አዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በዳግማዊ ደብረ ሊባኖስ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ዓመታዊው የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የልደታቸው ክብረ በዓል በድምቀት ተከበረ

በዛሬው ዕለት ታኅሣሥ 24 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ አሚን አባ ኃይለማርያም፣የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣የገዳሙ አገልጋዮችና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች አንዲሁም በርካታ ምእመናን በተገኙበት በዳግማዊ ደብረ ሊባኖስ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ዓመታዊው የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የልደት ክብረ በዓል በሥርዓተ ማኅሌት፣በቅዳሴና ያሬዳዊ ዜማ ታጅቦ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በዕለቱ ያስተማሩት የሙሁር ገዳም አበምኔት ቆሞስ አባ ዘኢየሱስ ሲሆኑ ‹የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ› በሚል የቅዱስ ጴጥሮስ ቃል መነሻነት ስለ ቅድስና ሰፋ ያለ ትምህርት አስተምረዋል፡፡ በዚህ ጥሪ ተጠርቶ ቅድስናውን ያከበረና በቅድስና የኖረ አቡነ ተክለሃማኖት ቅዱስ ብለን እንጠረዋለን ብለዋል፡፡ አያይዘውም በቀራንዮ መስቀል የጠራን የቅዱስ እግዚአብሔር አብ ልጅ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስና እንድንኖር ነውና ጥሪያችንን አክብረን በጽድቅና በቅድስና ሕይወት ልንኖር ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የተሰጠውን የቅድሰና ትምህርት ልንተገብረው ይገባል፤ ሁለት ቅዱሳን ቅዱስ ወልደው ቅድስና አሰተምረውታል፤ እኛም የተማርነውን የቅድስና ትምህረት በተግባር እንግለጸው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ወንጌል ሕይወት ነው፣ እውነት ነው፣ አንዲሁም ኑሮ ነውና በተግባር ማሳየት አለብን፤ ነገረ ቅዱሳን ሰምተን ተምረን ወደ ቅድስና ሊያደርሰን ይገባል ሲሉ ስለ ቅድስና አብራርተው አስተምረዋል፡፡
የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ አሚን አባ ኃይለማርያም ባደረጉት አጭር ንግግር ገዳሙ ለምእመናን የሚጠቅም ብዙ መልካም የልማት ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፤ ከነዚህም መካከል 19 ሚልዮን ብር የሚፈጅ ጸበል ቤት፣የጥምቀትና የሕሙማን ማረፊያ ያለው የተሟላ ህንጻ፣ 219000 ብር የሚፈጅ ሁለ ገብ ህንጻና በርከት ያሉ ክፍሎች ያለው ፎቅ በመገንባት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ የተገኙ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍም በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን እንደሚሻል በመግለጽ፣ እኛም እንደ ቅዱሳኑ ሁሉ ከሰው ይልቅ በእግዚአብሔር መታመኑ አማራጫ የሌለው ውሳኔያችን መሆን እነዳለበት መክረዋል፡፡
በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ምህላ ተደርጎ በጸሎትና ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።
መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ