕዶ ለዘላለሙ የጸና ነው፡፡

ይህ ምሥጢረ ተዋሕዶ እግዚአብሔር ለሰው ያለው የፍቅር ጥግ ያሳየ አምላካዊ ድርጊት ነው፡፡ ይህ አምላካዊ ፍቅር ሰውነትን ከባርነት ነጻ ማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ሰውነት በተዋሐደው መለኮት ምክንያት በመንበረ ጸባኦት ተቀምጦ የፍጥረት ሁሉ ገዢ እስከ መሆን ያበቃ ስለሆነ፣ ተመሳሳይም ሆነ ተነጻጻሪ ምሳሌ የማይገኝለት፣ ከፍቅር ሁሉ የሚበልጥ የእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር ነው፤ ለዚህም ነው “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” እያለ ቅዱስ መጽሐፍ የሚያስተምረን የአምላክና የሰው ተዋሕዶ በማኅፀነ ድንግል ማርያም ከተፈጸመበት ጊዜ አንሥቶ መለኮትነቱንና ሰውነቱን በሚገልጹ ስሞች አማኑኤል፣ ኢየሱስ፣ መሢሕ፣ ክርስቶስ፣ መድኃኔ ዓለም እየተባለ ይጠራል፡፡

እነኝህ ስሞች መለኮትነትን ብቻ፣ ወይም ደግሞ ሰውነትን ብቻ የሚያመለክቱ ሳይሆን የመለኮትና የሰውነት ተዋሕዶን በምሥጢር የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም በዛሬው ዕለት ታሕሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን የተወለደው ሕፃን ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው እንጂ ሰው ብቻም አይደለም፣ አምላክ ብቻም አይደለም፤ ይህም በመሆኑ ነው በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ” ተብሎ ለእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ለፍጡር የማይቀርብ ክብርና ምስጋና ከሰማይ ሠራዊተ መላእክት የቀረበለት፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የሌለ “እግዚአብሔር ቃል” ሰው ሊሆን የቻለው ሰውን ለማዳን ነው፡፡ ሰውን ለማዳን ሲባል የተፈጸመው ይህ ተዋሕዶ፣ በአምላክ ዘንድ ሰውን ማዳን ምን ያህል ታላቅ ነገር እንደሆነ ማስተዋል ለሰው ልጆች ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ምሥጢር ይልቅ ዓለምን ያዳነበት እንደሚበልጥ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡
ይህ የአምላካችን አድራጎት እኛም ሰውን ከማዳን የበለጠ ሥራ ሊኖረን እንደማይገባ የሚያስገነዝብ ነው፡፡

ከጌታችን ልደት ምሥጢራዊ መልእክት እንደምናስተውለው አንድነትን፣ ፍጹም ፍቅርን፣ ምሉእ ሰላምን፣ እግዚአብሔርን በመዝሙር ማመስገንን እና ማምለክን፣ ከተቸገሩት ማኅበረሰብ መካከል ተገኝቶ የሰውን ችግር ተካፋይ መሆንን ከአምላክ የተቸረን ፍጹም በረከት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ምሥጢረ ተዋሕዶ፣ ዝማሬ መላእክቱ፣ በከብቶች በረት መወለዱ፣ ለእረኞች መገለጡ፣ በዕለተ ልደቱ ከተገለጡ ዓበይት ክሥተቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በዚህም ቤተልሔም የእግዚአብሔር ክብር የበራላት፣ የመላእክትና የእረኞች መዝሙር የደመቀላት፣ እግዚአብሔር፣ መላእክትና ሰዎች በአንድነት የተገኙላት የእውነተኛይቱ መንግሥተ እግዚአብሔር ማሳያ ሆኖ ተገኝታለች፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፣

በቤተልሔም የታየው አምላካዊ መገለጥ ተአምረ አምላክ ብቻ ሳይሆን፣ በዕለቱ ከታየው ጣዕመ ሕይወት ትምህርት ወስደን እሱን እንድንለማመድ ብሎም እንድንከተል የሚያስገነዝብ አምላካዊ መልእክት የተላለፈበት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በመካከላችን የተገኘበት ዓቢይ ምሥጢር በአንድነት፣ በሰላምና በፍቅር የተወደደ እንደ ዕለተ ልደት ያለ ጣዕመ ሕይወት እንዲኖረን ብሎ እንደሆነ ልናውቅ ይገባል፡፡ ይኸውም እሱ እንደ ተዋሐደን እኛም እርስ በርሳችን ተዋሕደንና አንድ ሆነን በፍቅርና በሰላም እንድንኖር ነው፡፡ ይህንን ስናደርግ በዚህ ከእርሱ ጋር እንዋሐዳለን፥ ለወደፊቱም እግዚአብሔር ሁሉን አዋሕዶ በሚመጣው ዓለመ መንግሥቱ እውን የሚያደርገው ጣዕመ ሕይወት ይኸው እንደሆነ መገንዘብ አለብን፣ መላእክት በቤተልሔም ለተወለደው ሕፃን ምስጋናና አምልኮ እንዳቀረቡ እኛም ለምስጋናና ለአምልኮ ተጠርተናል፣ እሱ ዓለመ ፍጥረትን በእጁ ጨብጦ የያዘ አምላክ ሲሆን፣ በከብቶች በረት ከእረኞች ጋር ውሎውና አዳሩ እንዳደረገ፣ እኛም ሁሌም ውሎአችንና አዳራችን ከምስኪኑ የኅብረተሰብ ክፍል ጋር በማድረግ የተራበውን በማብላት፣ የተጠማውን በማጠጣት፣ የታረዘውን በማልበስ፣ የታመመውንና የታሠረውን በመጠየቅ የጣፈጠ ጣዕመ ሕይወትን መምራት ይኖርብናል፡፡

ዛሬ ሀገራችን በመከራ እየተፈተነች ያለችበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ የተፈናቀሉ፣ የተጐዱና ኑሮ የተመሰቃቀለባቸው ወገኖች በየአካባቢው በብዛት መኖራቸው ይታወቃል፣ በቤተልሔም የተወለደው ሕፃን ክርስቶስም ከእነሱ እንደ አንዱ ሆኖ በመካከላቸው እንደሚገኝ እሱ ራሱ ነግሮናል፣ ታድያ እኛም እዚያው ተገኝተን እንድናስተናግደው የወቅቱ ዓቢይ ጥሪያችንና መልእክታችን ነው፡፡

በመጨረሻም፡-

በቤተልሔም ዙሪያ የጐረፈው የእግዚአብሔር ክብርና ብርሃን፣ ሰላምና ዕርቅ፣ ተዋሕዶና ምስጋና በሀገራችንም ሰፍኖ ወደ ፍጹም ሰላምና አንድነት እንደርስ ዘንድ፣ እግዚአብሔርን በጸሎት ከመለመን ጋር ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለሰላም ለፍቅርና ለአንድነት ያላሰለሰ ጥረት እናደርግ ዘንድ አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም በዓለ ልደት ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ
ዘአክሱምወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ታሕሣሥ ፳ ፱ ቀን ፳ ፻ ወ፲ ፬ ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ