“ኢትዮጵያ የእግዚአብሄር ንዋየ ቅድሣት ሀገር ናት !!!” ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ዛሬ ህዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በተገኙበት በደብረ ምጥማቅ ሠአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካቴድራል የእመቤታችን ንግሥ ተከብሮ ውሏል።
በአውደ ምህረቱ የካቴድራሉ መምህራን “ሙሴኒ ርዕያ ሀገር ቅድስት የሚለውን እና አባ አቡነ አባ መምህርነ አባ መልከጴዴቅ” የሚለውን ለብፁዕነታቸው በሽብሻቦ አቀርበዋል። የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም ታቦተ ሕጉ የሚለውን ዝማሬ በጥሩ መናበብ ዘምረዋል።
በዐሉን በማስመልከት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምርህትና ሥልጠና ዋና ክፍል መልአከ ምህረት በቃሉ ወርቅነህ ከመጽሐፈ ሣሙኤል ከምዕራፍ 5 ቁጥር 7 ወአሀዘ ዳዊት ጽዮንሃ ሀገረ የሚለውን ጠቅሰው ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል።ጽዮን ማለት አንምባ መጠጊያ ማለት መሆኑን አንስተው ታቦተ ጽይንን የያዙ አባቶቻችን አፍረው እንዳልተመለሱ ገልጸው ከወቅቱ የኢትዮጵያ ችግር ጋርም አነጻጽረው ጽዮንን ይዘን አናፍርም አንፈራምም ሲሉ ደማቅ እልልታ ነበረ።
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ሀይለመለኮት ይሄይስ የንግሥ መድረኩን እየመሩ በየመሀሉ የቤተ ክርስቲያኗን የነገ ያሉትን ተስፈንጣሪ ሀሣብ ተተኪ ካህናት የሚፈልቁበትን መንፈሣዊ ልማት በዝርዝር አቀርበዋል። የአብነት ትምህርት ቤት ለመስራት አፈር ጠረጋውና ማስተካከሉ በጥሩ ሁኔታ እንዳለና ለዚህም የሠበካ መንፈሣዊ ጉባኤና የልማቱን ደጋፊዎች መልአከፀሐይ በትህትና ተሞልተው አመሠግነዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የዕለቱ ትምህርት በሰፊው በመልአከምህረት በቃሉ መሠጠቱን አድንቀው የክቡር አስተዳዳሪውን የሠላምና ቁሣዊ ልማትንም በእሠየው አበረታተዋል።
አዲስ አበባ ብዙ የእመቤታችን አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉና ዛሬም በብዙ አድባራት ቅድስት ድንግል ማርያም እየተከበረች መሆኗ ደስ ይለኛል ለምን ግን ታድያ እንደብዛታችን የዚህ ሁሉ ፀሎት አልተሰማም ሲሉ ጠይቀዋል። ሠባኪውም ተሠባኪውም በዝቷል አሁን የሚያስፈልገው በእምነት ጸንተን ለተግባር መነሣት ነው ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ይብል ሠብዕ እምነ ጽዮን የሚለውን የዳዊት መዝሙር የትምህርት ርዕስ አድርገው ስለታቦተ ጽዮን እጅግ ጣፋጭ ትምህርት የሰጡት ብፁዕነታቸው እኛ የጽዮን ባለቤቶች እንጂ አስተዋሾች አይደለንም ብለዋል።
የሠው ልጅ እንኳን እግዚአብሄርን እሱ የፈጠራትን ፀሐይን እንኳ በሙሉ አይኑ ማየት ስለማይችል ሊያየውና ሊዳሰው በሚችለው በታቦተ ሕጉ ላይ በእጁ የተጻፉ አስርቱ የመጀመሪያ የጽሑፍ ትዕዛዛት ተሰጡት ብለዋል።
የእስራኤል መመኪያ ጽዮን ናት የኛ መመኪያ እንድትሆንም ተሰጥታናለች ያሉት ብፁነታቸው ታቦተ ጽዮን በኢትዮጵያ መሆኗንና ኢትዮጵያ የእግዚአብሄር ንዋየ ቅድሣት መሆኗን ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ ችግር ውሃ እናፍስ ይብስ የሚያቀጣጥል ነገር አናፍስ ብለው ብፁነታቸው ሲናገሩ የምዕመናኑ ስሜት የፍቅር እሺታ ይነበብበት ነበር። ብፁነታቸው ቃለምዕዳን አድርገው ታቦታተ ሕጉ ወደ መንበረ ክብራቸው ሲመለሱ ነጫጭ የለበሱ ምዕመናን እልልታና አሜንታ ልብ ያሞቃል።
ፀአዳ የለበሱ ምዕመናን በሰፊው የካቴድራሉ ግቢ ችምችም ብለው ከመቆማቸው የተነሣ ከዋክብት ቦታ ቀይረው ከሠማይ ወደ ሠአሊተ ምህረት የረገፉ ይመስል ነበረ።
በተክለሃይማኖት አዳነ (ጋዜጠኛ)