አዲስ ተሠርቶ የተጠናቀቀው የአንቆርጫ ኮተቤ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ሕንጻ ቤ/ክ ብፁዓን ለቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በጸሎት ተባረከ
በዛሬው ዕለት ጥር 29/2013 ዓ.ም የሱማሌና የምሥራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ፣የሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና የየካ ክፍለከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች፣የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም በርካታ ምእመናን በተገኙበት አዲስ ተሠርቶ የተጠናቀቀው የአንቆርጫ ኮተቤ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ሕንጻ ቤ/ክ በጸሎት ተባርኳል።
መርሃ ግብሩን የመሩት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ የሆኑት መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ለቡራኬና ለአገልግሎት በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የዕለቱን ትምህርተ ወንጌል የሰጡት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ “ምሕረቱ፣ቸርነቱ ፣ፍቅሩና ይቅርታው” ብዙ የሆነውን ልዑል እግዚአብሔርን አመስግነው “እግዚአብሔር ሆይ ስማ” በሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕስ ተነስተው ሰፋ ያለ ትምህርት ያስተላለፉ ሲሆን በዚህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተሰቀለልንን፣የሞተልንን፣ ሞትንም ድል አድርጎ የተነሣውንና ዘወትር የሚሰማንን መድኃኔዓለምን በማመስገንና ባፈሰስከው ደምህ ይቅር በለን በማለት ወደ እርሱ መጸለይ እንደሚገባን አጽንዖት ሰጥተው አስተምረዋል።
አያይዘውም እናንተ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ የሆናችሁ ባነጻችሁት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ውስጥ እራሳችሁን በወንጌል አንጹ፣ ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን ተቀበሉ በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የሽልማት ሥነ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን ለአዲስ አበባና ለጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እያበረከቱት ላለው መልካም አስተዳደር በተወካያቸው በኩል ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
በተጨማሪም ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለመ/ር አካለ ወልድ ተሰማ፣ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ፣ ለየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ እሰኪያጅ መጋቤ ትፍስሕት ግርማ አሰፋና እንዲሁም ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ሢሠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት ስጦታ ተበርክቷል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ለደብሩ አስተዳዳሪ ለመልአከ ብርሃን አውላቸው ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ግሩም በሆነ መልኩ ተጠናቆ ለቡራኬ እንዲደርስ ላበረከቱት ቆራጥ አመራር አመስግነውና ቃለምዳን ሰጥተው መርሃ ግብሩ ተፈጽሟል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ