አዲስ ከተመደቡት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ እና ሌሎችም አዲስ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የትውውቅ መርሐ ግብር ተደረገ
ታህሳስ 2 ቀን 2013 ዓ/ም የጉራጌ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ ፕሬዘዳንት ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች እና ሠራተኞች እንዲሁም የሰባቱ ክፍላተ ከተሞች ሥራ አስኪያጆች እና ሠራተኞች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ ሀገረ ስብከቱ አዲስ ከተመደቡት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተስማ እና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ጋር ትውውቅ ተደርጓል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ አጭር ንግግር ያደረጉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተስማ “ዛሬ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፊት የተሰጠኝን የሥራ ኃላፊነት ተቀብየ፣ በፊታችሁ በመቆሜ ደስተኛ ነኝ፣ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ይህንና ያንን እናደርጋለን በሉ በሚለው ሕያው ቃል መሠረት እኔም ከብፁዕ አባታችን አባታዊ መመሪያ በመቀበል ከእናንተ ከአባቶቼና የሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን የሀገረ ስብከታችንን ብሎም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ዕድገት እናፋጥናለን፣ የተሰጣቸውን ዘመን በሙሉ በትምህርት ዝግጅት ካሳለፉ፣ መንፈሳዊነትን ከለውጥ ፍላጎት ጋር ካጣመሩ ከመንፈሳዊ አባቴ ከብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ጋር ለመሥራት ዕድል በማግኘቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ፣ እዚህ ያላችሁ ሁላችሁም ሀገረ ስብከታችን አሁን ላለበት ከፍተኛ ደረጃ ለመድረሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከታችሁ ናችሁ፣ ወደፊትም በምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ አብራችሁን እንደምትሰለፉ አምናለሁ፣ ለውጥ የሚፋጠነው አቅማችንን በማስተሳሰርና አንድነታችንን በማጠናከር ነው፡ ስለሆነም እኛ እንደ ሥራ ኃላፊዎች ለሥራ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላት፣ እናንተ ደግሞ ለለውጥ በመፋጠን ተቋማችንን እንለውጥ፣ በሠራንበት ልክና መጠንም የጥቅም ተቋዳሽ እንሁን በማለት አሳስበዋል::
በመቀጠልም የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ ፕሬዘዳንት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ” የትኛውም ሰው የራሱና የቤተሰቡ መሪ ነው፣ ነገር ግን የመሪነት ፈተናው የሚበረታው እና የሚከብደው በተቋማትና በሀገር ላይ የተመደብን ቀን ነው፣ ምክንያቱም ለመሪነት የሚያስቸግሩ ሻካር መንገዶች እና አስተሳሰቦች ሊያጋጥም ስለሚችል ነው፣ እንደዚህ ዓይነቱን የመሪነት ፈተና በአግባቡ ለመወጣት እውቀትን፣ እምነትን እና እውነትን ይዞ መጓዝ የአንድ መንፈሳዊ መሪ የመሪነት ግዴታ ነው፣ እነዚህን የያዘ መሪ በተሰበረ ድልድይ ላይ መሻገር ይችላል፣ የተመደቡላችሁም አዲሱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በእነዚህ ዐምዶች ላይ መሠረታቸውን ጥለው የሚመሩ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሀገረ ስብከቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅነት እና ዋና ጸሐፊነት ያደረገውን የሥራ ውድድር እና ውድድሩን አልፈው ለዋና ሥራ አስኪያጅነት የተመደቡትን የሥራ አመራር እንዲሁም ደግሞ ሀገረ ስብከቱ እየተከተለው ያለውን አዲስ አደረጃጀትና አሠራር በሰፊው ገለጻ አድርገዋል::
አያይዘውም የሀገረ ስብከቱን ችግሮችለመቅረፍ እና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ አዎንታዊ አስተሳሰብ እንገንባ፣ በዕቅድ በመመራት እና ታማኝነትን በማስፈን ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንወጣ፣ ለተቋሙ ይጠቅማል ያልነውን ማንኛውንም ሐሳብ እንጋራ በማለት አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ፡-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ